ከፍተኛ ሊግ ለ | ኢኮሥኮ፣ ነቀምቴ እና ሻሸመኔ ዓመቱን በድል ከፍተዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተከናውነው ኢኮሥኮ፣ ነቀምት ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ በሜዳቸው ድል አስመዝግበዋል።

ቦንጋ ላይ ካፋ ቡናን ከቤንች ማጂ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል። የካፋ ቡና ደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነትን በተላበሰ መልኩ ለቤንች ማጂ ቡና ደጋፊዎች ደማቅ አቀባበል አድርገው የተጀመረው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፍክክር የታየበት ሲሆን በመጀመሪያው 45 የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በረጅም የሚጣሉ ኳሶች የበዙበት ሆኖ አልፏል።

ቤንች ማጂ ቡና ጫና በመፍጠር በተደጋጋሚ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ያደረገ ቢሆንም ያንን እድል ወደ ጎል የሚቀይር ተጫዋች አልነበረም። በአንፃሩ ካፋ ቡና በመልሶ ማጥቃት ወደ ተጋጣሚው የግብ ክልል ሲደርስ ነበር። በየመሃሉ የሚፈጠሩ ጥፋቶችን በቀጥታ ወደ ግብ በመላክ ያንን ለመጠቀም ከሚደረግ ሙከራ ውጭ የረባ በራስ ጥረት ግብ ለመፍጠር የተደረገ ሙከራ ግን አልነበረም።

ከእረፍት መልስ የቤንች ማጂ ቡናው አጥቂ ፎሳ ሴንዴቦ ጨዋታው እንደተጀመረ አክርሮ የመታት ኳስ ግብ ጠባቂው በእግሩ የመለሰበት ጥሩ የግብ ዕድል ሆናለች። በ53ኛው ደቂቃም ካፋ ቡና ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በተለይም በመስመር በኩል የሚፈጥሯቸው እድሎች ተጠቃሚ አላደረጋቸውም እንጂ።

የቀድሞ ክለቡን የገጠመው የቤንች ማጂ ቡናው አጥቂ ኦኒ ኡጁሉ በግንባሩ ገጭቶ በግብ ጠባቂው ጥረት የዳነች ጥሩ አጋጣሚ ነበረች። በመጨረሻዎቹ ደቂቃ ካፋ ቡናዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ለመጠቀም ጥረት አድርገው ከግቡ አግዳሚ በላይ ወጥታለች። ጨዋታውም ጎል ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

መድን ሜዳ ላይ ኢኮሥኮን ከጅማ አባ ቡና ያገናኘው ጨዋታ በባለሜዳው 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። የአሰልጣኝ በፀሎት ስብስብ ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ እንደ አዲስ ቢገነባም ከጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጋር አሸንፏል። በ52ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን በጅሮንድ እንዲሁም በጨዋታው መጠነቀቂያ ላይ ፈጣኑ የመስመር የጫዋች አብዱልለጢፍ ሙራድ የኢኮሥኮን ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ወደ ነቀምቴ ያመራው ሀላባ ከተማ ሽንፈት አስተናግዷል። የምድብ ለውጥ ያደረገው ነቅምቴ ከዕረፍት በፊት በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ነው በድል ዓመቱን የጀመረው። ወደ ቀድሞ ቡድኑ የተመለሰው ኢብሳ በፍቃዱ በ25ኛው ደቂቃ እንዲሁም ቡና ቦቃ በ33ኛው ደቂቃ ጎሎቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ሻሸመኔ ከተማ አዲስ አዳጊው ጋሞ ጨንቻን በጠባብ ውጤት 1-0 አሸንፏል። አሰልጣኝ አብዲ ቡሊን የቀጠረው ሻሸመኔ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ አሸናፊ ጥሩነህ ባስቆጠረው ግብ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችሏል።

ሶዶ ላይ ወላይታ ሶዶ ከሀምበሪቾ ያለ ጎል የተጠናቀቀ ጨዋታ ሲሆን መከላከያ ከ አዲስ አበባ ከተማ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ጊዜ ተሸጋግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ