“በእኔ ላይ እምነት ጥለው ስላሰለፉኝ አሰልጣኙንም የምወደው ክለቤንም ማሳፈር አልፈልግም” ዓለምብርሀን ይግዛው

በዐፄዎቹ ደጋፊዎች ዘንድ “ትንሹ ልዑል” በመባል የሚጠራው ወጣቱ እና ተስፈኛው ዓለምብርሃን ይግዛው ስለ እግርኳስ ህይወቱ ይናገራል።

በ2011 ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ብቅ ካሉ ወጣት ተጫዋቾች አንዱ የሆነው ዓለምብርሃን ይግዛው ዐምና በአሰልጣኝ በውበቱ አባተ አማካኝነት በቢጫ ታሴራ ዋናውን ቡድን ከተቀላቀለ ወዲህ ለፋሲል ከነማ በመጫወት ላይ የሚገኝ ሲሆን በተለያዩ ሚናዎች ተሰልፎ እየተጫወተም ይገኛል። በአማካይ እና በመስመር እንዲሁም የመሀል አጥቂ ሚና ተሰጦት ከዚህ ቀደም ሲጫወት የተመለከትነው ይህ ወጣት በ2011 በወሳኙ የዋንጫ ፉክክር ወቅት በሱ ብቸኛ ጎል መቐለ 70 እንደርታን ማሸነፋቸው የሚጠቀስ አጋጣሚ ነው።

ሶከር ኢትዮጵያ ዘንድሮ በጉዳት እየታመሰ በሚገኘው ፋሲል በአሰልጣኙ በተለየ ቦታ ተሰልፎ እየተጫወተ ከሚገኘው ወጣት ተጫዋች ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ስለ አስተዳደግህ እና ስላሳለፍክባቸው የታዳጊ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ከቤተሰብ ስለሚደረግልህ ድጋፍ ግለፅልን?

እግርኳስን የጀመርኩት በጎንደር ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ መኮንን ገብሬ በሚያሰለጥነው ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ውስጥ ለሁለት ዓመት ሰርቻለሁ። ጥሩ ጊዜም ነው ያሳለፍኩት። ከዛ በመቀጠል ወደ ፋሲል ከነማ ተስፋ ቡድን ነበር የተቀላቀልኩት። በተስፋ ቡድን ለአንድ ዓመት ብቻ ቆይቼ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን አደኩ። ባደግኩበት ዓመትም በርካታ ዕድሎች እየተሰጡኝ ጥሩ የውድድር ግዜን አሳልፌያለሁ። እናም የእግርኳስ ጅማሬዬ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሮጀክት ነው። በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኝ መኮንን’ን ማመስገን እፈልጋለሁ። ቤተሰቦቼም ይረዱኝ ነበር። ከፕሮጀክት ጀምሬ ስሰራ የትራንስፖርት አይከለክሉኝም። ትጥቅም ያሟሉልኝ ነበር። ይበልጥ ደግሞ አባቴ በጣም ይረዳኝ ነበር። ቤተሰቦቼ በደንብ ነው ድጋፍ ያደረጉልኝ፤ አባቴ ደግሞ በተለየ ሁኔታ። ለሱ ትልቅ ቦታ አለኝ ።

እግርኳስ ተጫዋች እንድትሆን ተፅእኖ ያለው ሰው ወይም እዚህ ደረጃ እንድደርስ ትልቅ ነገር አደረገልኝ የምትለው ሰው አለ?

ምንም ጥያቄ የለውም ውበቱ አባተ! በተስፋ ቡድን ውድድር በግርማይ እየሰለጠንን በነበረበት ዓመት በጣም ጥሩ ቡድንን ነበረን። (አሰልጣኝ ግርማይ ኪሮስንም በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ) እና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሀዋሳ ላይ ብሔራዊ ሊግ ለመግባት በምንጫወትበት ወቅት ሜዳ ተገኝቶ ያኔ ነበር ያሳደገን። 4 ልጆችን አሳድጎ ባደግንበት ዓመትም በርካታ እድሎችን ሲሰጠኝ ነበር። አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለታዳጊ ያለው ነገር በጣም ጥሩ ነው። ለአንተ አቅም ጉልበት ነው የሚሆንህ፤ በጣም ያበረታታኝ ነበር፤ ብዙ ነገሮችን አስተካክሎኛል። የሱ ጥረት ነው የተሻለ ቦታ እንድትደርስ ያደረገኝ። ኃላፊነት ወስዶ ነው የሚያስገባህ፤ በጣም ደስ ብሎህ እንድትጫወት ነው የሚያደርግህ፤ እንድትጨናነቅ አያደርግህም። ያ ነገር ደግሞ እንደኔ ከተስፋ ቡድን ለመጡ ታዳጊዎች በጣም ጠቃሚ ነው። እና በኔ ህይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ አለው።

ስለ አዲሱ ቦታህ እና ስለተሰጠህ ግዳጅ ምን ትላልህ? እንዲሁም ወደ ቦታህ ስትመለስ ለሚጠበቅህ ፈተና ምንያል ዝግጁ ነህ?

ቦታው እኔ የምጫወትበት ተፈጥሯዊ ቦታ ባይሆንም አሰልጣኙ አምኖብኝ ግብ ጠባቂም ሁን ተብዬ ብጠየቅ ከመግባት ወደኋላ አልልም። ቦታው ላይ ጠንክሬ በመስራት ቦታው የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ለማሟላት ነው የምጥረው። እናም እስከ መጨረሻው ድረስ ያለኝን ነገር ሁሉ ሰጥቼ ነው የምጫወተው። አሰልጣኙ ከተፈጠረው ችግር አንፃር በርካታ ተጫዋቾች ቢኖሩም ቡድኑ ውስጥ በእኔ ላይ እምነት ጥሎ ስላስገባኝ አሰልጣኙንም የምወደው ክለቤንም ማሳፈር አልፈልግም። በኔ ቦታ ላይ የሚጫወቱ በርካታ የማከብራቸው ሲኒየሮች አሉ፤ ወደ ቦታዬ ስመለስ አሁን ካለሁበት በተሻለ ጠንክሬ በመሥራት ከእነሱ ጋር ተፎካክሬ በሚሰጥኝ እድል ከአምናው በተሸለ ግቦች ለማስቆጠር እንዲሁም ከቡድን አጋሮቼ ጋር ጥሩ በመንቀሳቀስ የተሻለ ስኬት ለማምጣት ነው ነው የምፈልገው።

በመስመር ተከላካይነት እንድትገባ ስትደረግ ቦታው ይከብደኛል ብለህ አልሰጋህም? በተለይ የማጥቃት ባህርይ ያለህ በመሆንህ በመከላከሉ ላይ እቸገራለሁ ብለህ አላሰብክም?

ከፊት ወደ ኋላ መመለስ ይከብዳል፤ ቢሆንም ግን የተሰጠኝን ግዳጅ በቶሎ ተላምጄዋለሁ። አሰልጣኙ ልምምድ ላይ በቦታው ብቁ እንድሆን የተወሰኑ ነገሮችን አሰርቶኛል። የመከላከል ሥራ ትንሽ ከበድ ይላል። ስለዚህ በጥንቃቄ የሚሰራ ሥራ ነው። እኔ የማጥቃት ባህሪ ስላለኝ ትንሽ ተፅዕኖ አለው። ግን እንደ መስመር ተጫዋችነቴ ወደ ኋላ ተመልሼ የመስመር ተከላካዩን የማገዝ ግዴታ ስላለብኝ፤ መከላከል አንድ የመስመር እንዲሁም የመሐል ተጫዋቾች ማሟላት ያለባቸው ነገርም ስለሆነ መከላከሉ ላይ እቸገራለሁ የሚለው ነገር አላሳሰበኝም ነበር።

የወደፊት እቅድህ ምንድነው?

የመጀመሪያው እቅዴ ከፋሲል ከነማ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማንሳት ነው። በባለፈው ዓመት ጫፍ ደርሰን ነበር፤ አልተሳካም። ከፈጣሪ ጋር ለቀጣይ ትልቁ እቅዴ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ማንሳት ነው። ከዛ በመቀጠል እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ሀገሬን በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ማገልገል እፈልጋለሁ፤ ከሀገሬም ጋር ስኬታማ መሆን እፈልጋለሁ። ሌላው ከሀገር ወጥቼ መጫወቱን እፈልገዋለሁ.. የወደፊት እቅዴ እነዚህ ናቸው ።

ስለ ፋሲል ከነማ ደጋፊዎች እና ስለ ሰጡህ ስም (ትንሹ ልዑል) ምን ትላለህ ?

በመጀመሪያ ስለሰጡኝ ስም በጣም አመሰግናለሁ፤ ምን እንደምል አላውቅም። ፋሲል ከነማ ለኔ እግርኳስ በትልቅ ደረጃ መጫወት የጀመርኩት ነው። ከኔ ብዙ ነገር ይጠበቃል፤ እኔም የሚጠበቅብኝን ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ። ለዚህ ደጋፊ ክለብ ምንም ነገር አደርጋለሁ፤ ደግሞም ይገባቸዋል። ወርቅ የሆነ ደጋፊ ነው ያለን። ለማሊያቸው የሚሞቱ ናቸው፤ ቃላት የለኝም። በጣም ነው የምወዳቸው እና ማከብራቸው። ከእነርሱ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከፍ አድርገን እንደምንስም ተስፋ አለኝ።

አብረውህ ስለሚጫወቱ እንዲሁም ስለሌሎች ክለቦች ወጣት ተጫዋቾች የምታጋራው ነገር አለ?

ወጣት ተጫዋቾች ፋሲል ከነማ ላይም ሆነ አብዛኞቹ የሀገራችን ክለቦች እድል እየተሰጣቸው አይደለም። ለምሳሌ ከእኔ ጋር 4 ተጫዋቾች ነበር ያደግነው። እነሱም ዕድል የማግኘት እና ያለማግኘት ጉዳይ ነው እንጂ አቅም አላቸው። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ክለቡ ውስጥ ያሉት ታዳጊዎች ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ክለቦች እድል ቢሰጡ ጥሩ ነው። እንደነገርኩህ በመጀመሪያ እድል መሰጠት ነው የሚያስፈልጋቸው፤ ሁሉም ነገር ዕድል ካገኙ በኋላ ከጨዋታ ጨዋታ በልምድ ይስተካከላል ብዬ አምናለሁ ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የምታደንቀው ወይም እንደ አርዓያ የምታየው ተጫዋች ማን ነው?

ኢትዮጵያ ውስጥ የማደንቀው ተጫዋች የሲዳማ ቡናው አንበል አዲስ ግደይ ነው። ከሀገር ውስጥ በጣም የሚመቸኝ እና የማደንቀው ተጫዋች እሱ ነው። በተለይ ጎንደር መጥቶ ሲጫወት ማየት በጣም ያስደስተኛል። እናም ለኔ አርያዬ አዲስ ግደይ ነው ።


© ሶከር ኢትዮጵያ