“ሁለቱ ወንድሞቼን አይቼ ነው እግርኳስ ተጫዋች የሆንኩት” ተስፈኛው ፀጋ ደርቤ

በከፍተኛ ሊጉ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በፊት እና በመስመር አጥቂነት እያገለገለ የሚገኘው የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ውጤት የሆነው ፀጋ ደርቤን በተስፈኛ አምዳችን ተመልክተነዋል፡፡

በሀገራችን ካሉ ከተሞች ውስጥ ተጫዋቾች የላቀ የኳስ ክህሎትን ይዘው ከሚወጡባቸው መካከል አንዷ በሆነችሁ ሀላባ ከተማ ውስጥ ነው ተወልዶ ያደገው። ሁለቱን ታላቅ ወንድሞቹን እያየ ወደ እግር ኳሱ የገባው ይህ ታዳጊ በአካባቢው በሚገኝ የካቶሊክ ጊቢ ውስጥ በአንድ ጣሊያናዊ በተቋቋመው ‘ጁቬንቱስ’ በተባለ የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ገብቶ የልጅነት ጊዜውን ካሳለፈ በኃላ ሀላባ ከተማን ወክሎ ከ15 ዓመት በታች የደቡብ ክልል የኮካ ኮላ ውድድር ላይ ተመርጦ በሚገባ በማገልገል አቅሙን አሳይቷል፡፡

ከሀላባ ከተማ ጋር በነበረው የኮካ ኮላ ውድድር ተሳትፎ በግሉ የኮከብ ተጫዋችነትን ክብርን ያገኘ ሲሆን ከቡድኑ ጋርም ዋንጫን ማሳካት ችሏል፡፡ በወቅቱ ባሳየው ምርጥ እንቅስቃሴ ለክልሉ ተመርጦ አዳማ ላይ በነበረው ውድድር የተጫወተ ሲሆን አሁንም በዚህ ውድድር ላይ ጥሩ መንቀሳቀስ በመቻሉ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተመርጦ አራት ዓመታትን በአካዳሚው ከማሳለፉ ባሻገር በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ሀገሩን አገልግሏል፡፡

ፀጋ በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ባሳየው ድንቅ አቋም መነሻነት በ2011 የኢትዮ-ኤሌክትሪክን ከ20 ዓመት በታች ቡድን ከተቀላቀለ በኃላ የማይቋረጥ ዕድገትን በማሳየቱ በሁለተኛ ዓመቱ በአሰልጣኝ አንዋር ያሲን አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን አድጓል። ዘንድሮም ከፍተኛ ሊጉ በኮሮና ቫይረስ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ምርጥ አቅሙን በማሳየት ላይ ይገኝ ነበር። በክለቡ ወጣት ቡድን ቆይታው የክለቡ ከፍተኛ ግቢ አግቢ የነበረው ፀጋ ደርቤ ዛሬ በተስፈኛ አምዳችን ተጋብዞ ቀጣዩን አጭር ቆይታ አድርጓል።

“ሁለቱ ወንድሞቼን አይቼ ነው እግርኳስ ተጫዋች የሆንኩት። ወንድሞቼ ተጫዋቾች ናቸው። አበሽ ደርቤ አሁን ሀላባ ከተማ ነው የሚጫወተው ታላቃችን ደግሞ ተመስገን ደርቤ ይባላል ፤ ተጫዋች ለመሆኔ መንስኤ የሆኑኝ እነሱ ናቸው። እነሱን እያየው ነው ያደኩት። ታላቃችን ተመስገንም ሀላባ እና ሻሸመኔ ተጫውቷል። አሁን ግን በጉልበት ጉዳት ምክንያት አይጫወትም። ለእኔ አርዓያዬ በተለይ እርሱ ነው። በአጠቃላይ ግን ሁለቱንም አይቼ ነው እዚህ የደረስኩት።

“በኢትዮ ኤሌክትሪክ ዘንድሮ ስንጀምር ጥሩ ነገር ነበረን። ክለቡም ለታዳጊዎች ትኩረት የሚሰጥ ነው። ኮሮና ከመምጣቱ በፊት ጥሩ ጊዜን ነበር እያሳለፍን የነበረው።

“ወደፊት ትልቅ ደረጃ መድረስ እፈልጋለሁ። ከሀገር ውጪ መጫወትንም ነው የማስበው። ለዛም ነው አሁን ላይ ጠንክሬ የምሰራው። ለምፈልገውም ዓላማ ጥሩ ቦታ ላይ ለመድረስም በሚገባ እየሰራሁ እገኛለሁ። እግዚአብሔር ብሎ ይሄም ኮሮና ካለፈ በኃላ ወደስራም ከተመለስን ኤሌክትሪክን በደንብ ማገልገል እፈልጋለሁ። ይሄን ዕድል ለሰጠኝም ክለብ የአቅሜን ላበረክትለት እጓጓለው።

“እዚህ ቦታ እንድደርስ ላደረጉልኝ ቤተሰቦቼ እስከ አሁንም ድጋፋቸው ስላልተለየኝ ላመሰግናቸው እፈልጋለው። ጓደኞቼ ደግሞ ስህተቴን ይነግሩኛል ፣ ይመክሩኛል እንዲሁም እኔ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ ትልቁንም ሚና ተጫውተዋል ላመሰግናቸው እወዳለሁ፡፡”

© ሶከር ኢትዮጵያ



👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!