መረጃዎች | 100ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት በመጀመሪያ ቀን የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ሲዳማ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ

ቀን 7 ሰዓት ላይ በሚደረገው የሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር በጥሩ መሻሻል ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ሳምንት ከናፈቃቸው ድል ጋር ከታረቁት አርባምንጮች ጋር ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ባለባቸው የወራጅነት ስጋት ምክንያት ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

ከተከታታይ አራት የ 1-0 ድሎች በኋላ ከወላይታ ድቻ ጋር በሁለት ቀን በተደረጉ 45 ደቂቃዎች ያለ ግብ የተለያዩት ሲዳማዎች ከወራጅ ቀጠናው ከሚገኘው ተጋጣሚያቸው በአምስት ነጥቦች ርቀው መቀመጣቸው የነገውን ጨዋታ ከተረቱ ስጋት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሊሆናቸው ይችላል። ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ከድቻ ጋር ነጥብ ሲጋራ በዝናብ ምክንያት አጋማሹ ላይ በተቋረጠው ጨዋታ የሜዳው አስቸጋሪነት ተጨምሮበት ጥሩ ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩም ተቋርጦ በነጋታው በተደረገው አጋማሽ ግን በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት እንቅስቃሴያቸው የተገደበ ሆኖ ተስተውሏል። ሆኖም ይህ ዝናባማ ሁኔታ በነገው ዕለት ከቀጠለም አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ድልን አልመው ከመግባታቸው አንጻር ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ይጠቀማሉ ተብሎ አይጠበቅም።

\"\"

አሰልጣኝ በረከት ደሙን በቀጠሩ ማግስት ኢትዮ ኤሌክትሪክ ላይ ግቦችን በማዝነብ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል የተመለሱት አዞዎቹ በተለይም በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ላይ ደካማ የነበረው የተከላካይ መስመራቸው ተሻሽሎ ግብ ሳያስተናግድ በወጣበት አጋጣሚ በአንጻሩ ደካማ ሆኖ አንድም ግብ ማስቆጠር ተስኖት የነበረው የአጥቂ መስመሩ የግብ ርሃቡን በማስታገሱ ለነገው ጨዋታም በተሻለ መነሳሳት እንዲቀርብ ምክንያት ሊሆነው ይችላል። አዲሱ አሰልጣኝ ያሳዩት አቀራረብ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም ከነገው ተጋጣሚያቸው አንጻር ግን ፈታኝ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ ካሳካቸው አምስት ድሎች አራቱን ያሳካው በምሽት ጨዋታዎች መሆኑ የተለየ ምክንያት ባይኖረውም ከሚፈልጉት የዓየር ሁኔታ አንጻር የነገው ጨዋታ በቀትር ሰዓት መደረጉ መጠነኛ እፎይታን ሊነሳቸው ይችላል።

በሲዳማ ቡና በኩል ያኩቡ መሐመድ  ከጉዳት ሲመለስ ቴዎድሮስ ታፈሰ ግን አሁንም ጉዳት ላይ በመሆኑ የነገው ጨዋታ የሚያልፈው ሲሆን
በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ አበበ ጥላሁን እና ወርቅይታደስ አበበ ለጨዋታው መድረሳቸው አጠራጣሪ ሲሆን ኤሪክ ካፓይቶ ከጉዳት ይመለሳል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ 17 ጊዜያት ተገናኝተው 11 ጨዋታዎች አቻ ሲጠናቀቁ አርባምንጭ ከተማ 4 ሲዳማ ቡና ደግሞ 2 ጨዋታዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር በ 40 ነጥቦች ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ በተቃራኒ አቅጣጫ የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ለገጣፎ ለገዳዲን ሲያገናኝ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን አጠናክረው ቻምፒዮን ለመሆን ለገጣፎዎች ደግሞ ከሊጉ ቢወርዱም ለክብር የሚያደርጉት ፍልሚያ ቀን 10 ሰዓት ላይ ይጀመራል።

ከሽንፈት እና ከአቻ ውጤት መልስ ወላይታ ድቻን 2-1 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተከታያቸው ባህርዳር ከተማ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ወደ አዳማ በመዛወሩ ከ አሥር ቀናት ዕረፍት በኋላ ወደ ጨዋታ ይመለሳሉ። ይህ የዕረፍት ጊዜም በተለይም በዝናባማ የዓየር ሁኔታ ወቅት  ከፍተኛ ጉልበት በሚፈልገው የሀዋሳ ሜዳ ላይ በሚፈልጉት ብርታት ለመጫወት እንደሚያግዛቸው ይታመናል። ለተከታታይ ዓመት ቻምፒዮን ለመሆን ግስጋሴያቸውን የቀጠሉት  ፈረሰኞቹ ከኢትዮጵያ መድን (48) በመቀጠል ሁለተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (46) ማስቆጠራቸና እና ዝቅተኛውን የግብ መጠን (16) ማስተናገዳቸው ተጋጣሚያቸው ደግሞ ከፍተኛውን የግብ መጠን (57) ማስተናገዱ እና ዝቅተኛውን የግብ መጠን (18) ማስቆጠሩ በተጨማሪም ለገጣፎ ከክብር ውጪ ድል የሚፈልግበት ዓላማ ባለመያዙ ጨዋታውን ቀላል እንደሚያርግላቸው ቢጠበቅም ከድል መልስ በተሻለ መነቃቃት ላይ የሚገኙት ለገጣፎዎች ፈታኝ ሆነው ሊቀርቡ ይችላሉ። ካለፉት 13 ጨዋታዎች 12 በሚሆኑት እንዲሁም ላለፉት ተከታታይ ስምንት ጨዋታዎች በመጀመሪያው አጋማሽ አንድም ግብ ያላስቆጠሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ማሳካት ከሚፈልጉት ዕቅድ እና የሜዳው ሳይጠበቅ በዝናብ አስቸጋሪ መሆን አንጻር ጨዋታውን ቀድመው ለመቆጣጠር በመጀመሪያ ደቂቃዎች ለሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥተው ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

\"\"

ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ በውድድር ዓመቱ ሦስተኛ ድላቸውን አዳማ ላይ ያሳኩት ለገጣፎዎች ምንም እንኳ ቁጥሮች አልደግፋቸው ብለው ከሊጉ ቢወርዱም ሜዳ ላይ የሚያሳዩት እንቅስቃሴ ጠንካራ ነበር። ካለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ግብ ያስቆጠረው ቡድኑ  ጨዋታዎችን በሚጀምርበት ግለት አለመጨረሱ ዋናው ድክመቱ ሲሆን ጥሩ ብቃት ላይ ይገኝ የነበረውን አዳማ ከተማ መርታቱ የሚፈጥርለት መነሳሳት እንዳለ ሆኖ ለክብር ከመጫወቱ ባሻገር ተጫዋቾቹ ያላቸውን ሁሉ አድርገው የብዙዎችን ትኩረት በመሳብ በመጪው የውድድር ዘመን ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ለመቆየት የሚያደርጉት ጥረት ቡድኑ አሁንም ፈታኝ ሆኖ እንዲቀርብ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መጫወታቸው ጨዋታውን ከባድ የሚያደርግባቸው ቢሆንም ከጫና ነጻ ሆነው መቅረባቸው ሜዳ ላይ ጥሩ ተፅዕኖ ይፈጥርላቸዋል ተብሎም ይጠበቃል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ምኞት ደበበ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ሲታወቅ አማኑኤል ገብረሚካኤል ለአዳማው ቆይታ ካልሆነ በቀር ለዚህ ጨዋታ አይደርስም። ረመዳን የሱፍ እና ፍሪምፖንግ ሜንሱም በአምስት ቢጫ ጨዋታው የሚያልፋቸው ይሆናል። በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል ደግሞ ሱለይማን ትራኦሬ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-0 ማሸነፉ ይታወሳል።