ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ወደ አሸናፊነት የተመለሰበትን ወሳኝ የደርቢ ድል አስመዘገበ

በአምስተኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለቱ የሀዋሳ ከተማ ክለቦችን ያገናኘው የሀዋሳ ከተማ እና የሲዳማ ቡና የደርቢ ጨዋታ በቡናማዎቹ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ሀዋሳዎች በአራተኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከተረቱበት ስብስብ መካከል በአምስቱ ላይ ለውጥን አድርገው ገብተዋል። ቢሊንጌ ኢኖህ፣ ዳንኤል ደርቤ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ፣ ተስፋዬ መላኩ እና ሄኖክ አየለን በማሳረፍ በምትኩ ሀብቴ ከድር፣ ወንድማገኝ ማዕረግ፣ ፀጋአብ ዮሐንስ፣ ዘላለም ኢሳይያስ እና አክሊሉ ተፈራን በመጀመርያ አሰላለፍ ተጠቅመዋል። ሲዳማዎች በበኩላቸው በተመሳሳይ በመቐለ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስባቸው ጊት ጋትኮች እና ዮናታን ፍሰሀን በብርሀኑ አሻሞ እና አማኑኤል እንዳለ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡
ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በብቃት በመሩት ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ የደርቢነት መልክን ያላየንበት ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ ያሳየን ሲሆን አልፎ አልፎ ከሚታዩ ጥቂት አጋጣሚዎች ውጪ የረቡ ዕድሎችን ለመመልከት አልቻልንም።

ሀዋሳዎች አለልኝ አዘነ እና አጥቂው ብሩክ በየነ በግል ጥረታቸው ከሚፈጥሩት የማጥቃት አጋጣሚ ውጪ ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ያላሳዩ ሲሆን በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች በተለመደው የጨዋታ መንገዳቸው ከአማካዮች ተለጥጠው ወደሚጫወቱ የመስመር አጥቂዎች በሚጣሉ ኳሶች ለማጥቃት የሞከሩበት ነበር፡

ሲዳማ ቡናዎች የመጀመሪያዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ያደረጉት ፈጣን የረጃጅም ኳስ አማራጭ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። 12ኛው ደቂቃ በቀኝ በኩል ሀብታሙ ገዛኸኝ ፍጥነቱን ተጠቅሞ እየነዳ ወደ ግብ ለመሄድ ሲሞክር ከፊቱ ለነበረው ይገዙ ሰጥቶት ተጫዋቹ ኳሷ ስታመልጠው በቀኝ በኩል ለሲዳማ ቡና በዚህ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመርያ ተሰላፊ ሆኖ የገባው የመስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ ከማዕዘን ምቱ ጥቂት ፈቀቅ ካለ ቦታ ላይ በቀጥታ ወደ ግብ ያሻማት ኳስ የግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር የአቋቋም ስህተት ታክሎበት ከመረብ አርፋ ሲዳማን መሪ አድርጓል፡፡

ከግቧ በኃላ የመሀል ሜዳው እጅጉን ላልቶ ሲታይባቸው የነበሩት ሀይቆቹ ከቅጣት የተመለሰው ወንድማገኝ ማዕረግን ከተከላካይ አማካይ ቦታ ላይ ወደ ኋላ በመሳብ ተከላካይ ስፍራ ቦታ ሲመልሱት ዘላለም ኢሳይያስን በዮሐንስ ሱጌቦ በመቀየር በፍጥነት ክፍተቱን ለመድፈን ጥረት አድርገዋል፡፡ ሀዋሳዎች ምንም እንኳን በአማካይ ስፍራው ላይ የተጫዋች ለውጥ ማድረጋቸው እንቅስቃሴያቸውን ባያሻሽለውም ከርቀት በሚመቱ እና ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖን ባልፈተኑ ኳሶች እድሎች ፈጥረዋል፡ በተለይ ብርሀኑ በቀለ ሁለት ጊዜ ከሳጥን ውጪ መቶ የያዘበት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪ ወደ መልበሻ ቤት ሊያመሩ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩም በተመሳሳይ አለልኝ አዘነ ከቅጣት ምት፤ ዮሐንስ ሱጌቦ ከሳጥን ጠርዝ አክርረው በመምታት ሞክረው በቀላሉ የመሳይ ሲሳይ ሆነዋል፡፡

ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ በተወሰነ መልኩ ለዕይታ ሳቢ በነበረው የሁለተኛ አጋማሽ ክፍለ ጊዜ ሀዋሳዎች ደካማ እንቅስቃሴን ሲያሳይ የነበረው የተሻ ግዛውን በመስፍን ታፈሰ እንደመቀየራቸው ማጥቃት ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ቢባልም በተጠበቀው ልክ መሆን ግን አልቻሉም፡፡ በተለይ ከፊት ለፊታቸው ብቻ በማተኮር ግብ የማስቆጠር የሚል ዕቅድን ይዘው ቢገቡም ኃላቸውን በሚገባ መድፈን አለመቻላቸው ተጨማሪ ግብን እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ረጃጅም ተሻጋሪ ኳሶችን በሚጠቀሙት ሲዳማ ቡናዎች ለማስተናገድ ተገደዋል፡፡ በ55ኛው ደቂቃም ሀብታሙ ገዛኸኝ በተከላካዮች መሐል የተሻገረለትን ኳስ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር መውጣትን በመመልከት ሀብቴን ካለፈው በኃላ በግሩም አጨራረስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል፡፡

ከሲዳማ የድጋሚ ጎል በኋላ ከርቀት በብርሀኑ በቀለ በሚሞከሩ ኳሶች ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት ሀዋሳዎች በ59ኛው ደቂቃ ጎች አግኝተዋል። የሲዳማው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱኩ በሳጥን ውስጥ በያኦ ኦሊቨር ላይ በሰራው ጥፋት የተገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ በየነ መቶ ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ ሲመልሳት ራሱ ብሩክ የተመለሰችውን በድጋሚ አግኝቶ በማስቆጠር ሀዋሳን ወደ 2ለ1 አሸጋግሯል፡፡

ሆኖም አሁንም ከስህተት ያልፀዳው የሀዋሳ የተከላካይ ክፍል ተጨማሪ ግብን አስተናግዷል፡፡ 64ኛው ደቂቃ ላይ ከተመለደው አጨዋወቱ ቀዝቅዞ የነበረው የመሀል አማካዩ ዳዊት ተፈራ በረጅሙ በሀዋሳ የመሀል ተከላካዮች በአየር ላይ ያሳለፈውን ይገዙ ቦጋለ ደርሶባት የግብ ጠባቂው ሀብቴ ከድር መውጣትን በመመልከት በአናቱ ላይ አሳልፎ በማስቆጠር የሲዳማን የግብ መጠን ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል፡፡

ሀዋሳዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግብ ለማስቆጠር ቢታትሩም ወደ መከላከሉ የተሸጋገሩት ሲዳማዎች ተሳክቶላቸዋል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሀዋሳ ከተማ ደጋፊዎች በአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ድምፅ በማሰማት ተቃውሞን ሲያስተጋቡ አድምጠናል፡፡

* በ60ኛው ደቂቃ ሁለት የሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ሜዳ ላይ በወደቁበት ሰዓት የሲዳማ ቡናው የህክምና ባለሙያ አበባው በለጠ አንደኛውን ለማከም ሲገባ ሌላኛው በሜዳ ላይ ወድቆ ሳለ የሀዋሳው የህክምና ባለሙያ ሂርፓ ፋኖ ሮጦ በመግባት የሰጠው ህክምና ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ