ሪፖርት | ኃይቆቹ ከመረብ ጋር በታረቁበት ጨዋታ ከፈረሰኞቹ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል

ማራኪ ፉክክር የታየበት እና ሀዋሳ ከተማዎች ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ግብ ያስቆጠሩበት ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ፈረሰኞቹ ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ካስተናገደ ቡድን በረከት ወልዴ እና አቤል ያለውን በሀይደር ሸረፋ እና ቸርነት ጉግሳ ተክተው ገብተዋል። ኃይቆቹ በበኩላቸው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ዳንኤል ደርቤ ፣ ሰለሞን ወዴሳ ፣ በቃሉ ገነነ ፣ ዓሊ ሱሌማን እና ሙጂብ ቃሲምን በአቤኔዜር ኦቴ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ አዲሱ አቶላ እና ተባረክ ኤፋሞ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

ተጠባቂ የነበረው እና ማራኪ ፉክክር የታየበት ይህ ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ጥሩ የማጥቃት ፍላጎት ያሳዩበት ነበር። በአጋማሹ ከኳስ ውጭ ጫና በመፍጠር ተጋጣሚያቸው ምቾት ተሰምቶት ኳስ እንዳይቀባበል ውጤታማ ጫና ያደረጉት ኃይቆቹ በርካታ ሙከራዎች ባያደርጉም ሁለት ጥራት ያላቸው ዕድሎች ፈጥረዋል። ልክ ጨዋታው እንደተጀመረ እዮብ በረዥሙ የተሻማለትን ኳስ ተጠቅሞ የፈጠረው ዕድል እና አዲሱ የጊዮርጊስ ተጫዋቾች በፈጠሩት ስህተት አግኝቶት በደካማ ውሳኔ አሰጣኝ ችግር ያመከነው ኳስ ይጠቀሳሉ። እዮብ በመልሶ ማጥቃት የመጣው ኳስ አሻግሮት አዲሱ ሳያገኘው የቀረው ኳስም አስቆጪ ነበር።

\"\"

በአጋማሹ የኃይቆቹን ወጥመድ አልፈው የተሳካ ቅብብል ማድረግ የተሳናቸው ፈረሰኞቹ የመጀመርያው አጋማሽ የመሀል ሜዳ ብልጫ ለመውሰድ የተቸገሩበት ነበር። ይህን ተከተሎም በረዣዥም ኳሶች እና የቆሙ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ተገደዋል። ፍሪምፖንግ ከመዕዘን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ እና ዳዊት ከቅጣት ምት ተሻምቶ አጎሮ የጨረፈው ኳስ አግኝቶ በደካማ እግሩ ያደረገው ሙከራም በተጠቀሰው መንገድ የተፈጠሩ ሙከራዎች ነበሩ። በሰላሳኛው ደቂቃ ግን ፈረሰኞቹ የአጋማሹን ትልቁ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዋል ፤ ኦራ አጎሮ የሀዋሳ ከተማ ተከላካዮች ስህተት ተጠቅሞ መቶት ግብ ጠባቂው በጥሩ መንገድ ያከሸፈው ኳስም ፈረሰኞቹን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ ፈረሰኞቹ በቸርነት አማካኝነት መሪ የሚያደርጋቸው ግብ አግኝተዋል። የመስመር ተጫዋቹ ሄኖክ በረጅሙ ያሻማውን ኳስ የሀዋሳ ተከላካዮች ያለመናበብ ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ በግንባሩ ማስቆጠር ችሏል። ሆኖም ተጫዋቹ ግቡን ሲያስቆጥር በዐይኑ አከባቢ በደረሰበት ጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል።

ከግቡ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ተጫዋቾች ቀይረው በተመሳሳይ መንገድ በረዣዥም ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ቢሞክሩም በአጨዋወቱ ጥራት ያላቸው የጎል ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።

በሰባኛው ደቂቃም ግን ሀዋሳዎች ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ከመረቡ ጋር ታርቀዋል። በፈረሰኞቹ ሳጥን ውስጥ ጥፋት ተሰርቷል በሚል የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ተባረክ ኤፋሞ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ በኋላ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ፈረሰኞቹ ጠጣሩን የሀዋሳ የመከላከል አደረጃጀ ጥሰው የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ሆኖም በመጨረሻው ደቂቃ አሸናፊ የሚሆኑበት ዕድል አግኝተው ነበር። ሄኖክ ከግራ መስመር አከባቢ የተገኘው ቅጣት ምት አሻምቶ ተገኑ በግንባር ገጭቶ በመጨረሻው ደቂቃ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።

አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ በመጀመርያው አጋማሽ ያቀዱትን ነገር እንዳሳኩ ጠቅሰው በአጋማሹ የግብ ዕድሎች እንዳልተጠቀሙ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በሁለተኛው አጋማሽ የአቻነትዋን ጎል ለማስቆጠር ያደረጉት እንቅስቃሴ ጥሩ እንደነበር ተናግረዋል። የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጠንካራ ጨዋታ እንደነበር ጠቅሰው እንደነበረባቸው ችግሮች ውጤቱ መጥፎ እንዳልሆነ ገልፀዋል። በተከታታይ ጨዋታዎች ስላስመዘገቡት ውጤት የተጠየቁት አሰልጣኙ በሥነ ልቦና ደረጃ ችግር እንደሌላባቸው በመጥቀስ በቀጣይ ጨዋታዎች አሻሽለው ለመቅረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

\"\"