ሪፖርት | ሀዋሳ ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋን አሸንፏል

በአማኑኤል አቃናው 

በ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ሣምንት በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ስታድየም ሀዋሳ ከተማ ድሬዳዋን ከተማን አስተናግዶ 2-1 አሸንፏል።

ጨዋታው የዕለቱ ዕንግዶች ከተጫዋቾች ጋር ባደረጉት ትውውቅ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የተጀመረ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን ወደ ግብ በመድረስ ቀዳሚ በነበሩት ድሬዳዋዎች በኩል በተከላካዮች ስህተት የተገኘችውን አጋጣሚ ኤልያስ ማሞ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል።

ግብ ካስተናገዱ በኋላ ተጭነው የተጫወቱት ሀዋሳዎች በሄኖክ ድልቢ ፣ ብሩክ በየነ ፣ መስፍን ታፈሰ እና አለልኝ አዘነ በተደጋጋሚ ወደ ግብ መድረስ ችለው የነበረ ቢሆንም በድሬዎች ጥብቅ የመከላከል አጨዋወት ምክንያት ፍሬ ማፍራት ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሲቃረብም ሀዋሳዎች የተከላካይ መስመር ተጫዋቻቸው መሣይ ጳውሎስ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት በፀጋአብ ዮሃንስ ቀይረው ለማስወጣት ተገደዋል።

ከዕረፍት መልስ ዳንኤል ደርቤን በዘላለም ኢሳያስ ቀይረው ያስገቡት ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ግብ በመድረስ የተሻለ ጫና ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በዚህም ጥረታቸው ቀጥለው 58ኛው ደቂቃ ላይ መስፍን ታፈሰ ከአለልኝ አዘነ የተሻገረለትን ኳስ ተቀብሎ ባስቆጠራት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በሀዋሳዎች የጨዋታ ብልጫ እና አልፎ አልፎ በሚሰነዘረው የድሬዳዋዎች የመልሶ ማጥቃት የቀጠለው ጨዋታ 73ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል።

ብርሀኑ በቀለ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የብርቱካናማዎቹ ተከላካይ ዘሪሁን አንሼቦ በእጅ በመንካቱ ሀዋሳዎች የፍፁም ቅጣት ምት ያገኙ ሲሆን አዲስዓለም ተስፋዬ መትቶ በግብ ጠባቂው ቢመለስበትም በቅርብ የነበረው ብሩክ በየነ ማስቆጠር ችሏል። አጋጣሚው ኢንተርናሽናል ዳኛ ብሩክ የማነብርሀን ዘሪሁን አንሼቦን በቀይ ካርድ ከሜዳ ያስወጡበትም ሆኖ አልፏል። ጨዋታውም የውጤት ለውጥ ሳይታይበት በባለሜዳዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በጨዋታው ድሬዳዋ ከተማዎች በቅጣት ላይ የሚገኙት አሰልጣኝ ስምዖን ዓባይን ግልጋሎት አላገኙም።


© ሶከር ኢትዮጵያ