የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 1ኛ ዙር ክለቦች ዳሰሳ – ሰበታ ከተማ

የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ዙር በሳምንቱ መጀመርያ መጠናቀቁን ተከትሎ ክለቦች በተናጥል መዳሰስ እንጀምራለን። በዚህኛው ዳሰሳችንም የመጀመሪያውን ዙር በ18 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ሰበታ ከተማን የአጋማሽ ጉዞ ተመልክተናል።

የመጀመሪያ ዙር ጉዞ

በ2011 የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ በአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየተመሩ አስደናቂ የውድድር ዘመንን በማሳለፍ አንድም ጨዋታ ሳይሸነፉ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ፕሪምየር ሊግ ተካፋይ መሆናቸውን ያረጋገጡት ሰበታ ከተማዎች በክረምቱ በርካታ በሊጉ የመጫወት የካበተ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾችን ጨምሮ በሊጉ ዐምና በፋሲል ከነማ ምን መስራት እንደሚችሉ ያሳዩት ውበቱ አባተን በአሰልጣኝነት በመቅጠር ነበር ወደ ውድድር የገቡት።

ቡድኑ ከውድድሩ መጀመር ቀናት በፊት ሊጉን በሚመራው ዐቢይ ኮሚቴ ሜዳው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎችን ለማከናወን ብቁ መሆኑ ስላልታመነበት ውድድሮችን በአማራጭነት ያቀረበው የአዲስ አበባ ስታዲየምን እንደ ሜዳው እየተጠቀመ ይገኛል። ገና ከጅምሮ ተቃውሞ ያልተለየው ቡድኑ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተከታታይ የደረሰበት ሽንፈት የቡድኑ ደጋፊዎቹ እንደ አዲስ በውበቱ አባተ የተዋቀረውን ቡድን ውጤታማነት እንዲጠራረጠሩ ያደረገ ነበር። ነገር ግን በተከታታይ ወልቂጤን የተረቱበት እንዲሁም ከጠንካራው ፋሲል ከነማ ጋር በሁለት የጎል ልዩነት ከመመራት ተነስተው በመጨረሻ ደቂቃዎች 3-3 የተለያዩበት እና በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ውጤት ማስመዝገባቸው በተወሰነ ደረጃ ቡድኑን እፎይ ቢያሰኙም አሁንም ግን የተወሰኑ የክለቡ ደጋፊዎች በክለባቸው እንቅስቃሴ ደስተኛ ስላለመሆናቸው ይስተዋላል።

ወጣ ገባ የሚል የውድድር ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ቡድኑ በተከታታይ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ እጅጉን ሲቸገር ይስተዋላል። በአንድ ጨዋታ ላይ ጥሩ ተስፋን የሚሰጥ እንቅስቃሴ አሳይቶ ተስፋ ሲደረግበት በቀጣዩ ጨዋታ ተስፋ ሲጣልበት በተቃራኒው የሚገኝ ቡድን ስለመሆኑ የመጀመሪያ ዙር ጉዞው ይመሰክራል።

ቡድኑ በመጨረሻ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ውስጥ በሦስቱ ተሸንፎ አንድ ሲያሸንፍ በሌላኛው ደግሞ አቻ ለመለመያየት ችሏል። ከተወሰኑ ደጋፊዎች ቡድኑ በጨዋታዎች ነጥብ ባጣ ቁጥር ተቃውሞ የሚያስተናግደው ቡድኑ ዙሩን ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ርቆ በ18 ነጥቦች በ12 ደረጃ ላይ ማጠናቀቅ ችሏል።

የውጤት ንፅፅር ከ2011 ጋር

ቡድኑ ባለፈው ዓመት በከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ የነበረ በመሆኑ ንፅፅር ለማቅረብ አስቸጋሪ ነው።

የቡድኑ አቀራረብ

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሊጉ ውስጥ በማሰልጠን ላይ ካሉ አሰልጣኞች ውስጥ በግልፅ የሚታይ የጨዋታ መንገድን ለመተግበር ከሚሞክሩ ውስን አሰልጣኞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ መሆናቸው ባያጠያይቅም በዘንድሮው ሰበታ ከተማ ላይ ግን የሚታወቁበትን የኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተውን ቡድን በሰበታ ለማሳየት እየተቸሩ ይገኛል።

በእርግጥ የቡድኑ ተጫዋቾች በአመዛኙ ለቡድኑ አዲስ በመሆናቸው እና በተደጋጋሚ የተጫዋቾች ጉዳት የመጀመርያ ተመራጭ ተጫዋቾቻቸውን ያላገኙባቸው አጋጣሚዎች በርከት ቢሉም ቡድኑ ፍፁም በተራራቁ ሁለት የጨዋታ መንገዶች ወደ ጨዋታዎች ሲቀርብ ይስተዋላል።

ቡድኑ በአመዛኙ በ4-3-3 መነሻ ቅርፅ እንደ ተጋጣሚ ሁኔታ ሲከላከሉ ወደ 3-4-3/4-1-4-1/ 4-5-1 የሚቀያየር የመከላከል አቀራረብ ሲኖረው ቡድኑ በተወሰኑ የጨዋታ ቅፅበቶች ኳስን ለመመስረት በአመዛኙ የጨዋታ ሒደቶች ደግሞ በተለይ ከዳንኤል አጃይ የሚነሱ ረጃጅም ኳሶች በመጠቀም አደጋ ለመፍጠር የሚሞክር ቡድን ሆኖ ተመልክተነዋል።

ቡድኑ በፊት መስመር በፊት አጥቂነት ተቀዳሚ ምርጫቸው ከሆነው ፍፁም ገ/ማርያም ቀኝ እና ግራ ለተለያዩ አጨዋወቶች ኳስን ለማሻማትም ሆነ ሰብሮ ለመግባት የተመቹት እንደ ተጋጣሚ ሁኔታ በመቀያየር ባኑ ዲያዋራ፣ ሲይላ ዓሊ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ ናትናኤል ጋንቹላ፣ ፍርዳወቅ ሲሳይ እና ሳሙኤል ታየን በመቀያየር ሲጠቀም ተስተውሏል።

በአማካይ ስፍራ ቡድኑ ያለምንም ተፈጥሯዊ የተከላካይ አማካይ (መስዑድ መሀመድ አልያም ዳዊት እስጢፋኖስ) ቢጠቀሙም ከጎናቸው ደግሞ ታደለ መንገሻ እና ከመስዑድ /ዳዊት/ አንዱ በ8 ቁጥር ሚና ይበልጥ የማጥቃቱ ኃላፊነት ላይ ሲሳተፉ ይስተዋላል።

ተከላካይ መስመሩ በተጫዋቾች ጉዳትና በተለያዩ ምክንያቶች ያልተረጋጋና ብዙ ክፍተቶች የነበሩት እንደነበር ለማየት ተችሏል። ውድድር ዘመኑ ሲጀመር በመስመር ተከላካይነት የጀመሩት ፍርዳወቅ ሲሳይ እና ጌቱ ኃይለማርያም በሒደት ወደ ተጠባባቂ ወንበር አምርተው በምትካቸው ኃይለሚካኤል አደፍርስ እና ኢብራሒም ከድር (ያለ ተፈጥሮአዊ ቦታው) በዚህኛው ስፍራ ተሰልፈው በመጫወት የመጀመሪያ ዙሩን አጠናቀዋል። ከሁለቱ የመስመር ተከላካዮች ኢብራሂም ከድር በማጥቃቱ ይበልጥ የሚሳተፍ ሲሆን ኃይለሚካኤል ግን ይበልጥ ጠንቀቅ ብሎ በመከላከሉ ላይ የጎላ አበርክቶ ሲኖረው ተመልክተናል።

በተጫዋቾች ጉዳት የተነሳ የጠበበ የመሀል ተከላካይ አማራጭ የነበረው ቡድኑ 8ኛ ሳምንት ላይ ወሳኝ ተከላካያቸው አንተነህ ተስፋዬ ከጉዳት መመለስ የተወሰነ ፋታ ያገኘ ቢመስልም የቡድኑ የመከላከል መስመር በመከላከል አደረጃጀትም ሆነ ለማጥቃት ኳስ ለማስጀመር በሚደረጉ የምስረታ ሙከራዎች በርካታ ስህተቶች የሚሰራ እና በቀላሉ ግቦችን የሚያስተናግድ ሆኖ ተመልክተናል።

ጠንካራ ጎን

ቡድኑ በተለያዩ የጨዋታ አቀራረቦች መቅረቡ ተገማች እንዳይሆንና ለተጋጣሚዎች ለግምት አስቸጋሪ መሆኑ በመጀመሪያው ዙር የቡድኑ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ሲሆን ቡድኑ ምንም እንኳን ሜዳው የማሻሻያ ስራዎች እየተከወኑለት እንደመገኘቱ ተለዋጭ ሜዳው በሆነው በአዲስ አበባ ስታዲየም ባደረጋቸው ጨዋታዎች ላይ መልካም ውጤትን ማስመዝገብ ችሏል። አጠቃላይ ቡድኑ በአጋማሹ ይዞ ካጠናቀቀው አስራ ስምንት ነጥቦች ውስጥ አስራ አምስቱ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተገኙ ናቸው። በዚህም አዲስ አበባ ላይ ካደረጓቸው ጨዋታዎች በሊጉ መጀመሪያ በወልዋሎ ከደረሰበት ሽንፈት ውጭ በአራት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።

ደካማ ጎኖች

እንደ አብዛኛዎቹ የሊጉ ቡድኖች ከሜዳቸው ውጭ ለማሸነፍ በእጅጉ የሚቸገረው ቡድኑ ከሜዳው ውጭ በአራተኛው ሳምንት ወልቂጤን ከረታበት ጨዋታ ውጭ ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች በአንዱም ጨዋታ ነጥብ ማስመዝገብ ሳይችል ቀርተዋል። በአመዛኙ ቡድኑ በሁለተኛው ዙር በርከት ያሉ የሜዳ ጨዋታዎች ከፊቱ እንደመጋረጣቸው ከሜዳው ውጭ ነጥብ ማስመዝገብ ካልቻለ በሊጉ ከስጋት የፀዳ የውድድር ዓመት የማሳለፉ ነገር አደጋ ውስጥ የመግባት እድሉ በጣም የሰፋ ነው።

በመከላከሉ ረገድ በርካታ ስህተቶችን የሚሰራው ቡድኑ በተለይ አሰልጣኙ በዋነኝነት በሚታወቁበት የኳስ ምስረታ ሒደት ላይ እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ኳስ ጋር እምብዛም ምቾት የሚሰማቸው ባለመሆኑ በአነስተኛ ጫና ውስጥ ሲገቡ የሚሰሯቸው የማቀበል ስህተቶች እንዲሁም ፊታቸው የሚገኙ ክፍት ሜዳዎች ለመጠቀም ከመሞከር ይልቅ ቀጥተኛ ኳሶችን ወደ ፊት ለመጣል መታተራቸው የቡድኑን የኳስ ምስረታ ሂደት በችግሮች የታጀበ እንዲሆን አስችሏል።

ሌላኛው የቡድኑ የመከላከል ችግር ቡድኑ በሜዳኛው የላይኛው ክፍል ተጋጣሚን ጫና ውስጥ ለመክተት እንደማሰቡ ተከላካዮቹ በተሻለ ለመሐል ሜዳ ቀርበው ለመከላከል በሚሞክሩበት ወቅት በተለየ ሁለቱ የመሀል ተከላካዮች የጊዜ አጠባበቅና ከጀርባ የሚገኘውን ጥልቀት ለማጥቃት የሚሞክሩ ቡድኖች ተጫዋቾች ወደ ኋላ ተመልሶ በማቋረጥ ረገድ ክፍተቶች ይስተዋላሉ።

በመከላከሉ ረገድ ችግሮች የሚስተዋልበት ቡድኑ ዓመቱን ሲጀምር በቀኝ መስመሮ ተከላካይነት ጨዋታዎችን ይጀምር የነበረው ጌቱ ኃይለማርያም ሆነ ያለ ቦታው በሽግሽግ የመጣው ኢብራሂም ከድር በሚሰለፍበትም ወቅት ቡድኑ በቀኝ መስመር በኩል ያለው ሚዛናዊ ያልሆነ እንቅስቃሴ በቀኝ ወገን ተጋላጭነቱ ከፍ ያለ እንዲሆን አስገድዷል።

ቡድኑ በሜዳኛው የላይኛው ክፍል ኳስን መልሶ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት በተቃራኒ የሜዳ ክፍል በቁጥር በርከት ብለው ቢገቡም ኳስን መልሶ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ቅንጅት የሚጎድለው በመሆኑ ተጋጣሚ ኳሶቹን በቀላሉ ከእነሱ የጫና ወጥመድ እየወጣ ወደ ማጥቃት ሽግግር ሲገቡ ይስተዋላል።

ቡድኑ በመሀል ሜዳ ላይ በርከት ያሉ በሊጉ ደረጃ በፈጠራ ብቃታቸው ከፍ ያለ ደረጃ ይገኛሉ ተብሎ የሚቀመጡ በርከት ያሉ ተጫዋቾች በቡድኑ ውስጥ ቢገኙም ከመሀል ለመሀል ከሚነሱ ኳሶች ቡድኑ ብዙም የጠሩ የግብ እድሎችን ሲፈጥር አይስተዋልም። ለዚህም በቀጣይ ጊዜ ቡድኑ የተሻለ ውጤትን ለማስመዝገብ የእነዚህን ተጫዋቾች አቅም በይበልጥ ለመጠቀም መሞከር ይገባል ፤ ይህም የቡድኑን አጥቂዎች በቂ የአቅርቦት መስመር አለመኖሩ ቡድኑ በቂ ግቦችን ለማምረት እየተቸገሩ ይገኛል።

በሁለተኛ ዙር ምን ይጠበቃል?

ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ እንደማደጉ በዚህኛው የውድድር ዘመን በሊጉ መቆየት ከተቻለው ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ እንደመሆኑ ቢታመንም በሊጉ የካበተ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች ቡድኑ እንደመገንባቱ የተሻለ ውጤትን ማስመዝገብ ይጠበቅበታል።

ቡድኑ በመከላከሉ ረገድ ያሉበትን ችግሮች ከፊት ላይ የሚታዩበትን ችግሮች መቅረፍ ከተቻለ ቡድኑ ካለው የስብስብ ጥራት አንፃር በሊጉ የተሻለ ደረጃን ይዞ የማጠናቀቅ እድሉ የሰፋ ነው።

ክፍተቶች ለመድፈን በማሰብ ግዙፉን ናይጄሪያዊ አጥቂ ፒተር ኑዋዲኬን እንዳስፈረሙ የተነገረው ሰበታ ፊት መስመር ላይ ከፍፁም ገ/ማርያም በተጨማሪ ሌላ የማጥቃት አማራጭ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይገመታል።

የ1ኛ ዙር ኮከብ ተጫዋች

ዳንኤል አጃይ – በክረምቱ ከጅማ አባ ጅፋር የተቀላቀለው ግብ ጠባቂው ለቡድኑ ወሳኝ ኳሶችን ከማዳን በዘለለ ወደ መሐል ሜዳ ከተጠጋው የተከላካይ መስመር ጀርባ የሚጣሉ ኳሶችን በማፅዳት እና እጅግ የተሳካ በሆኑት ረጃጅም ኳሶች ለቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ አይነተኛ ሚናን ተወጥቷል።

ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች

ኃይለሚካኤል አደፍርስ – በግራ የመስመር ተከላካይ ስፍራ የሚጫወተውና ለሊጉ አዲስ የሆነው ኃይለሚካኤል እርጋታውና ጥንቃቄው በጣም የተለየ ያደርገዋል። ተፈጥሯዊ የግራ እግር የግራ መስመር ተከላካካዮች እጥረት ባለበት ፕሪምየር ሊግ ውስጥ የተገኘው ይህ ባለ አስደናቂ ክህሎት የመስመር ተከላካይ በቀጣይ ራሱን እያሻሻለ ከመጣ ለብሔራዊ ቡድንም ጥሩ ግብዓት የመሆን አቅም ይኖረዋል።

© ሶከር ኢትዮጵያ