ሪፖርት | አዞዎቹ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ድል አድርገዋል

በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ሀዋሳ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ያለውን የነጥብ ልዩነት ስድስት አድርሷል።

አርባምንጭ ከተማ ከአዳማው የአቻ ውጤት አራት ለውጦች አድርጓል። በዚህም ጉዳት የገጠማቸው ተካልኝ ደጀኔ እና ፍቃዱ መኮንን ጨምሮ የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት ሙና በቀለ እና ሀቢብ ከማል ከረጅም ጊዜ ጉዳት በተመለሰው አህመድ ሁሴን ፣ ፀጋዬ አበራ ፣ መላኩ ኤልያስ እና ሱራፌል ዳንኤል ተተክተዋል።

ሀዋሳ ከተማዎች ከአዲስ አበባው ጨዋታ መልስ ባደረጓቸው ሦስት ለውጦች ደግሞ ከቅጣት የተመለሰው መድኃኔ ብርሀኔ ፣ ሄኖክ ድልቢ እና አብዱልባስጥ ከማል ጨዋታውን ሲጀምሩ ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ዳዊት ታደሰ እና በቃሉ ገነነ ተተክተዋል።

በተጋጣሚዎቹ የቀጥተኝነት ባህሪ እየተንፀባረቀበት ወደ ግብ ክልል በሚላኩ ረጅም ኳሶች የጀመረው ጨዋታ ብዙም ሳይቆይ ከቆመ ኳስ ጎል ተመዝግቦበታል። ጎሉ 12ኛው ደቂቃ ላይ የእንዳልካቸው መስፍንን የማዕዘን ምት አሸናፊ ፊዳ በግንባር በመግጨት ግብ ሲያደርገው የተቆጠረ ነበር።

ከግቡ በኋላም ወደ ሳጥን በመድረሱ የተሻሉ የነበሩት አርባምንጮች ነበሩ። ቡድኑ የሀዋሳ የኳስ ቅብብሎች ወደ አጋማሹ እንደገቡ በማቋረጥ በፍጥነት ወደፊት ይሄድበት የነበረበት መንገድ ወደ ቀኝ አድልቶ ደጋግሞ ወደ ግብ እንዲቀርብ አድርጎታል። በተለይም 19ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ አበራ ከቀኝ መስመር ያሳለፈለትን እንዳልካቸው መስፍን ሳጥን ውስጥ ደርሶ በጠንካራ ምት ወደ ግብ የላከው እና በዳግም ተፈራ ቅልጥፍና የዳነው ኳስ ከባዱ ሙከራ ነበር። 23ኛው ደቂቃ ላይም ተደጋጋሚ ኳሶችን ወደ ሳጥን ሲያደርስ የነበረው ሱራፌል ዳንኤል ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የላከው የተሻማ የሚመስል ኳስ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል።

ሀዋሳ ከተማዎች ከኳስ ውጪ በፍጥነት የሚደራጀው ተጋጣሚያቸውን ለማስከፈት ከብዷቸው ታይተዋል። ቡድኑ በተሻለ ሁኔታ ሳጥን ውስጥ በገባበት የ26ኛ ደቂቃ ሙከራ ወንድምአገኝ ኃይሉ ከቀኝ ወደ ግብ የላከው ኳስ በበርናንድ ኦቻንግ ተጨርፎ ሲያገኘው ብሩክ በየነ ያደረገው ሙከራ ወደ ላይ ወጥቷል። 

ሀዋሳ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የተሻለ ኳስ መስርቶ አርባምንጮችን የተጫነ ቢመስልም ቀጣዩ ከባድ የግብ ሙከራ የመጣው ግን ከአዞዎቹ በኩል ነበር። 35ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅይታደስ አበበ ከዛው ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ ግብ አፋፍ ላይ ኤሪክ ካፓይቶ በጉልበቱ ጨርፎት በግቡ ቋሚ ተመልሷል።

ሀዋሳዎች የተጋጣሚያቸው የቀኝ መስመር ጥቃት ቀዝቀዝ ባለባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ኳስ ይዘው የተሻለ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ከተባረክ ሄፋሞ ኢላማውን ያልጠበቀ የ41ኛ ደቂቃ የግንባር ሙከራ ውጪ ሌላ ዕድል ሳይፈጥሩ ጨዋታው ተጋምሷል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ የአርባምንጭን ከረጅም ኳስ የሚነሱ ጥቃቶች እያሳየን ቢጀምርም ሀዋሳዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነቷን ግብ አግኝተዋል። ብሩክ በየነ የቡድኑን ጥቃት ይዞ ከመጣው ኤፍሬም አሻሞ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ የተቀበለውን ኳስ ገፍቶ በመግባት ሲያመቻችለት ወንድምአገኝ ኃይሉ በግራ እግሩ ጎል አድርጎታል። 

አዞዎቹ በቀጣዮቹ አራት ደቂቃዎች በአህመድ ሁሴን ፣ ፀጋዬ አበራ እና ሱራፌል ዳንኤል መልስ ለመስጠት የጣሩባቸው ሙከራዎች ወደ ውጪ የወጡ ነበሩ።
የማጥቃት ጉልበታቸውን ጨምረው የታዩት ሀዋሳዎች ወደ ግራ አድልተው ተደጋጋሚ ጫና አድርሰዋል። በተለይም ኤፍሬም አሻሞ በሁለት ደቂቃ ልዩነት ከመድኃኔ ብርሀኔ ቀጥሎም ከብሩክ በየነ ለግቡ ቀርቦ ያገኛቸው ዕድሎችን ያልተጠቀመበት መንገድ ለሀዋሳ የሚያስቆጭ ነበር። አርባምንጮች ወደ ፊት በሚልኳቸው ኳሶች አልፎ አልፎ ወደ ኃይቆቹ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ለማስተናገድ ተገደዋል።

ከነዚህም ውስጥ 67ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ኳስ እየገፋ ወደ ሳጥን የተጠጋው ወንድምአገኝ በውጪ እግሩ ያደረሰውን ኳስ ብሩክ ከሳጥን ውስጥ ወደ ግብ ሞክሮ በይስሀቅ ተገኝ ጥሩ የግብ አጠባበቅ ድኖበታል። ይኸው እንቅስቃሴ በማዕዘን ምት ቀጥሎ ኤፍሬም አሻሞ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ አብዱልባስጥ ከማል በግንባሩ ሞክሮ ይስሀቅ በድጋሚ አድኖበታል።

በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ የተጫዋች ቅያሪዎችን ያደረጉት አዞዎቹ የሀዋሳዎችን ጫና ማቀዝቀዝ ችለዋል። ጨዋታው ከሙከራዎች በራቀበት ሁኔታ ውስጥም በድንገት አርባምንጮች ወሳኝ ግብ አስቆጥረዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ አርባምንጮች ረጅም ኳስ ወደ ሳጥን ሲልኩ ሀዋሳዎች ያላጠሩትን ሁለተኛ ኳስ እንዳልካቸው መስፍን በተከላካዮች መሀል ሲያሳልፍለት ተቀይሮ የገባው በላይ ገዛኸኝ ጎል አድርጎታል። 

ተነቃቅቶ የታየው አርባምንጭ ከግቡ በኋላ በሌላው ተቀያሪ አሸናፊ ኤልያስ ከርቀት ተከታታይ መከራዎችን ማድረግም ችሎ ነበር። 

ጨዋታው ወደ መጠናቀቂያው ሲቀርብ  አርባምንጭ ከተማዎች ወደ ጥንቃቄው አዘንብለው ሲጨርሱ ሀዋሳዎች በእንቅስቃሴ እና በቆሙ ኳሶች የፈጠሩትን ጫና ወደ ውጤት ሳይቀይሩ ጨዋታው በአዞዎቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 30 በማድረስ ወደ 9ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ 36 ነጥቤች ላይ ቆሟል።