ሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መከላከያ እና ሀዋሳ በድል ሁለተኛውን ዙር ጀመሩ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን የሁለተኛው ዙር በአስረኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ በአዳማ ሲጀመር መከላከያ ጌዲኦ ዲላን 3 ለ 0 ፤ ሀዋሳ ከተማ አዳማ ከተማን በመጨረሻ ደቂቃ ጎል 1 ለ 0 በመርታት ዙሩን በድል ጀምረዋል፡፡

ረፋድ 4፡00 ላይ መከላከያ በቅጣት ባጣቸው አሰልጣኞቹ ሳይመራ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ጠንካራው ጌዲኦ ዲላም ለቡድኑ ፈተና ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም መከላከያ በአስፈሪ አጥቂዎቹ ታግዞ ግቦችን ማግኘት ችሏል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ 22ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር መሳይ ተመስገን ወደ ጎል የላከችላትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር ቡድኗን መሪ በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲያመሩ አስችላለች፡፡

ከእረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ 54ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ከማዕዘን በቀጥታ የመታችው ኳስ የጌዲኦ ዲላዋ ግብ ጠባቂ መስከረም መንግስቱ ስህተት ታክሎበት ለክለቧ ሁለተኛውን ጎል ከመረብ አሳርፋለች፡፡ ጌዲኦ ዲላዎች ከመጀመሪያው ዙር ጥንካሬያቸው በተወሰነ መልኩ የተዳከሙ ሆነው መታየታቸው ጎል እንዳያስቆጥሩ ዳርጓቸዋል፡፡ 65ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ የዲላን የተከላካይ ክፍል ስህተት በሚገባ ተጠቅማ ለራሷ ሁለተኛ ለክለቧ ሶስተኛ ጎልን በማስቆጠር ጨዋታው በመከላከያ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ከሰዓት 10፡00 የአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የዕለቱን ሁለተኛ ጨዋታን በአዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መካከል ተደርጎ ሀዋሳ ከተማ 1ለ 0 አሸንፏል፡፡ ሀዋሳ ላይ በነበረው የመጀመሪያው ዙር በፎርፌ ተሸናፊ የነበረው አዳማ ከተማ በዛሬው ጨዋታ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ቢሆንም ጎል እና መረብን የሚያገናኝ ተጫዋች ባለመኖሩ ሀዋሳ ከተማ በ90ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሯል፡፡ ምስር ኢብራሂም ከርቀት አክርራ የመታቻትን ኳስ የአዳማ ከተማዋ ተከላካይ ምህረት ተስፋልዑል ጨርፋት በራሷ ጎል ላይ ያሳረፈች ሲሆን ጎሉ በሀዋሳዋ አጥቂ ምስር ሊመዘገብ ችሏል። ጨዋታውም በሀዋሳ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡

መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ሁለት አስደንጋጭ የነበሩ ክስተቶች በሜዳ ላይ ተከስተዋል፡፡ የሀዋሳ ከተማዋ አጥቂ መሳይ ተመስገን ከአዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ይርጋሸዋ ጋር ኳስን ለማግኘት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እርስ በእርስ የተጋጩ ሲሆን የአዳማ ከተማዋ ግብ ጠባቂ እምወድሽ ምላሷን የመተንፈሻ አካሏን በመዝጋቱ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል በአምቡላንስ ልታመራ ችላለች፡፡ ሁለተኛው ክስተት ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ መልካሙ ታፈረ ራሱን ስቶ የወደቀ ሲሆን እሱም በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ተጉዞ ከረጅም ሰአት በኃላ ሊነቃ ችሏል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ ከሁለቱም አካላት እንዳረጋገጠችው ግብ ጠባቂዋ እምወድሽም ሆነች አሰልጣኝ መልካሙ በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ