በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተደረገ

ትናንት ምሽት በእግርኳሱ ያሉ አካላትን ያሳተፈ “ያለፉትን እናመስግን፤ ቀጣዩን የኢትዮጵያን ኳስ እንዴት እናሳድግ” በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ የቪዲዮ ውይይት ተከናውኗል፡፡

ውይይቱን በዋናነት ያዘጋጁት አሜሪካ የሚገኘው መዝሙረዳዊት መኩሪያ የስፖርት ኤጀንት እና አማካሪ እንዲሁም በስፖርት ዞን ትብብር ነበር።

ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው በዚህ ውይይት ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ፣ የፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሰውነት ቢሻው፣ ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱ በዚህ ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩ አካላት ናቸው፡፡ በተጨማሪም የፕሮግራሙ አዘጋጆች መዝሙረዳዊት መኩሪያ እና ጋዜጠኛ ሰዒድ ኪያርን ጨምሮ ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ እና ሶከር ኢትዮጵያም በተጋባዥነት በዚህ ዓለምአቀፍ ውይይት ላይ ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡የሀገራችን አሰልጣኞች፣ በአሜሪካ እየኖሩ የሚገኙት የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና አሰልጣኝ ሸዋንግዛው አጎናፍር፤ በአሜሪካ፣ አውሮፓ እና አውስትራሊያ የሚገኙ የእግር ኳሱ ቤተሰቦች በዚህ መድረክ ላይ ከነበሩ በጥቂቱ ናቸው፡፡

ይህ ውይይት ከሁለት ሰዓታት በላይ የፈጀ ሲሆን መክፈቻውም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ህዝብ መዝሙር የታጀበ ነበር። በኢትዮጵያ እግርኳስ የቀደመው ታሪክ ላይ ያውጠነጠነ ከዚህም ባለፈ ታሪክ የሰሩትን እናመስግን በቀጣይ የሀገራችን ኳስ ማደግ ካለበት እንዴት እናሳድግ እንዲሁም እናሻግረው በሚሉ መሠረታዊ ሀሳቦችን ላይ ትኩረቱን በስፋት አድርጓል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጅራ ባደረጉት መክፈቻ ንግግርም ውይይቱ ጀምሯል፡፡ በንግግራቸው “የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስጨንቋችሁ ይህን ውይይት በመጀመራችሁ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ያሉ ሲሆን “ያለፉትን ልናመሰግን ይገባናል፤ መወቃቀስ ሳይሆን በአንድነት መስራት ከቻልን እግር ኳሳችንን በሚገባ መገንባት እንችላለን” ብለዋል፡፡

በመቀጠል የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እና አሰልጣኝ የነበሩት ሸዋንግዛው አጎናፍር እሳቸው ያለፉበትን የቀደመውን የእግርኳስ መንገድ አውስተው ይህ ትውልድ የተሻለ እና መስራት የሚችል በመሆኑ ለቀደመው ክብር እየሰጠ መስራት ከተቻለ የኢትዮጵያን ኳስ በሚገባ ማሳደግ ይቻላልም ብለዋል፡፡ የሳቸውንም የእግርኳስ ህይወት ለተሳታፊዎች ያጋሩ ሲሆን አሁንም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ እድገት ከጎን ነኝም ብለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና ኢንስትራክተር አብርሀም መብራቱም የግላቸውን ያለፉበትን ተሞክሮ በማቅረብ ለቀጣይ የእግር ኳሳችን ዕድገት መሠረት ይሆናል ያሉት ሀሳብ ሰንዝረውበታል፡፡

ይህ ውይይት በስተመጨረሻም ያለፈውን የኢትዮጵያን እግር ኳስ ተጫዋቾችን እና ታሪክ የሰሩትን ማመስገን አለብን፤ የተረሱትንም ማስታወስ ይገባናል። ለዚህም ሁላችንም መስራት አለብን ያሉ ሲሆን ይህ እያደረግን ከመጣን የኢትዮጵያን የወደፊት እግር ኳስ ዕድገት በሚገባ ማሳደግ ይቻላል፤ ለአሁኑ ትውልድም ትልቅ ምሳሌ ይሆናል በማለት ተሳታፊዎች ገልፀዋል። ውይይቱም እንደ መጀመሪያ ጊዜ ጥሩ ተሞክሮ የተገኘበትና ለቀጣይም መሠረት የጣለ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ