​የሲዳማ ቡና ይቅርታ ጠይቋል

[iframe src=”https://bbc.com/” width=”1%” height=”1″]

በኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ እና በሲዳማ ቡና መካከል የነበረው ጉዳይ በውይይት መፈታቱን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሳወቀ።

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አምስተኛ ሳምንት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ከማድረጋቸው አንድ ቀን በፊት ሲዳማ ቡና በጨዋታው አርቢትር ምደባ ላይ ቅሬታ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል። ክለቡ በወቅቱ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር እና ሥነስርዓት ኮሚቴ የዕለቱ ኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ‘የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ በመሆናቸው ጨዋታውን በዳኝነት እንዳይመሩ’ ሲል ነበር በደብዳቤው የገለፀው።

በዚህ መነሻነት አርቢትሩ ተቃውሟቸውን በእግር ኳስ ስፖርተኞች ህጋዊ ወኪል እና የህግ አማካሪ እና ጠበቃ በሆኑት ብርሀኑ በጋሻው አማካኝነት ጉዳያቸውን ፌዴሬሽኑም ጉዳዩን በመመልከት በሽምግልና መፍታት የተሻለው አማራጭ ነው ብሎ በማመኑ ባለጉዳዮቹን በዛሬው ዕለት በፅህፈት ቤቱ በመጥራት ማወያየቱን በማህበራዊ ድረ ገፆቹ አስታውቋል። የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ፣ የፅህፈት ቤቱ አላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ፣ ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ፣ የህግ አማካሪው አቶ ብርሀኑ በጋሻው እንዲሁም የሲዳማ ቡና ተወካይ የተገኙበት የዛሬው ውይይትም ለጉዳዩ ዕልባት ሰጥቷል።

በውጤቱም ሲዳማ ቡና ያቀረበው ክስ በስህተት የተፈጠረ መሆኑን በማመን ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማን ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴን እና መላውን የእግርኳስ ቤተሰብ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል። ይህ የክለቡ ይቅርታ በዋና ባለጉዳዩ አርቢትር ዘንድ አዎንታዊ ምላሽ በማግኘቱም ጉዳዩ በስምምነት መቋጨቱን የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ ይፋ አድርጓል።