የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዲያ ሆሳዕና 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሁለቱ አሰልጣኞች ከሱፐር ስፖርት ጋር ተከታዩን ቆይታ አስርገዋል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና

ውጤቱ ተገቢ ስለመሆኑ

ማግኘት የነበረብን ውጤት ነበር ፤ በራሳችን ጥፋት ነው ጎል የገባብን በተከላካይ እና በግብ ጠባቂ አለመናበብ ችግር ነው። ከዛ ውጪ ለእኛ ይሄ ትልቅ ውጤት ነው። ምክንያቱም ከአራት ቀን በላይ ቡድኑ አልተዘጋጀም። ስራው የነበረው ሙሉ ለሙሉ የታክቲክ ስራ ነው። በቀላሉ ጎሎች እንዳይቆጠሩብን የምንሰራቸው ስራዎች ነበሩ። ካሳለፍነው ውጣ ውረድ አንፃር ትልቅ ድል ነው ለእኛ ለሀዲያ ሆሳዕናዎች።

ስለመረጡት አጨዋወት

ተጫዋቾቼ ያለዝግጅት ነው የመጡት። ነቅለህ ከወጣህ ደግሞ የሚፈጠረውን አደጋ ማሰብ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአህጉራችን አለ የሚባል ትልቅ ቡድን ነው ፤ ቀላል ቡድን አይደለም። እና ፊት ላይ ያሉት አጥቂዎች በጣም ኃይለኞች ናቸው ፤ የመጫወቻ ቦታ ነው ያሳጣናቸው። ሌላ አማራጭ ያመጣሉ ብለን ሌላም ዕቅድ ይዘን ነበር። ነገር ግን በምንፈልገው መንገድ ስለቀረቡልን ውድድሩን በዚህ መልኩ ጨርሰናል።

የጅማ ቆይታቸው ስኬታማ ስለመሆኑ

በፍፁም አይደለም። በጣም ደስተኛ ሆኜ ያላሳለፍኩበት ውድድር የጅማ ውድድር ነው። እንዲህ ነበር ብሎ ለመናገር ያማል። ብትናገረውም አይመችም ብትተወውም አይመችም። ስለዚህ ይዤው ብቀር ይሻላል።

አሰልጣኝ ማሒር ዴቪድስ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው

ሦስት ነጥብ ፈልገን ነበር የገባነው ግን ማግኘት አልቻልንም። የመጀመሪያው የቅጣት ምት ጎል የገባበት መንገድ እና 1-0 የተመራንበት መንገድ የሚያስቆጭ ነበር። ሆኖም በቶሎ ምላሽ ሰጥተናል። ብቻ ጥሩ ነበር ፤ ውጤቱ ለሁለታችንም ተገቢ ነው።

ስለማጥቃት ዕቅዳቸው

በተወሰኑ ቅፅበቶች ወደ ፊት ስበናቸው ከጀርባ መግባት ችለን ነበር። ጥሩ ቅብብሎችን አድርገን ለመግባት እንሞክር ነበር ፤ ግን ክፍተት አልነበረም። ግዙፍ ተከላካዮቻቸው እና የተከላካይ አማካዩ ክፍተቶችን ይዘጉ ነበር። በተወሰኑ ደቂቃዎችም መስመሮች በኩል የመግባት ዕቅድም ነበረን ግን በፈለግነው ጊዜ ላይ ክፍተት ማግኘት አልቻልንም። በመጨረሻም 1-1 ተጠናቋል።

ጌታነህ ግብ ካስቆጠረ ስለመቆየቱ

ጌታነህ ማስቆጠሩ አይቀርም ፤ ሐት ትሪክ የሰራበትም አጋጣሚም ነበር። ስለሱ ብቻ አይደለም ሁሉም ተጫዋች የድርሻውን ማድረግ አለበት። ሦስት ጨዋታ ብቻ ነው ፤ በቀጣዩ ጨዋታም ሊያስቆጥር ይችላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ