ግዙፉ አጥቂ ዐፄዎቹን ለመቀላቀል ተስማምቷል

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ፋሲል ከነማዎች ናይጄሪያዊውን አጥቂ የግላቸው ለማድረግ ስምምነት ፈፅመዋል።

በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመሩት ፋሲል ከነማዎች ራሳቸውን አጠናክሮ በቀጣይ የውድድር ዓመት ለመቅረብ እና ከፊታቸው የሚጠብቃቸውን የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች በተሻለ መንገድ ለመዘጋጀት ከቀናት በፊት የተከፈተው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ። ከደቂቃዎች በፊትም ከአስቻለው ታመነ ጋር ለመፈራረም መስማማታቸውን ዘግበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ናይጄሪያዊውን አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል መስማማታቸውን አረጋግጠናል።

2010 ላይ ከጅማ አባጅፋር ጋር የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ያገኘው ኦኪኪ በአሁኑ ሰዓት በትውልድ ሀገሩ ናይጄሪያ ይገኛል። ነገርግን ፋሲል ከነማ በአህጉራዊ ውድድሩ የሚሳተፉ ተጫዋቾችን ስም ቀድሞ መላክ ስላለበት ከህጋዊ ወኪሉ ጋር ድርድር ሲያደርግ ቆይቷል። ተጫዋቹም በአፍሪካ መድረክ ለመሳተፍ ካለው ፍላጎት ፋሲል ከነማን ለመቀላቀል መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።