የአሰልጣኞች አስተያየት | ስሑል ሽረ 1 – 1 አዳማ ከተማ

ትግራይ ስታዲየም ላይ የተደረገው የስሑል ሽረ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ 1-1 ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“በክፍተቶቻችን ላይ እየሰራን በቀጣይ የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን” ሳምሶን አየለ (ስሑል ሽረ)

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በሜዳችን እንደመጫወታችን ሦስት ነጥቦችን አስጠብቀን ለመውጣት ይዘነው የገባነው አጨዋወት ተጫዋቾቻችን ተግባራዊ አድርገውታል። በመጀመርያው አጋማሽ በመሃል ሜዳ የኳስ መቆራረጥ ነበር። እነሱ በቁጥር በርከት ብለው ስለነበር ትንሽ ችግሮች ነበሩ። በሁለተኛው አጋማሽ ግን ጥሩ ተንቀሳቅሰን ግብም አስቆጥረናል። በመጨረሻው ግን በግብ ጠባቅያችን የአቋቋም ስህተት ግብ ተቆጥሮብን አቻ ተለያይተናል። ይህ እግር ኳስ ነው ውጤቱን በፀጋ መቀበል ነው።

ስለ ቡድኑ ችግር

ባለፈው የነበው ችግር በተወሰነ መልኩ ተቀርፈዋል። በቀጣይ ቀናትም ሙሉ በሙሉ እንደሚቀረፍ ነው ስራ አስፈፃሚው ተወያይቶ መፍትሔ ያስቀመጠው። ይህ በቡድኑ ላይ ብዙም ተፅዕኖ የሚያመጣ አደለም። ብዙ ውይይት ተደርጎበት የተስተካከለ ነገር ነው።

ስለ ቡድኑ ወቅታዊ ውጤት

ሌሎች ክለቦች በነጥብ ብዙም አልራቁም። የጨዋታው መብዛት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ክለቦችስ ምን ይመስላሉ የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። በክፍተቶቻችን እየሰራን በቀጣይ የተሻለ ውጤት እናስመዘግባለን።

” አቻ በዝቶብናል፤ እሱ ነገር ማስወገድ የውዴታ ግዴታ ነው” አሸናፊ በቀለ

ስለ ጨዋታው

ጨዋታው ጥሩ ነበር። በመቐለ ስጫወት የቤቴ ያህል ነው የሚሰማኝ። ደጋፊው ጥሩ ለሚጫወት ስለሚደግፍ በነፃነት ነው የምትጫወተው። ደጋፊው ለተጋጣሚው የሚፈጥረው ነገር የለም። ሽረ አምና ከነበረው ዘንድሮ የተሻለ ነገር አለው። ከጊዮርጊስ አቻ ተለያይቶ ነው የመጣው፤ ጥሩ ጨዋታ ነው ያደረግነው። የሁለታችን አጨዋወት በማጥቃት የተመሰረተ ነበር። ሁለታችን በተመሳሳይ በርካታ ሙከራዎች አምክነናል። እነሱ አስተካክለው ወደ ጥሩ እንደሚመጡ አስባለው እኛም አስተካክለን እንመለሳለን።

ስለ ቀጣይ ጨዋታዎቻቸው

እስካሁን ድረስ አቻ በዝቶብናል፤ እሱን ነገር ማስወገድ የውዴታ ግዴታ ነው። በዚህ ጨዋታም አሸንፈን ለመውጣት ነበር የመጣነው። በዚህ ጨዋታ ሦስት የተለያዩ አጨዋወቶችን ነበር የሞከርነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ