ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ከድንቅ እንቅስቃሴ ጋር የዓመቱን የመጀመርያ ድል አስመዝግቧል

በርከት ያሉ የግብ ማግባት ሙከራዎች በተስተናገዱበት የ4ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ሀዋሳ ከተማን 4-1 አሸንፏል።

ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች በ3ኛ ሳምንት ወደ ሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል አምርተው ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የመጀመርያ 11 አንድ ተጨዋች ብቻ ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል። በዚህም አቡበከር ናስርን በሚኪያስ መኮንን በመተካት ጨዋታውን አከናውነዋል። በተጋባዦቹ በኩል ቡድኑ በሜዳዉ ባህር ዳርን ከረታው የተጨዋች ስብስብ ሦስት ለውጦችን አድርጓል። በዚህም አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ዘላለም ኢሳይያስ፣ መስፍን ታፈሰ እና እስራኤል እሸቱን በየተሻ ግዛው፣ ብሩክ በየነ እና አዲስዓለም ተስፋዬ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

በኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት የተጀመረው ጨዋታው የግብ ሙከራዎችን ማስተናገድ የጀመረው ከ5ኛው ደቂቃ ጀምሮ ነው። በቅብብል ስህተት የተገኘውን ኳስ አማኑኤል ዮሐንስ ለሚኪያስ መኮንን አቀብሎት ወደ ግብ የተመታውን የሀዋሳው ግብ ጠባቂ ቤሊንጋ አምክኖበታል። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት ቡናዎች ከሦስት ደቂቃ በኋላም ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል በመጓዝ ሌላ ሙከራ ሰንዝረዋል።

ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው ጨዋታቸውን የቀጠሉት ሃዋሳ ከተማዎች የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ10ኛው ደቂቃ አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ አዲስዓለም ተስፋዬ በቀኝ መስመር አካባቢ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሯል።

በቀኝ መስመር በኩል ወደ ሀዋሳ የግብ ክልል ያመሩት ባለሜዳዎቹ ሚኪያስ ከመስመር አሻምቶት እንዳለ ደባልቄ በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ በቀየረው ኳስ መሪ ሆነዋል። በ19ኛው ደቂቃ ተክለማርያም ሻንቆ በሰራው ስህተት ግብ ለማስቆጠረ ተቃርበው የነበሩት ተጋባዦቹ ከደቂቃ በኋላ በቡሩክ በየነ አማካኝነት ሌላ ሙከራ አድርገው መክኖባቸዋል።

ከግብ ክልላቸው ጀምሮ ኳስ መስርተው ለመውጣት ሲጥሩ የነበሩት የአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ተጨዋቾች ራሳቸው ላይ አደጋን ሊጋብዙ በሚችል መልኩ የቅብብል ስህተቶችን ሲፈፅሙ ታይቷል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም ሀዋሳዎች በ25ኛው ደቂቃ ብሩክ በየነ በሞከረው ሙከራ የአቻነት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር። በጨዋታው በርከት ያሉ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን መፍጠራቸውን የቀጠሉት ቡናማዎቹ በ30ኛው ደቂቃ አህመድ ረሺድ እንዲሁም በ31ኛው ደቂቃ የመጀመሪያውን ግብ ባስቆጠረው እንዳለ አማካኝነት ሙከራ ሰንዝረዋል።

የአቻነት ግብ በመፈለግ የግብ ክልላቸውን ለቀው የወጡት ሀዋሳዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮባቸዋል። አማኑኤል የሀዋሳ አማካዮች የሰሩትን የኳስ ቅብብል ስህተት አቋርጦ ያገኘውን ኳስ በጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው አቤል ከበደ በማቀበል በአቤል አማካኝነት ማራኪ ጎል ተቆጥሯል። ለግቡ መቆጠር የሃዋሳው ግብ ጠባቂ ኳሱን ከአቤል ቀድሜ አገኛለው በሚል የፈጠረው የመዘናጋት ስህተት ለአቤል ምቹ አጋጣሚን ፈጥሮ አቤል ኳሷን በአየር ላይ (ቺፕ) አስቆጥሯል።

የግብ ልዩነቱ የሰፋባቸው ተጋባዦቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን አድርገዋል። ለአብነትም በ40ኛው ደቂቃ በረጅሙ የተመታን ኳስ ይተሻ ግዛው ለዳንኤል ደርቤ አቀብሎት ዳንኤል ወደ ግብ የሞከረው አስደንጋጭ ሙከራ ተጠቃሽ ነው። ጨዋታው የቀለላቸው ቡናዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ሌላ ጥሩ አጋጣሚ በእንዳለ አማካኝነት ፈጥረው ቤሊንጋ አምክኖባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት በባለሜዳዎቹ መሪነት ተጠናቋል።

የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮዋቸውን በግብ ለማጀብ ያለሙ የሚመስሉት ቡናዎች አቤል ለእንዳለ አመቻችቶ አቀብሎት እንዳለ ባመከነው ኳስ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ይህንን አጋማሽ የጀመሩት ሃዋሳዎች ሙከራዎችን ማድረግ ጀምረዋል። በ51ኛው ደቂቃም በጥሩ የኳስ ቅብብል ወደ ኢትዮጵያ ቡና የግብ ክልል በመድረስ ዳንኤል ደርቤ አስቆጪ አጋጣሚ አምክኗል። ከዚህ ሙከራ በተጨማሪ ቡድኑ በ56ኛው ደቂቃ በይተሻ ግዛው አማካኝነት ሌላ ሙከራ ሰንዝሯል።

በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ክፍት የጨዋታ እንቅስቃሴ በተስተዋለበት ጨዋታ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎች መስተናገድ ቀጥለዋል። በሃዋሳ በኩል ተቀይሮ የገባው ሄኖክ ደልቢ በ65ኛው ደቂቃ እንዲሁም በኢትዮጵያ ቡና በኩል በ66 እና 67ኛው ደቂቃ በአቤል እና በሚኪያስ አማካኝነት ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ ታይታል።

በጨዋታው ከተቻለ ሦስት ነጥብ ካልተቻለ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት የግብ ክልላቸውን ለቀው የወጡት ሀዋሳዎች በፈጠሩት የትኩረት ማነስ ችግር ሶስተኛ ግብ በእንዳለ አማካኝነት በ70ኛው ደቂቃ ተቆጥሮባቸዋል።

ጨዋታው ሙሉ ለሙሉ ከእጃቸው የወጣው ተጋባዦቹ የማስተዛዘኛ ጎል ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ ቀጥለዋል። በዚህም አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ መልሶበት ኳስ እና መረብ ሳይገናኝ ቀርቷል። በሚፈልጉት መልኩ ጨዋታውን እያከናወኑ የነበረው ቡናዎች ደግሞ አሥራት ቱንጆ ላይ ተቀይሮ የገባው ዩሃንስ ሶጌቦ በሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እንዳለ ደባልቄ ለራሱ ሦስተኛ ለቡድኑ ደግሞ አራተኛ ጎል በማስቆጠር መሪነታቸውን አስፍተዋል።

በዚኛው አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት ጥቃቶችን ለመፈፀም ሲሞክሩ የነበሩት ሃዋሳዎች የጨዋታውን የመጨረሻ ግብ በብሩክ በየነ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታው ተገባዷል።

ውጤቱን ተከትሎ የዓመቱ የመጀመርያ ድል ያስመዘገቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ደረጃቸውን ወደ ዘጠኝ ከፍ ሲያደርጉ ተጋባዦቹ ከነበሩበት አራተኛ ደረጃ ሸርተት በማለት አምስተኛ ደረጃ ላይ በግብ ልዩነት በመበለጥ ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ