“ኮትዲቯርን እናከብራለን፣ ነገርግን ከፍተኛም ሆነ ዝቅተኛ ግምት አንሰጣቸውም” አብርሃም መብራቱ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ከነገው የኳትዲቯር ጨዋታ በፊት አስተያየታቸውን ለጋዜጠኞች ሰጥተዋል።

ስለ ዝግጅት

“ለኮትዲቯሩ ጨዋታ ዝግጅት የጀመርነው መቐለ ላይ ነበር። ከማዳጋስካሩ ጨዋታ በኋላ ያደረግናቸው ዝግጅቶች የማገገምያ ስራዎች ናቸው። ምክንያቱም ጠንካራ ልምምዶችን የማድረጊያ ጊዜ ስላልነበረን። በአጠቃላይ በስነ ልቦናም ረገድ ቡድኑ ጥሩ ዝግጅት አድርጓል።”

ዛሬ ቡድኑን ስለተቀላቀሉ 4 ተጨዋቾች

“አዲስ ተጨዋቾችን አልቀላቀልንም። ወደ ማዳጋስካር መሄድ የነበረባቸው 20 ተጨዋቾች ብቻ ስለነበሩ ነው እንጂ ተጨዋቾቹን መጀመሪያም አልቀነስንም። እኛ ያደረግነው ተጨዋቾቹ በየክለባቸው ልምምድ እየሰሩ እንዲጠብቁን ነው።”

ስለ ማዳጋስካሩ ጨዋታ…

“በጨዋታው በመጀመሪያ 10 እና 15 ደቂቃዎች ጫና መቋቋም ከብዶን ነበር። ይህም የሆነው ደግሞ በቡድኔ ውስጥ ወጣት ተጨዋቾች ስላሉ ነው። በጨዋታው ግቧ ከቆመ ኳስ ከተቆጠረብን በኋላ ወደሚፈለገው መንገድ ገብተን ለመጫወት ሞክረናል። በቀሪ የጨዋታው ክፍለ ጊዜም ከተጋጣሚያችን በተሻለ ተንቀሳቅሰን ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረናል። ነገር ግን በነበረብን የአጨራረስ ድክመት ማሸነፍ ወይም አቻ መውጣት ሳንችል ቀርተናል። በአጠቃላይ ግን በሁለተኛው አጋማሽ ማዳጋስካርን በልጠን መጫወታችን እንደጥሩ ነገር ይዘን መነቃቃቱን ለማስቀጠል እንሰራለን።”

ቡድኑ በቆመ ኳስ ስለሚቸገርበት ጉዳይ

“እኛ በየጊዜው እንሰራለን። ከቆሙ ኳሶች እኛ ተጠቃሚ ለመሆን በተከታታይ ስራዎችን እየሰራን ነው። እንደሚታወቀው በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ያሉ ተጨዋቾች የቆመን ኳስ ለመጠቀም የሚያስችል በቂ ግንዛቤ የላቸውም። ይህ ነገር ደግሞ በ8 እና በ10 ቀን ብቻ በሚሰሩ ልምምዶች የሚቀረፉ አደለም። ነገር ግን ከሌላው ጊዜ እየተሻሻለ እንደሆነ መናገር ይቻላል። በማዳጋስካሩ ጨዋታ እንኳን ማዳጋስካሮች ካገኟቸው 13 የቆሙ ኳሶች አንዱን ብቻ ነው የተጠቀሙት። ይህ የሚያሳየው ቡዙው ለመቀነስ ተሞክሯል ማለት ነው። ቢሆንም ግን ወደ ፊት ያለውን ነገር ለማሻሻል እንጥራለን።”

ቡድኑ እያሳየ ባለው እንቅስቃሴ ደስተኛ ነህ?

“አዎ ጥሩ ነው። ከውጤቱ ጋር የተያያዘ ሳይሆን ቡድኑ በወጣቶች የተገነባ መሆኑ እና እያሳየ ባለው እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ። እኔ የምፈልገው የልጆቹን በራስ መተማመን ማሳደግ ነው። በአጠቃላይ ግን በቡድኑ እንቅስቃሴ ደስተኛ ነኝ።”

ስለ ኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን

“ምንም ጥርጥር የለውም የኮትዲቯር ብሄራዊ ቡድን ጠንካራ ብቃት ያላቸውን ተጨዋቾች የያዘ ቡድን ነው። ነገር ግን እኛ የኮትዲቯርን ቡድን እንዴት ማሸነፍ እንዳለብን ነው እንጂ የምናስበው ስለ ቡድኑ ግዝፈት አናወራም። ቡድኑን እናከብራለን ነገርግን ከፍተኛም ሆነ ዝቅተኛም ግምት አንሰጣቸውም። ትልቅ ግምት የምንሰጠው ለራሳችን አጨዋወት ነው።”


© ሶከር ኢትዮጵያ