ቅድመ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሰበታ ከተማ

የ14ኛው ሳምንት መጀመሪያ የሆነውን ጨዋታ በዳሰሳችን እንዲህ ተመልክተነዋል።

በወራጅ ቀጠናው መግቢያ በተከታታይ ደረጃዎች ላይ የተቀመጡት ሰበታ እና ድሬዳዋ ነገ እርስ በእርስ መገናኘታቸውን ተከትሎ ከአደጋው ክልል ለመራቅ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። በእርግጥ ሰበታ ከተማ ከተጋጣሚው በሦስት ነጥቦች ልቆ በመገኘቱ የሰንጠረዡን አጋማሽ አልፎ ለመሄድ የሚያስችል ውጤትን ሊያሳካም ይችላል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ከሽንፈት ርቆ ስምንት ነጥቦችን የሰበሰበ መሆኑም ከድሬ ይልቅ የተሻለ ግምት ያሰጠዋል። ከሁለት ሽንፈቶች በኋላ ከሀዋሳ ነጥብ የተጋራው ድሬዳዋ በበኩሉ የዚህ ጨዋታ ውጤት ይበልጥ ያስፈልገዋል። ከቀናውም ደረጃውን እስከ ስምንተኛ ድረስ ከፍ የማድረግ ዕድል ይኖረዋል።

በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ ስር የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ በቀጣይ ጨዋታዎች የሚኖራቸውን አቀራረብ የሚጠቁም ጨዋታ አከናውነዋል። ለኳስ ቁጥጥር የተሻለ ግምት የሰጠ ሆኖ የታየው ድሬዳዋ በኋላ ክፍሉ ላይ አሁንም የአማራጭ እጦት ቢኖርበትም ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ሳያስተናግድ መውጣት መቻሉ ጠንካራ ጎኑ ነበር። ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር እንደቡድን ክፍተቶችን ከመዝጋት አንፃር ለነገው ጨዋታ የሚተርፍ ዓይነት መሻሻልን አሳይቷል። በማጥቃቱ ረገድ ግን የቡድኑ የኳስ ፍሰጥ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ የሚቀረው መሆኑ በነገው ጨዋታ እንዲቸገር ሊያደርገው ይችላል። በተለይም ቡድኑ ከአሰልጠኝ ለውጥ ጋር ተያይዞ ሽግግር ላይ የሚገኝ መሆኑ በተመሳሳይ ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥርን የሚያዘወትር እና የተሻለ ውህደት ላይ ከሚገኝ ቡድን ጋር መገናኘቱ ሊፈትነው መቻሉ ዕሙን ነው።

ሰበታ ከተማ በሒደት መሻሻሎችን እያሳየ የመጣ ቡድን ሆኗል። የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ የሚያስገባቸው ተጨዋቾች በውል እየተለዩ እና መልክ እየያዘ ከመታየቱ በተጨማሪ በውጤትም ረገድ ጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል። የቡድኑ የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ያደረገ አቀራረብ እንደ ፋሲል ባለ ጠንካራ ተጋጣሚ ላይ ብልጫን የማግኘት ደረጃ ላይ መድረሱ በራሱ ለነገው ጨዋታ በራስ መተማመኑን የሚጨምርለት ነው። አሁን ላይ ቡድኑ ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ከመድረስ ባለፈ ከቅብብሎቹ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ትልቁ ክፍተቱ ሆኗል። ከግብ ጋር በተገናኘባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ከመረብ ያረፉት ሦስት ግቦችም መነሻቸውን ያደረጉት ከቆሙ ኳሶች ነበር። በዚህ ረገድ ምንም እንኳን ባለፈው ጨዋታ መሻሻልን ቢያሳይም የድሬዳዋ የኋላ ክፍል ስህተቶች ዳግም ከተፈጠሩ ደከም ብሎ የሚታየው የሰበታ የፊት መስመር በአግባቡ ይጠቀምበታል ወይ የሚለው ጉዳይ በጨዋታው ተጠባቂ ይሆናል።

በጨዋታው ድሬዳዋ ከተማ ፍቃዱ ደነቀ እና በረከት ሳሙኤልን ሰበታ ከተማ ደግሞ ፉዓድ ፈረጃ እና ታደለ መንገሻን በጉዳት ምክንያት እንደማይጠቀሙ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– እስካሁን በሰባት አጋጣሚዎች የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ ውጤት አስመዝግበዋል። ድሬዳዋ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሰበታ በሜዳው ያደረጋቸውን ሦስት ጨዋታዎች በድል ተወጥቷል፡፡

– በዚህ የውድድር ዓመት መክፈቻ ያገናኛቸው ጨዋታ ደግሞ ያለግብ ተጠናቋል።

– በሰባቱ ጨዋታዎች ድሬዳዋ 4 ሰበታ ደግሞ 5 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-3-3)

ፍሬው ጌታሁን

ዘነበ ከበደ– ያሬድ ዘውድነህ – ፍሬዘር ካሣ – ሄኖክ ኢሳይያስ

እንዳለ ከበደ – ዳንኤል ደምሴ – ሱራፌል ጌታቸው

ጁኒያስ ናንጄቦ – ሙኸዲን ሙሳ – አስቻለው ግርማ

ሰበታ ከተማ (4-3-3)

ምንተስኖት ዓሎ

ጌቱ ኃይለማርያም – መሳይ ጻውሎስ – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ

መስዑድ መሐመድ – ዳዊት እስጢፋኖስ – አብዱልሀቪዝ ቶፊቅ

ዱሬሳ ሹቢሳ – እስራኤል እሸቱ – ቡልቻ ሹራ


© ሶከር ኢትዮጵያ