ቅድመ ዳሰሳ | የ27ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን በዳሰሳችን ተመልክተናቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወልቂጤ ከተማ

የጨዋታ ሳምንቱ በሰንጠረዡ አናት እና ግርጌ ባለው ፉክክር ላይ ልዩነት ሊፈጥር በሚችል ጨዋታ ይጀምራል። ጨዋታው ከተከታዩ ፋሲል ከነማ ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ሦስት ላይ ለደረሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሻነፍ ውጪ ሌላ ምርጫን የማይሰጥ ነው። ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ርቀት ላይ ብቻ ለሚገኘው ወልቂጤ ከተማም አሁን ላይ ያለበት 10ኛ ደረጃ አስተማማኝ ባለመሆኑ ውጤቱ እጅግ አስፈላጊው ነው።

ከዚህ ቀደም ቡድኖቹ ካደረጓቸው ጨዋታዎች እና ሁለቱም የማጥቃት ደመነፍስ ያላቸው ከመሆኑ አንፃር ጨዋታው ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት እና በግብ ሙከራዎች የታጀበ እንደሚሆን ይገመታል። በእርግጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታም ሆነ በፋሲሉ ሽንፈት ጨዋታዎችን ከፍ ባለ ጫና የሚጀምርበት አኳኋን እና ተደጋጋሚ ቀጥተኛ ጥቃቶችን የሚሰነዝርበት አካሄዱ ተቀዛቅዞ ታይቷል። በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ሁኔታው ከብሔራዊ ቡድን አገልግሎት መልስ ከተሰለፉ ተጫዋቾች የድካም ስሜት ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ሲታሰብ ያለፉት ቀናት ከሚሰጡት የማገገም ዕድል አንፃር ቡድኑ ነገ በተሻለ ጉልበት ወደ ሜዳ ሊመለስ እንደሚችል ይታሰባል። ከዚህም ባለፈ በስብቡ ውስጥ ምንም ዓይነት የቅጣት እና የጉዳት ዜና አለመኖሩ ለአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ሰፊ አማራጭ የሚሰጥ በመሆኑ አስፈላጊ ለውጦች ሊደረጉ እንደሚችሉ ይገመታል።

ወልቂጤ ከተማን በተመለከተ ከነገው ጨዋታ በፊት በዋነኝነት ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ትናንት እና ዛሬ ርዕሰ ዜና ሆኖ የቆየው የጌታነህ ከበደ የቅጣት ውሳኔ ነው። በሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ የሦስት ጨዋታ ቅጣት አግኝቶት የነበረው አጥቂው በሊጉ አክሲዮን ማህበር እና በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የዲስፕሊን ኮሚቴ ውሳኔዎች መሀል ለነገው ጨዋታ የመሰለፉ ነገር ሲዋልል ቆይቷል። ማምሻውን ግን ክለቡ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ መሰረት በማድረግ የነገውን ጨዋታ አደርጋለው የሚል ውሳኔ ላይ በማድረሱ ተጫዋቹን ሊጠቀምበት የሚችልበት ዕድል ይኖራል። አሰልጣኝ ተመስገን ዳናም ለአብዱልከሪም ወርቁ ሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥሪ ሚና በመስጠት የሸፈኑትን ቦታ በነጋው ጨዋታ በቀጥታ ተጫዋቹን በማስገባት ወይንስ በሌላ መንገድ የፊት መስመራቸውን ያዋቅራሉ የሚለው ተጠባቂ ሆኗል። ይህ የክለቡ ውሳኔ ከተተገበረ ግን የዚህ ጨዋታ አወዛጋቢነትም ለቀጣይ ቀናት መነጋገሪያ መሆኑ የሚቀር አይመስልም። ከዚህ ውጪ በተሰማ የቡድ ዜና ወልቂጤዎች አበባው ቡታቆ እና ተስፋዬ ነጋሽን በጉዳት እንደሚያጡ ታውቋል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ፣ ረዳቶች ዘሪሁን ኪዳኔ እና ኃብተወልድ ካሳ ፣ አራተኛ ዳኛ በላይ ታደሰ

ተጨማሪ ዳኞች – አበራ አብርደው እና ሸዋንግዛው ከበደ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– በርካታ ግቦችን ባስተናገዱት የእስካሁኖቹ ሦስት ጨዋታዎቻቸው በሙሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለድል መሆን ችሏል። በዚህም ጊዮርጊስ 11 ግቦችን ሲያስመዘግብ ወልቂጤ አምስት አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-2-3-1)

ቻርለስ ሉኩዋጎ

ሱሌይማን ሀሚድ – ምኞት ደበበ – ፍሪምፖንግ ሜንሱ – ሄኖክ አዱኛ

ሀይደር ሸረፋ – ጋቶች ፓኖም

አቤል ያለው – ከነዓን ማርክነህ – ቸርነት ጉግሳ

ኢስማኤል ኦሮ-አጎሮ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሰዒድ ሀብታሙ

ዮናታን ፍሰሀ – ዮናስ በርታ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ኢሞሞ ንጎዬ – ሀብታሙ ሸዋለም

ጫላ ተሺታ – አብዱልከሪም ወርቁ – ያሬድ ታደሰ

ሀዋሳ ከተማ ከ ባህር ዳር ከተማ

የነገው ሁለተኛ ጨዋታ የሦስተኛ ደረጃ ተፎካካሪው ሀዋሳን ከወራጅ ቀጠናው እምብዛም ካልራቀው ባህር ዳር ያገናኛል። ሀዋሳ ከተማ ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ በድሬዳዋ ላይ ካሳካው ድል መልስ ነው የነገውን ጨዋታ የሚያደርገው። በአንፃሩ ከሊጉ መሪ ጋር ከባድ ጨዋታ ያደረገው ባህር ዳር ከተማ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። የነገው ጨዋታ ግን ከሀዋሳ ይበልጥ በመቀመጫ ከተማው ለሚጫወተው ባህር ዳር እጅግ በጣም ወሳኝ ይሆናል ምክንያቱም ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው መግቢያ ሁለት ነጥቦች ርቀት ላይ ብቻ ነው የሚገኘው።

የድሬዳዋው ድል ሀዋሳ ከሦስት ነጥብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከጠንካራ ጎኑ ጋርም የተገናኘበት ነበር። ከዚህ ቀደም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ጥምረት ጨዋታዎችን አሸንፎ የሚወጣበት ዋነኛ መለው የነበረ ሲሆን ለረጅም ሳምንታት ያጣውን ይህንን ብርታቱን መልሶ አግኝቷል። በሆኑም በነገውም ጨዋታ ለኳስ ቁጥጥር አብዝቶ የማይፋለም እና ከኳስ ውጪ ወደ ራሱ ሜዳ አድልቶ የሚጫወት ሀዋሳ ይጠበቃል። ቡድኑ ከዕረፍቱ መነሻነት በሚመስል መልኩ በጥሩ ጉልበት ጨዋታውን መከወኑ ለነገም የሚረዳው ሲሆን አዲስዓለም ተስፋዬ እና መስፍን ታፈሰም ከቅጣት እና ጉዳት ይመለሱለታል።

በተመሳሳይ ወሳኝ ተጫዋቹ ፍፁም ዓለሙን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ባህር ዳር ከተማም ከከዚህ ቀደም ጨዋታዎቹ አንፃር ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የተሻለ ተንቀሳቅሷል ማለት ይቻላል። በእርግጥ ከነገ ተጋጣሚው አንፃር በሲዳማ ቡና እንደደረሰበት ሽንፈት ሁሉ የኳስ ቁጥጥር ጥራቱ ይበልጥ መሻሻል ካልቻለ ለከባድ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ሊያጋልጠው ይችላል። በጊዮርጊሱ ጨዋታ ሁለት ግቦችን ያስቆጠረው አጥቂው ኦሴይ ማዉሊ ብቃት ግን በነገውም ጨዋታ ለባህር ዳር በእጅጉ ያስፈልገዋል። የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በመጨረሱ በኩል ድክመት ያለበት ቡድኑ ጋናዊው አጥቂ ከፍ ባለ ትኩረት ላይ ሲገኝ ምን ያህል ጠቃሚ ሊሆን እንደሚቻ በማየቱ በነገው ጨዋታ ዕቅዱ ውስጥ የኳስ ፍሰቱ ዋነኛ መቋጫ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።

የጨዋታው ዳኞች – ዋና ዳኛ ተካልኝ ለማ ፣ ረዳቶች ትንሳኤ ፈለቀ እና ዳንኤል ጥበቡ ፣ አራተኛ ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ

ተጨማሪ ዳኞች – ተመስገን ሳሙኤል እና ሙሉነህ በዳዳ

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሁለቱን በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ሀዋሳ ሁለቴ ባህር ዳር ደግሞ አንድ ጊዜ ድል አድርገዋል። በጨዋታዎቹ እኩል አራት አራት ግቦችንም አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-5-2)

መሀመድ ሙንታሪ

ካሎንጂ ሞንዲያ – አዲስዓለም ተስፋዬ – ላውረንስ ላርቴ

ዳንኤል ደርቤ – አብዱልባስጥ ከማል – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

አህመድ ረሺድ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – ግርማ ዲሳሳ

አብዱልከሪም ኒኪማ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – አለልኝ አዘነ

ተመስገን ደረሰ – ኦሴይ ማዉሊ – ፍፁም ዓለሙ