በማሟያው ውድድር ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሰዓት ይከናወናሉ

በሀዋሳ ከተማ ከሰኔ 18 ጀምሮ ሲደረግ የነበረው የትግራይ ክልል ክለቦችን ለመተካት የሚደረገው ውድድር ዕሁድ ሲጠናቀቅ ቀድሞ ያረጋገጠው አዳማ ከተማን የሚከተሉ ሁለት ክለቦችን ለመለየት በሁለት ሜዳዎች ላይ በእኩል ሰዓት ጨዋታ ይደረጋሉ፡፡

በማሟያ ውድድሩ ተቀራራቢ ነጥብ ያላቸው ክለቦች በተመሳሳይ ሰዓት መጫወት እንዳለባቸው ክለቦች ከቀናት በፊት ከአወዳዳሪው አካል ጋር ባደረጉት ስብሰባ የወሰኑ ሲሆን በዚህም መሠረት ዛሬ በሴንትራል ሆቴል የአወዳዳሪ ኮሚቴ እና የአራት ክለብ ተወካዮች በተገኙበት በዕጣ ቡድኖቹ የሚጫወቱበት ሜዳ እና ሰዓት ተለይቶ ታውቋል፡፡ የማሟያውን ጨዋታ በአስር ነጥብ አጠናቆ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የትግራይ ክለቦች ካልመጡ መሳተፉን ቀድሞ ያረጋገጠው አዳማ ከተማ ከ ጅማ አባጅፋር የሚያደርጉት ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ሲደረግ፤ ወልቂጤ ከተማ ከ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ በአርቴፊሻል ሜዳ በተመሳሳይ 4፡00 ላይ የሚከወን ይሆናል፡፡

ቀድመው አለማለፋቸውን ያረጋገጡት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ቀን 8፡00 ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመርሀግብር ማሟያቸውን ይጫወታሉ፡፡