ቻን 2023 | ስለ አልጀርያን ብሔራዊ ጥቂት መረጃዎች

በዛሬው ዕለት 04:00 ላይ ኢትዮጵያን ስለምትገጥመው ደጋሿ አልጀርያ ብሔራዊ ቡድን ጥቂት መረጃዎች እናጋራችሁ።

አልጀርያ የምታዘጋጀውን የቻን ውድድር መቃረብ አስመልክተን የተለያዩ መረጃዎች ስናቀርብላቹ መቆየታችን ይታወሳል። አሁን ደግሞ በዛሬው ዕለት ከምሽቱ 4:00 በኔልሰን ማንዴላ ስቴድየም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የምትገጥመው የአልጀርያን ቡድን በወፍ በረር ለመቃኘት እንሞክራለን።

\"\"

በቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ እግርኳስ
ጥሩ ብቃት በማሳየት የሚገኙት የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎቹ አልጀርያዎች በርከት ያሉ ተጫዋቾች (9) ከሊጉ ሻምፒዮን ቤሎይዝዳድ አካተው ወደ ውድድሩ በመቅረብ የመጀመርያው የምድብ ጨዋታ ድል አድርገዋል።

ቀደም ብለው በሀገር ውስጥ ሊግ የተውጣጡ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት \”Algerian A\” በሚል ስያሜ ቡድን በማዋቀር የተለያዩ የአቋም መለክያ ጨዋታዎች ስያደርጉ እና በተለያዩ ውድድሮች ሲሳተፉ የቆዩት አሰልጣኝ ማጂድ ቡግሄራ የስብስባቸው ጥራት ለዋንጫ እንዲታጩ ያደርጋቸዋል።

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ 25 ጨዋታዎች (17) ድል (6) አቻ እና (2) ሽንፈት ማስተናገዱን ሲታይ ደግሞ ለውድድሩ ክብር አለማጨት ከባድ ነው። ከዛ በተጨማሪም ውድድሩ በሜዳቸው እና በደጋፍያቸው ፊት መሆኑ ትልቅ ግምት እንዲሰጣቸው የምያስገድድ ሌላ ምክንያት ነው።

አሰልጣኙ ከወራት በፊት በወጣቶች ስብስብ ከማውሪታንያ እና ሴኔጋል ካካሄዱት የአቋም መለክያ ጨዋታዎች ውጪ ላለፉት በርካታ ወራት በአመዛኙ ተመሳሳይ ፊቶች ይዘው ነበር ጨዋታዎቻቸውን ያካሄዱት።

ቡድን ምንም እንኳ ባለፉት 25 ጨዋታዎች ባስመዘገበው ውጤት ትልቅ ግምት ቢሰጠውም በውድድሩ መቃረብያ ለቻን ይፋ ባደረጉት የመጨረሻ ስብስብ የአቋም መለክያ ጨዋታዎች አድርገው በተከታታይ አቻ በመለያየታቸው በቡድኑ ብቃት ጥርጣሬ የገባቸው ጥቂቶች አይደሉም። ሆኖም ቡድኑ በመጀመርያው ጨዋታ ሊብያን በጠባብ ውጤት አንድ ለባዶ አሸንፎ ውድድሩን በድል ጀምሯል።

\"\"

አልጄሪያ በውድድሩ ያላት ታሪክ

አልጀርያ በ2011 በሱዳን በተካሄደው ሁለተኛው የቻን አፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ተሳትፎዋ ነው። በውድድሩም በአሰልጣኝ ዓሊ ፈርጋኒ እየተመራች በአራተኛነት ፈፅማለች ፤ ይህ ውጤትም የውድድሩ ምርጥ ውጤትዋ ነው።

ቡድኑ ከዚህ ውድድር ውጪም ከሁለት ዓመት በፊት በ2021 የአረብ ካፕ አሸናፊ መኖሩ መረሳት የለበትም።

የቡድኑ ተጠባቂ ተጫዋቾች

በቡድናቸው ውስጥ በርከት ያሉ ተጠባቂ ተጫዋቾች ለያዘው የአልጀርያዎች ስብስብ ይመራል ተብሎ የሚጠበቀው የሀያ ስምንት ዓመቱ የቀድሞ የኒምስ ተጫዋች ካሪም አሪቢ ነው። በፈረንሳዩ ኒምስ ሁለት የውድድር ዓመታት አሳልፎ ወደ ወቅቱ የአልጀርያ ሻምፕዮን ቤሎዚዳድ ያመራው ይህ አንጋፋ አጥቂ በልምድ ረገድ ቡድኑን ይጠቅማል ተብሎ ይጠበቃል። ሌላው የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የወቅቱ የአልጀርያ ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ የሆነው አማካዩ አህመድ ኬንዶሲ ነው። ከሁለቱ ተጫዋቾች ውጭም የሀያ አንድ ዓመቱ መሐመድ በልኪሪ ተስፋ ከተጣለባቸው ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው።