ሪፖርት | ብርቱካናማዎቹ ሜዳቸውን በድል መርቀዋል

ሀምበሪቾዎች አስራ አንደኛ ሽንፈታቸውን ባስተናገዱበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ በዘርዓይ ገብረስላሴ ብቸኛ ጎል 1ለ0 በመርታት የውድድር ዘመኑን ስድስተኛ ድል አግኝቷል።

የአዳማ የሊጉ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ በተካሄደበት ወቅት ድሬዳዋ ከተማ ወልቂጤ ከተማን ድል ባደረጉበት ወቅት ከተጠቀመው አሰላለፍ ውስጥ ቴዎድሮስ ሀሙን ከቅጣት በተመለሰው እያሱ ለገሠ ፣ ዳዊት እስጢፋኖስን በሔኖክ አንጃው ሲለውጡ በአንፃሩ ሀምበሪቾ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለ ጎል ከቋጩት ጨዋታ አኳያ በተደረጉ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ትዕግስቱ አበራ ፣ አፍቅሮት ሠለሞን ፣ እና የኋላሸት ፍቃዱን በዲንክ ኪያር ፣ በፍቃዱ አስረሳኸኝ እና አላዛር አድማሱ ተክተዋቸዋል።

በድሬዳዋ ስታዲየም በጣለው ሐይል የቀላቀለ ዝናብ የተነሳ 37 ያህል ደቂቃዎችን ሊዘገይ በቻለው ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ፊፋ ስታዲየሙ መመዘኛዎችን ማለፉን የሚያረጋግጥ የሰርተፍኬት ርክክብ ስነ ስርዓት ተከናውኖ ጨዋታው በእያሱ ፈንቴ የመሐል ዳኝነት ጅምሩን አድርጓል። ቀዝቀዝ ባለ አየር በታጀበው ጨዋታ የመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻሉ ሆነው ቢቀርቡም በተጋጣሚያቸው ቀዳሚ የሆነ ሙከራን ግን አስተናግደዋል።

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም በፍጥነት እግራቸው ስር የሚገቡ ኳሶችን ከመስመር በማሻማት ጎል ለማስቆጠር የሚታትሩት ሀምበሪቾዎች 10ኛው ደቂቃ በረከት ወንድሙ ከቶሎሳ የተቀበለውን ኳስ ከቀኝ ወደ ሳጥን ሲያሻማ እያሱ ለገሠ በአግባቡ ከግብ ክልሉ ገጭቶ አለማራቁን ተከትሎ በፍቃዱ አስረሳኸኝ ያገኛትን ኳስ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ቢመታትም በግቡ አግዳሚ ታካ ወጥታበታለች። ዝግ ባለ እና ብዙም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ሳያስመለክተን በዘለቀው ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ወደ በሁለቱም መስመሮች በኩል በተለይ የግራውን ክፍል አብዱለጢፍን በመጠቀም በይበልጥ ጫናን የሚያሳድሩ መልካም አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል።

17ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋዎች ከማዕዘን ምት አብዱለጢፍ መሐመድ በቀጥታ ወደ ጎል አክርሮ መቶ ፓሉማ ያወጣበት እና ከአንድ ደቂቃ መልስ በተመሳሳይ አብዱለጢፍ ከግራ ወደ ሳጥን የላካትን ኳስ አቤል አሰበ አግኝቶ ቢመታትም በቀላሉ ወደ ውጪ ሰዷታል። የሀምበሪቾን ወደ ኋላ አፈግፍጎ መጫወትን ተከትሎ የአጋማሹን የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች በይበልጥ መሐል ሜዳው በመጠቀም ከርቀት በሚደረጉ እና በሰንጣቂ ኳሶች ዕድሎችን ለመፍጠር የሚታትሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 40ኛው ደቂቃ አቤል አሰበ በተከላካይ መሐል አሾልኮ የሰጠውን ኳስ ቻርለስ ሙሴጌ ከግብ ጠባቂው ፓሉማ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ጋናዊው የግብ ዘብ በጥሩ ብቃት ካዳነበት በኋላ ወረድ ያሉ ፉክክሮች ያስመለከተን አጋማሽ ያለ ጎል ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታ ተመልሶ ሁለት ደቂቃዎች ያህል ቡድኖቹ ከተጫወቱ በኋላ ሀምበሪቾዎች ዲንክ ኪያርን በትዕግስቱ አበራ ተክተው ቀጥለዋል። ረጃጅም ኳሶችን ወደ መስመር እና ከተከላካይ ጀርባ በድግግሞሽ በመጣል ግቦችን ለማግኘት የሚደረጉ ፉክክሮችን በሁለቱም በኩል ባስተዋልንበት ቀጣዮቹ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች የደቂቃን መግፋት ተከትሎ የቀኙን ሜዳ በጥልቀት አልያም በተሻጋሪ ኳሶች በተደጋጋሚ አደገኛ ሙከራዎችን አድርገዋል። 57ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሔኖክ አንጃው አክርሮ መቶ ፓሉማ ከያዘበት ከስድት ደቂቃዎች መልስ ድሬዎች ግብ አስቆጥረዋል። አቤል አሰበ ወደ ቀኝ የሰጠውን ዳግማዊ አባይ ወደ ሳጥን ሲያሻግር ዘርዓይ ገብረስላሴ ነፃ ቦታ ሆኖ ያገኛትን ኳስ የቀድሞው ቡድኑ መረብ ላይ አሳርፏታል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ወጥተው የተጋጣሚ ሦስተኛው የሜዳ ክፍሎ ደርሶ ዕድሎችን ለመፍጠር ብዙም ስኬታማ ያልነበሩት ሀምበሪቾዎች በተቃራኒው በባለሜዳው በተደጋጋሚ ጫና

የገቡበት ሂደት መመልከት ችለናል። ድሬዎች በሙህዲን ሙሳ የርቀት ሙከራ እና 73ኛው ደቂቃ ላይ በተለይ ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ ጋናዊው ተከላካይ መሐመድ አብዱልጋኒዮ በግንባር ገጭቶ የግቡን ቋሚ ብረትን ኳሷ ገጭታ የወጣችበት የድሬዳዋን ብልጫ የሚያሳዩ ሙከራዎች ነበሩ። 91ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከቅጣት ምት ኤፍሬም አሻሞ አክርሮ የመታን ኳስ ግብ ጠባቂው ፓሉማ ከግብ ብረቱ ጋር ተጋግዘው ካወጡት በኋላ በመጨረሻም ጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ 1ለ0 አሸናፊነት ተቋጭቷል። ድሉም ለድሬዳዋ ስድስተኛ ማሸነፉ ሲሆን በአንፃሩ በጨዋታው የመጨረሻ ሀያ አምስት ደቂቃዎች የተዳከሙት ሀምበሪቾዎች 11ኛ የውድድር ዘመኑ ሽንፈታቸው ሆኖ ተመዝግቧል።