ጎፈሬ እና አርባምንጭ ከተማ የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፅመዋል

ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት በዛሬው ዕለት ፈፅሟል።

\"\"

ከበርካታ የሀገር ውስጥ እንዲሁም የምስራቅ አፍሪካ ክለቦች ጋር አብሮ የሚሰራው ጎፈሬ በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከሚሳተፈው አርባምንጭ ከተማ ጋር በትጥቅ ጉዳዮች እንዲሁም የብራንዲንግ እና የፋይናንስ አቅም ማሳደጊያ የጋራ ሥራዎች ለመከወን ስምምነት ፈፅሟል። በአርባምንጭ ከተማ በተከናወነው የፊርማ ስምምነት ላይ አርባምንጭን ወክለው የክለቡ ፕሬዝዳንትና የከተማው ከንቲባ አቶ ማርቆስ ማቲያስ እና ሥራ-አስኪያጁ አቶ ታምሩ ናሳን ጨምሮ የቦርድ እና የደጋፊ ማኅበር አመራሮች እንዲሁም ጎፈሬን ወክለው ምክትል ሥራ-አስኪያጁ አቶ አቤል ወንድወሰን እና የማርኬቲንግ ሀላፊው አቶ ፍፁም ክንድሼ ተገኝተዋል። የክለቡ ፕሬዝዳንት እና የጎፈሬ ምክትል ሥራ-አስኪያጅ ስምምነታቸውን በፊርማ ካፀኑ በኋላ ዝርዝር ጉዳዮችን ገለፃ አድርገዋል።

መድረኩን የመሩት ሥራ-አስኪያጁ አቶ ታምሩ ከጎፈሬ ጋር የሥራ ግንኙነት ቢኖራቸውም ያሉ ነገሮችን አጠናክሮ ወደፊት ለመሄድ ይህንን ስምምነት ማድረጉ እንዳስፈለገ አንስተው የክለቡ ፕሬዝዳንት ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል።

\”ጎፈሬ ጥራት ያላቸውን ምርቶች ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች እንደሚያቀርብ ይታወቃል። ከክለባችንም ጋር በተለያየ መንገድ እየሰራን ቆይተናል። አሁንም በቀጣይ ጊዜያት ስለምንሰራቸው ስራዎች ስምምነት ለመፈፀም ወደ ከተማችን ስለመጣችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት እፈልጋለው።\” ያሉት ፕሬዝዳንቱ እንደ ከተማ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ ከሜዳ የራቀውን ደጋፊ ለመመለስ ሰፋፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልፀው በዋናነት ጎፈሬ ለክለቡ ከሚያቀርበው ትጥቅ ባለፈ በደጋፊዎች የሚነሳውን የማሊያ እጥረት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ አመላክተዋል።

\"\"

አቶ አቤል በበኩላቸው ጎፈሬ የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት ከሆነው እና ስመጥር ተጫዋቾችን ካፈራው አርባምንጭ ከተማ ጋር ለመስራት በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ አጋርተው ከዚህ ቀደም ከክለቡ ጋር በግዢ እና ሽያጭ ጉዳዮች ብቻ የነበረውን የሥራ ግንኙነት አሳድገው በስፖንሰርሺፕ ደረጃ ማድረጋቸው ለሁለቱም አካላት ጥቅም እንዳለው አስረድተዋል። በስምነቱም የደጋፊዎች ማሊያ እና በክለቡ ስር የሚገኙ ቡድኖችን የትጥቅ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ጉዳዮች እንደተካተቱ ገልፀዋል። ከትጥቅ ባሻገርም ክለቡ የፋይናንስ አቅሙን የሚያሰፋባቸው የማርኬቲንግ ስትራቴጂዎች፣ ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታዎች እና ሌሎች የአጋርነት ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልፀዋል።

በስምምነቱ መሠረት ጎፈሬ ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ለሁሉም የአርባምንጭ ከተማ የፆታ እና የእድሜ እርከን ቡድኖች ትጥቆችን እንዲሁም የደጋፊዎች ማሊያን የሚያቀርብ ይሆናል።