በከፍተኛ ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ለገጣፎ እና ገላን አቻ ተለያይተዋል

የ2013 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ባቱ ላይ 4:00 በተደረገ የምድብ ሀ ጨዋታ ሲጀመር ለገጣፎ ለገዳዲ ከ ገላን ከተማ ያለ ጎል ተለያይተዋል።

የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ ኢብራሂም መሐመድ እና ኢንጅነር ኤሌሮ አፒዮ በክብር እንግድነት በመገኘት ያስጀመሩት ጨዋታ ቀዝቀዝ ባለ ፉክክር፣ ጥቂት የግብ ዕድል እና ጥሩ ዳኝነት ታጅቦ ተከናውኗል።

የመጀመርያው አርባ አምስት አጋማሽ ደቂቃ ድረስ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ያላሳየው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እንቅስቃሴ በሜዳው አጋማሽ ላይ ተገድቦ የቆየ ሲሆን በ26ኛው ደቂቃ ላይ ለገጣፎዎች በቅጣት ምት እና በ28ኛው ደቂቃ ዘካርያስ ከበደ አሻምቶት አንዋር አብዱልቃድር በሞከረው ኳስ ለግብ ቀርበው ነበር። በገላኖች በኩል በ30ኛው ደቂቃ ቢንያም ካሳሁን በግል ጥረቱ ከመስመር እየገፋ ሄዶ የሞከረው ሙከራ ተጠቃሽ ነበር።

ጨዋታው ቀስ በቀስ እየተሟሟቀ ቀጥሎ የተሻለ ፉክክር አስተናግዷል። በ32ኛው ደቂቃ የገላን ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅሞ ጥሩ ኳስ ያገኘው አንዋር አክርሮ መትቶ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻለም። አብዱለጢፍ ሙራድ እና ዝናቡ ባፋ በ43ኛው እና በ45ኛው ደቂቃ ከተመሳሳይ ቦታ ለማስቆጠር ሞክረው መክኖባቸዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ሰዓት ገላኖች ጥሩ እድል አግኝተው አብዱልለጢፍ ሙራድ ከመስመር አፍትልኮ ወደ ጎል በሚያመራበት ወቅት የለገጣፎ ግብ ጠባቂ አብርሀም ከተማ በመውጣት በሰራው ጥፋት በእለቱ ዳኛ አሸናፊ በላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶል። ይህም የውድድሩ የመጀመርያ ቀይ ካርድ ሆኖ ተመዝግቧል።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ መልኩ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ ሙከራ ለማስተናገድ 3 ደቂቃዎች ብቻ ፈጅተውበታል። በ48ኛው ደቂቃ ተደራጅተው ወደ ገላኖች የግብ ክልል የደረሱት ጣፎዎች በፋሲል አስማማው አማካኝነት ግብ ቢስቆጥሩም ከጨዋታ ውጭ ተብሎባቸዋል። ለገጣፎዎች ምንም እንኳን ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ቢከላከሉም በአንድ አንድ አጋጣሚዎች ፍጥነት የታከለበት ሽግግር በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረዋል። በዚህም በ63ኛው ደቂቃ ገላኖች ትተውት የሄዱትን ክፍተት በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ሙከራ ሳዲቅ ተማም እና ፋሲል አስማማው አድርገው መክኖባቸዋል።

በተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ገላኖች በበኩላቸው በ75፣ 81 እና 87ኛው ደቂቃ ከመስመር ባሻሟቸው ኳሶች ጥሩ ጥሩ እድል ቢፈጥሩም ግብ ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። የ2013 የመጀመሪያ ጨዋታም በዚህ መልኩ ያለ ግብ ተጠናቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ