ድሬዳዋ ከተማ የአራት ተጫዋቾችን ውል አደሰ

ድሬዳዋ ከተማ የምንተስኖት የግሌ፣ ቢኒያም ጥዑመልሳን፣ ሙህዲን ሙሳ እና ያሲን ጀማልን ውል አራዝሟል፡፡

ዛሬ ውል ካራዘሙት መካከል የሆነው ሙህዲን ሙሳ ከተስፋ ቡድን አድጎ ሲጫወት የቆየ ሲሆን በከፍተኛ ሊግ ለሀዲያ ሆሳዕና ተጫውቶ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወደ ድሬዳዋ በመመለስ ግቦችን በማስቆጠር ድንቅ ጊዜያን ሲያሳልፍ ታይቷል፡፡

ሌላኛው ውሉን ያራዘመው የመስመር አጥቂ ቢኒያም ጥዑመልሳን ነው፡፡ የቀድሞው የናሽናል ሲሚንት ተጫዋች ከ2010 ጀምሮ ለድሬዳዋ እየተጫወተ የሚገኝ ሲሆን በተለይ ዘንድሮ ሊጉ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ጥሩ ጊዜ አሳልፏል።

ያሲን ጀማል በአሰልጣኝ ስምኦን አባይ አማካኝነት ወደ ክለቡ ከመጣ በኃላ በተለይ ዘንድሮ በመስመር ተከላካይነት ክለቡን በወጥነት ያገለገለ ሲሆን ይህን ተከትሎም በክለቡ ለመቆየት ተስማምቷል፡፡

ግብ ጠባቂው ምንተስኖት የግሌ ሌላው ያራዘመ ተጫዋች ነው፡፡ ከሳምሶን አሰፋን እና ፍሬው ጌታሁን በመቀጠል የቡድኑ ሦስተኛ ግብ ጠባቂ ቢሆንም ለቀጣይ ዓመታት ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ ክለቡ ውሉን ተራዝሞለታል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ