ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና በጫላ ተሺታ ብቸኛ ግብ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል።

የቀድሞውን የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋች መላኩ ዳምጠውን ሕልፈት ተከትሎ በሕሊና ጸሎት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ኢትዮጵያ ቡና ብልጫውን መውሰድ ችሏል። በዚህም 5ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቡንም በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ኳስ ይዞ የገባው በፍቃዱ ዓለማየሁ በተረጋጋ አጨራረስ የላከውን ኳስ ጫላ ተሽታ በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል።

 

የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ይሁን እንጂ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ቡናዎች 11ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ኤርሚያስ ሹምበዛ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ገጭቶ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ጫላ ተሺታ ኳሱን ሳያገኘው ቀርቶ የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ተደራጅተው መግባት ያልቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በአጋማሹ ብቸኛውን የግብ ሙከራቸውን 41ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ካርሎስ ዳምጠው ከኤፍሬም አሻሞ በተቀበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አስወጥቶበታል። ይህም የአጋማሹ የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ በኢትዮጵያ ቡና 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ የተቀዛቀዘ አጀማመር ቢታይበትም 55ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። ጫላ ተሺታ በጥሩ ብቃት ተጭኖ ያገኘውን ኳስ ወደ ሳጥን እየገፋ በመውሰድ ከማቀበል አማራጭ ጋር ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ መልሶበታል።

ድሬዳዋ ከተማዎች የተጫዋች ቅያሪዎችን በማድረግ ወደ ተሻለ የጨዋታ ግለት ሲመለሱ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 72ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል። ኤፍሬም አሻሞ በጥሩ ንክኪ ያሳለፈለትን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አቤል አሰበ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አግዶበታል። ሆኖም ጨዋታው በጭማሪ ደቂቃዎች አማኑኤል አድማሱ ካደረገው ለግብ የቀረበ ሙከራ በተጨማሪ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት በኢትዮጵያ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።