ሪፖርት | ወልቂጤ ከተማ ከጅማ አባጅፋር ነጥብ ተጋርቷል

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ 9 ሰዓት ላይ ጅማ አባጅፋርን የገጠመው ወልቂጤ ያገኛቸውን አጋጣሚ መጠቀም ባለመቻሉ ነጥብ ተጋርቶ ለመውጣት ተገዷል።

በመጀመሪያው ጨዋታ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር 2ለ2 የተለያዩት ወልቂጤ ከተማዎች የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በዚህም በተስፋዬ ነጋሽ እና አቡበከር ሳኒ ምትክ ሙሀጅር መኪ እና ሥዩም ተስፋዬ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ ሲያስገቡ በአንፃሩ ዛሬም ያለ ተጠባባቂ ግብ ጠባቂ ጨዋታን ያደረጉት ጅማ አባጅፋሮች ደግሞ አራት ለውጦችን በማድረግ በአቡበከር ኑሪ፣ ከድር ኸይረዲን፣ ሀብታሙ ንጉሤ፣ ብዙዓየሁ እንደሻው ምትክ ጃኮ ፔንዜ፣ ውብሸት ዓለማየሁ፣ ትርታዬ ደመቀ እና ሙሉቀን ታሪኩ ባለፈው በአዳማ ከተማ ሽንፈት ካስተናገደው ስብስብ ላይ በአዲስ መልኩ የተካተቱ ተጫዋች ናቸው።

እጅግ አሰልቺ መልክ በነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱም ቡድኖች ከመከላከል ባለፈ ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ በሚገቡበት ወቅት ያልተቀናጀ እና የሚቆራረጡ ሂደቶች የተመለከትንበት ነበር።

አሰልቺ በነበረው አጋማሽ በ8ኛው ደቂቃ ፈጣኑ የወልቂጤ መስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ከፍሬው ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብ የላካትና የግቡ ቋሚ ከመለሰበት ኳስ ውጭ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ የግብ እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ የመሻሻል ምልክቶችን ያሳዩት ወልቂጤ ከተማዎች በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን ቢፈጥሩም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ብቻ 3 አጋጣሚዎችን ሁለት በአህመድ ሁሴን እንዲሁም በአንድ አጋጣሚ በያሬድ ታደሰ አማካኝነት ማግኘት ቢችሉም መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል።

በ58ኛው ደቂቃ ወልቂጤ ከተማዎች ከራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በረጅሙ የላኩትን ኳስ በውብሸት አለማየሁ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ታግዞ የተገኘውን አጋጣሚ አህመድ ሁሴን ከሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ የላከው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ የተመሰበት እንዲሁም በ71ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው አብዱራህማን ሙባረክ ከርቀት አክርሮ የመታውና የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ በወልቂጤ በኩል አስቆጭ ሙከራዎች ነበሩ።

በአመዛኙ መከላከልን ምርጫቸው አድርገው የገቡት ጅማ አባጅፋሮች ከጨዋታው የፈለጉትን አንድ ነጥብ አሳክተው መውጣት ችለዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ