ሀዋሳ ከተማ ዝግጅት የሚጀምርበት ቀን ታውቋል

በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ የሚመራው ሀዋሳ ከተማ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት የሚገቡበት ቀን ይፋ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ከ1990 ጀምሮ መሳተፍ የጀመረው ሀዋሳ ከተማ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት በአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ በሊጉ ቆይታን ያደረገ ሲሆን በክረምቱ የአሰልጣኙ ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ዳግም ክለቡን እንዲመራ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመት ኮንትራቱን በማደስ የዝውውር መስኮቱን በመጠቀም አራት ተጫዋቾችን በይፋ በማስፈረም እና ከአንዱ ጋር መስማማታቸው ይታወሳል። ክለቡ በዝውውሩ እንየው ካሳሁን ፣ አማኑኤል ጎበና እና ፂዮን መርዕድን በእጁ ያስገባ ሲሆን ከታፈሰ ሰለሞን ጋር ስምምነት መፈፀሙ እና የበርካታ ተጫዋቾችን ውል ማራዘሙ ይታወሳል።

ለ2016 የውድድር ዘመን በቀጣዮቹ ቀናትም አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደሚጨምር የሚጠበቀው ሀዋሳ ከተማ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደሚገባ ተጠቁሟል። ዛሬ ነሀሴ 12 የክለቡ አባላት በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል ከተሰባሰቡ በኋላ የህክምና ምርመራ እና የስነ ምግባር ትምህርቶች እና መሰል ጉዳዮች ለተጫዋቾቹ ከተሰጠ በኋላ የፊታችን ሰኞ ነሀሴ 15 በይፋ ልምምዳቸውን እንደሚጀምሩ ታውቋል።