ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ባህር ዳር ከተማ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት ነገ ሲቀጥል አዳማ ላይ ጅማ አባ ጅፋር ባህር ዳር ከተማን ያስተናግዳል።

ጅማ አባ ጅፋር ባለፈው ዓመት የተላለፈበት የሜዳ ቅጣት ወደ ዘንድሮ በመሸጋገሩ ጅማ ላይ መደረግ የነበረበት ይህ ጨዋታ አዳማ ላይ የሚካሄድ ይሆናል።

ባለፈው ዓመት እንዳደረጉት ሁሉ በዘንድሮው ክረምትም በርካታ ተጫዋቾችን በማስፈረም ጳውሎስ ጌታቸውን አሰልጣኝ አድርገው የቀጠሩት ጅማ አባ ጅፋሮች ስብስባቸው ካለፉት ዓመታት አንፃር የተዳከመ ሲሆን በቅድመ ውድድር ጊዜም ጥሩ ያልሆነ ጊዜያትን አሳልፈዋል።

ሜዳ ላይና ከሜዳ ውጪ በበርካታ ውጥንቅጦች የተተበተው ቡድኑ በአዳማ ከተማ ዋንጫ ተሳትፎው በርካታ ክፍተቶች እንዳሉበት ተስተውሏል። በመከላከሉም በማጥቃቱም ረገድ በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ጅማ በቀጥተኛ አጨዋወት ወደፊት ለመሄድ ጥረት ቢያደርግም ቡድኑ የአየር ላይ ኳስ አጠቃቀም ላይ ግን ሰፊ ክፍተቶች ይስተዋልበታል። ቡድኑ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ከክለቡ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾች ግልጋሎት የሚያገኝ ከሆነ ነገሮች በመጠኑም ቢሆን መሻሻል ያሳያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አባ ጅፋር በነገው ጨዋታ አዲስ ፈራሚዎቹ መሐመድ ሙንታሪ ሙንታሪ፣ ያኩቡ መሐመድ እና አሌክስ አሙዙን የፓስፖርት ጉዳዮች ባለመጠናቀቃቸው የማያሰልፍ ሲሆን አጥቂው ብዙዓየሁ እንዳሻውም በጉዳት አይሰለፍም። ዘሪሁን ታደለም በጉዳት የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው።

እንደጅማ ሁሉ አዲስ አሰልጣኝ በመቅጠር የውድድር ዓመቱን የሚጀምሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከዓምና ስብስባቸው ላይ የተወሰኑ ለውጦችን አድርገው በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ እየተመሩ የውድድር ዓመቱን ይጀምራሉ።

ባህርዳር ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ በነበረው ቆይታ በመልሶ ማጥቃት ቁመና የተገነባ ቡድን ሆኖ ቀርቧል። የጣና ሞገዶቹ ከኳስ ውጪ በጥልቀት ተደራጅተው በመከላከል እንዲሁም ኳሷችን በፍጥነት ከመከላከል ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ በማስገባት ተጋጣሚዎች ሳይደራጁ ጥቃት ለመሰንዘር ሙከራ ያደርጋሉ። ቡድኑ አምና የነበረበትን ግብ የማስቆጠር ችግር ለመቅረፍ ግዙፉ ማሊያዊው አጥቂ ማማዱ ሲዲቤ በተለይ ቡድን ለመከተል የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አይነተኛ መሳሪያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ባህር ዳር ከተማ ግርማ ዲሳሳን በጉዳት ሚካኤል ዳኛቸውን ደግሞ በቅጣት በዚህ ጨዋታ አይጠቀሙም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ዐምና በፕሪምየር ሊጉ በተገናኙባቸው ጨዋታዎች በመጀመሪያው ዙር 1-1 በሆነ ውጤት ሲለያዩ በሁለተኛው ዙር ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጪ 1-0 መርታት ችሎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ጀሚል ያዕቆብ – ከድር ኸይረዲን- መላኩ ወልዴ- ኤልያስ አታሮ

ንጋቱ ገብረሥላሴ – ኤልያስ አህመድ – ኤርሚያስ ኃይሉ

አምረላ ደልታታ – ተመስገን ደረሰ – ሱራፌል ዐወል

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ሀሪሰን ሄሱ

ሚኪያስ ግርማ – አዳማ ሲሶኮ – አቤል ውዱ – ሳላምላክ ተገኝ

ፍ/ሚካኤል ዓለሙ – ዳንኤል ኃይሉ – ፍፁም ዓለሙ

ፍቃዱ ወርቁ – ማማዱ ሲዲቤ – ወሰኑ ዓሊ


© ሶከር ኢትዮጵያ