ቅዱስ ጊዮርጊስ የሊጉ ቻምፒዮን ሆኗል

ዛሬ በተመሳሳይ ሰዓት በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ፈረሰኞቹ የሊጉን ክብር ሲቀዳጁ አዲስ አበባ ሦስተኛው ወራጅ ቡድን ሆኗል።

የሊጉን አሸናፊ እና ቀሪውን ወራጅ ቡድን ለመለየት ዛሬ 04:00 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአዲስ አበባ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ በባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንዲሁም ሀዋሳ ከተማ ከአዳማ ከተማ በአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ከሦስቱ ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ እና የቅዱሱ ጊዮርጊስ ነጥብ መጣል የውድድሩ አሸናፊ ያደርጋቸው የነበሩት ፋሲል ከነማዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ በበረከት ደስታ ጎል ቀዳሚ ሆነዋል። ሆኖም የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወስን ይችሉ የነበሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከአንድ ደቂቃ በኋላ በኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ጎል ወደ ዋንጫው መቅረብ ችለዋል። 

በሌላው ጨዋታ የተሻለ የመትረፍ ዕድል የነበራቸው አዳማ ከተማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በአብዲሳ ጀማል ሁለት እንዲሁም በዳዋ ሆቴሳ አንድ ጎል በማስቆጠር ለከርሞው በሊጉ የመቆየታቸውን ነገር ወደ ማረጋገጡ ተጠግተዋል። ከዕረፍት መልስ በአፄ ቴዎድሮስ ስታዲየሙ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በአቤኔዘር ኦቴ እና ብሩክ በየነ ጎሎች ልዩነቱን ቢያጠብም አዳማ ከተማ ጨዋታውን 3-2 በማሸነፍ በሊጉ መቆየቱን ማረጋገጥ ችሏል።

በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ጨዋታዎች ሁለተኛ አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊስ 54ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ሁለተኛ ግብ አክሎ የቻምፒዮንነቱን ክብር ይበልጥ ወደራሱ አስጠጋ። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየምም 61ኛው ደቂቃ ላይ ፋሲል ከነማ በበዛብህ መለዮ ጎል መሪነቱን ወደ ሁለት አሳድጓል። ነገር ግን ጊዮርጊስ መሪነት መስፋት ፍልሚያውን ወደ ፈረሰኞቹ መውሰዱን ተከትሎ ቀጣዩ ተጠባቂ ጉዳይ ሦስተኛውን ወራጅ ቡድን መለየቱ ላይ ነበር።

የተሻለ ዕድል የነበራቸው አዲስ አበባ ከተማዎች የድሬዳዋ ሽንፈት በሊጉ ያቆያቸው የነበረ ቢሆንም ድሬዳዋ ከተማ ከ77ኛው ደቂቃ በኋላ በጋዲሳ መብራቴ ፣ ሄኖክ አየለ እና አብዱርሀማን ሙባረክ ጎሎች ጨዋታውን 3-2 ማሸነፍ ችሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ ከመውረድ ተርፏል።

በአንፃሩ ከድሬዳዋ ግቦች በኋላ ተስፋ የቆረጡት አዲስ አበባዎች በአማኑኤል ገብረሚካኤል ሁለት ተጨማሪ ግቦች አስተናግደው በቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 ለመሸነፍ በቅተዋል። በዚህም የድሬዳዋ ከተማ የመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች የዕለቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ሆነው አዲስ አበባን ወደ ሁለተኛው የሊግ ዕርከን ሲሸኙ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ65 ነጥቦች የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን መሆኑን አረጋግጧል።

ይህንንም ተከትሎ በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም የተለያዩ የክብር ዕንግዶች በተገኙበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ኃላፊዎች ፣ የቡድን አባላት እና ደጋፊዎች ግዙፉን ዋንጫ በመረከብ ደስታቸውን አጣጥመዋል።