ሪፖርት | አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም የተከናወነው የአዳማ ከተማ እና የሀዋሳ ከተማ ጨዋታ የባለ ሜዳዎቹ ብልጫ ታይቶበት 1-1 ተጠናቋል።

ባለሜዳዎቹ አዳማ ከተማዎች በ6ኛ ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ወደ መቐለ አምርተው የመጀመሪያ የሊጉ ሽንፈታቸውን ካስተናገዱበት ጨዋታ ጃኮ ፔንዜ፣ ሱሌይማን መሐመድ፣ አዲስ ህንፃ እና የኋላሸት ፍቃዱን በደረጄ ዓለሙ፣ መናፍ ዓወል፣ በላይ ዓባይነህ እና እስማኤል ሳንጋሪ ቀይረው ለጨዋታው ቀርበዋል። ተጋባዦቹ ሃዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው በሜዳቸው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ነጥብ ከተጋሩበት የመጀመርያ 11 አለልኝ አዘነ እና መስፍን ታፈሰን በወንድማገኝ ማዕረግ እና ብርሃኑ በቀለ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃቶችን በመሰንዘር ጨዋታውን የጀመሩት አዳማ ከተማዎች በ4ኛው ደቂቃ በአምበላቸው ምኞት ደበበ እንዲሁም በ8ኛው ደቂቃ በበረከት ደስታ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራ አድርገዋል። ከእነዚህ ሙከራዎች በተጨማሪ በ12ኛው ደቂቃ ከነዓን ማርክነህ ከመዓዘን የተተፋን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት ለጥቂት ወጥቶበታል። ኳስን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ትተው ሲጫወቱ የታዩት ሃዋሳ ከተማዎች መልሶ ማጥቃትን እንደ ቀዳሚ ግብ በባስቀመጥ ተንቀሳቅሰዋል። ነገር ግን ይህ የተጋጣሚያቸው ውሳኔ የጠቀማቸው አዳማዎች ኳስን በማንሸራሸር ግቦችን መፈለግ ቀጥለዋል።

ጨዋታው ቀጥሎም አዳማዎች በ14ኛው ደቂቃ እጅግ ለግብነት የተቃረበ እድል አምልጧቸዋል። በዚህ ደቂቃ ዳዋ ከተከላካዮች ጀርባ የተሰነጠቀለትን ኳስ ተጠቅሞ ግብ ለማስቆጠር ሲሞክር ግብ ጠባቂው ቢሊንጋ ኢኖህ እራሱን ለአደጋ አጋልጦ አክሽፎበታል። በጨዋታው ከፍተኛ የበላይነት የወሰዱት ባለሜዳዎቹ ከመስመር የሚነሱ ጥቃቶችን እንደ አማራጭ በመውሰድ ወደ ሃዋሳ የግብ ክልል ደርሰዋል። በ23ኛው ደቂቃም በጉዳት ተቀይሮ የወጣው ዳዋን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ቡልቻ ሹራ ከበረከት የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ጥሯል።

ጨዋታው የከበዳቸው የሚመስሉት ተጋባዦቹ ከ25ኛው ደቂቃ በኋላ ረጃጅም ኳሶችን መጠቀም ምርጫቸው አድርገዋል። በዚህ አጨዋወትም በ29ኛው ደቂቃ ቢሊንጋ ኢኖህን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሀብቴ ከድር ረጅም ኳስ አሻማለሁ ብሎ በሰራው ጥፋት ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። በዚህ ደቂቃ በግብ ጠባቂው ስህተት የደረሰውን ኳስ ከነዓን በቀጥታ ወደ ግብ መትቶት ላውረንስ ላርቴ እንደምንም በግንባሩ አውጥቶበታል።

እስከ መጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ደቂቃ ድረስ ምንም የግብ ማግባት ሙከራ አዳማዎች ላይ ያልሰነዘሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ41ኛው ደቂቃ የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በራሳቸው በኩል አድርገዋል። በዚህ ደቂቃ የተገኘን የመዓዘን ምት ያኦ ኦሊቨር አሻምቶት ግብ ጠባቂው ደረጄ ሲተፋውን ጥሩ ኳስ ያገኘው ተስፋዬ መላኩ ተግብጦ ግሩም ሙከራ አድርጎ መክኖበታል።

የልፋታቸውን ፍሬ ማየት ያልቻሉት አዳማዎች የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ሱሌማን ሰሚድ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የሃዋሳ አምበል ዳንኤል ደልቢ በእጁ በመንካቱ የእለቱ ዳኛ የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው በረከት ደስታ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑ እንዲመራ አስችሏል። የመጀመሪያ አጋማሽም በባለሜዳዎቹ 1-0 መሪነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው አንድ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ጥረቶችን በሁለተኛው አጋማሽ የጀመሩት ሃዋሳዎች ጠንካራውን የአዳማ የተከላካይ መስመር ማስከፈት ተስኗቸው ታይቷል። በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የመጫወቻ ቦታን ያገኙት አዳማዎች መሪነታቸውን ከፍ ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል። አጋማሹ በተጀመረ በ8 ደቂቃዎች ውስጥም በበላይ፣ ከነዓን እና ቡልቻ አማካኝነት ግቦችን ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በተለይ ሃዋሳዎች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ በሚሞክሩበትት ጊዜ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጥቃቶችን ሰንዝረዋል። በዚህ የጨዋታ እንቅስቃሴም ሳንጋሪ በ56ኛው፣ በረከት በ65ኛው እንዲሁም ሱሌማን በ66ኛው ደቂቃ ወደ ግብ የሞከሯቸው አጋጣሚዎች ሃዋሳዎችን እጅግ የፈተኑ ነበሩ።

የአጥቂ ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾችን በዚህኛው አጋማሽ ለውጠው ወደ ሜዳ የገቡት ሃዋሳዎች በ74ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥረዋል። በዚህ ደቂቃ ወደ ግብ በርከት ብሎ ያመራው ቡድኑ ኳስ በእጅ በመነካቱ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝቷል። የፍፁም ቅጣት ምቱንም ሄኖክ ደልቢ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። ጨዋታውን በሚገባ መቆጣጠር ሳይችሉ ግብ ያስተናገዱት አዳማዎች እንደገና ግብ ለማስቆጠር እና ወደ መሪነት ለመመለስ ጥረቶችን ማድረግ ቀጥለዋል።

አዳማዎች ጨዋታው ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ሲቀረውም ቡልቻ እና ቴዎድሮስ ከርቀት በመቱት ኳስ ወደ ግብ ቀርቦ ነበር። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆም በተጨመሩት 5 ደቂቃዎች ውስጥም ቡድኑ 5 እጅግ ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎችን ሰንዝሯል። በእነዚህ ደቂቃዎች ቡልቻ እና ዱላ ሁለት ጊዜ እንዲሁም ምኞት አንድ ግዜ ወደ ግብ የመቱትን አደገኛ ኳሶች ሀብቴ ከድር በሚገርም ብቃት አምክኖባቸዋል።

ጨዋታውም ተጨማሪ ግብ ሳይስተናገድበት 1-1 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ አዳማ እና ሀዋሳ ከተማ ከነበሩበት 11ኛ እና 9ኛ ደረጃ አንድ ደረጃዎችን ተንሸራተው 10ኛ እና 12ኛ ደረጃ ላይ (በቅደም ተከተላቸው) ተቀምጠዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ