ዋልያው ከቡሩንዲ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ወደ ግማሽ ፍፃሜው የማለፉ ተስፋው ተመናምኗል

የቡሩንዲ አቻውን የገጠመው የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በድጋሜ ነጥብ ተጋርቶ ወደ ቀጣይ ዙር የማለፉ ዕድሉ ጠቧል።

የምድብ የመጨረሻ ጨዋታቸውን ለማድረግ ወደ ሜዳ የገቡት ዋልያዎቹ ነጥብ ከተጋሩበት የኤርትራው ጨዋታ አራት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ የግብ ዘቡ ፅዮን መርዕድን በፋሲል ገብረሚካኤል ሲተኩ ተከላካዩ ሰለሞን ወዴሳ በመሳይ ጻውሎስ፣ አማካዩ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅን በዳዊት ተፈራ እንዲሁም የመስመር አጥቂው ሙኽዲን ሙሳን በብሩክ በየነ ተለውጠዋል።

ጨዋታውን በጥሩ ተነሳሽነት የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኳስን በጥሩ ሁኔታ በመቀባበል ወደ ጎል ለመድረስ ሲጥር ታይቷል። በዚህ ሂደትም ጨዋታው ገና በተጀመረ በአምስተኛው ደቂቃ አቡበከር ናስር ከግራ መስመር ቸርነት ጉግሳ የሰነጠቀለትን ኳስ በመጠቀም የመጀመሪያውን ጎል ሊያስቆጥር ነበር። ነገርግን ተጫዋቹ ወደ ግብ የላከው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ከኳስ ጀርባ በመሆን መጫወት የያዙት ቡሩንዲዎች ግብ እንዳይቆጠርባቸው ግጥግጥ ብለው በመከላከል ሲጫወቱ ተስተውሏል።

አሁንም የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሰቀቀስ የቀጠሉት የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ተጫዋቾች ግብ የማስቆጠሪያ አማራጭ ለማግኘት በተጋጣሚ የመከላከል ወረዳ ላይ መቆየትን መርጠዋል። በተለይ ጠጣሩን የቡሩንዲ ተከላካይ ለማስከፈት ኳስን በፍጥነት ከግራ ወደ ቀኝ ከኋላ ወደ ፊት ሲቀባበሉ ታይቷል። በዚህ አጨዋወትም ዊልያም ሠለሞን በ31ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ሞክሮት ወደ ላይ ወጥቶበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ቡሩንዲዎች እጅግ አስደንጋጭ ጥቃት ለመጀመሪያ ጊዜ ፈፅመው ነበር። በዚህም ቢዚማን አላዲን መናፍ ዐወል የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘው የቅጣት ምት ሲሻማ በጥሩ ዝላይ ኳስ እና መረብን በጭንቅላቱ ሊያስቆጥር ነበር። ይህ ሙከራ ያላስደነገጣቸው ዋልያዎቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የልፋታቸውን ፍሬ አግኝተዋል። በዚህም በቁጥር በዝተው ወደ ቡሩንዲ የግብ ክልል ሄደው የተገኘውን ወርቃማ ኳስ ቸርነት ጉግሳ ወደ ግብነት ቀይሮታል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ ለምንም መሪነት ተገባዷል።

የሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያሰቡት ቡሩንዲዎች በ47ኛው ደቂቃ ምቢሪዚ ኤሪክ አክርሮ በመታው ኳስ አቻ ለመሆን ጥረው መክኖባቸዋል። ከዚህ ሙከራ በኋላም ጫን ብለው ለመጫወት በመሞከር ግብ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ ነበር። በዚህም መሻሻላቸውን በጎል ለማጀብ ያደረጉት ሙከራ በ68ኛው ደቂቃ እውን ሆኖ አቻ ሆነዋል። ከመዓዘን ምት የተሻገረውን ኳስ በሩቁ ቋሚ ሆኖ ያገኘው ሀኪዚማና ኢሳ ኳሱን ከመሬት ጋር በማንጠር ለግብ ጠባቂ እንዳይመች አድርጎ መረብ ላይ አሳርፎታል።

በተቃራኒው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን ኳሶችን በመቀባበል ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መጓዝ ያልቻሉት ዋልያዎቹ ቀስ በቀስ በጨዋታው እድገት እያሳዩ ቢመጡም የጠራ የግብ ማስቆጠሪያ ዕድል እና የቡሩንዲን የግብ ዘብ የፈተነ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ጨዋታው ቀጥሏል። አሠልጣኝ ውበቱ አባተም የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው ወደ ሜዳ ቢያስገቡም ኳስ እና መረብን የሚያገናኝላቸው ተጫዋች አጥተዋል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው የተጫወቱት ቡሩንዲዎች ሀይል የተቀላቀለበት አጨዋወት በመከተል መታተር ይዘዋል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ ተቀይረው የገቡት አስራት ቱንጆ እና በረከት ወልዴ በደቂቃ ልዩነት ጥሩ ጥቃት ፈፅመው የነበረ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ጨዋታውም አንድ አቻ ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ቡሩንዲ በአራት ነጥቦች ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፏን አረጋግጣለች። በምድቡ ሁለት ነጥብ ብቻ ያለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ ምርጥ ሁለተኛ ሆኖ ግማሽ ፍፃሜውን ለመቀላቀል የሌሎች ምድብ ውጤቶችን የሚጠብቅ ይሆናል።