ሪፖርት | ፋሲል ከነማ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል

ዐፄዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ግቦች ኢትዮጵያ መድንን 2ለ0 መርታት ችለዋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን ከፋሲል ከነማ ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ከ16ኛ ሳምንት ጨዋታቸው የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መድኖች ከባህር ዳር ጋር 0ለ0 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በርናንድ ኦቼንግ እና አሚር ሙደሲር ወጥተው አዲስ ፈራሚዎቹ ሚሊዮን ሰለሞን እና ሐይደር ሸረፋ ሲገቡ ሀዋሳን 2ለ1 የረቱት ፋሲሎች በአንጻሩ አምሳሉ ጥላሁን እና ይሁን እንዳሻውን አስወጥተው አቤል እንዳለ እና ቃልኪዳን ዘላለምን በቋሚ አሰላለፍ አስገብተዋል።


10 ሰዓት ሲል በዋና ዳኛ ዳንኤል ግርማይ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያ 15 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ፋሲል ከነማዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ዮናታን ፍስሃ ከግራ መስመር ያመቻቸውን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዩ ሚሊዮን ሰለሞን በግሩም ሸርተቴ አግዶበታል።

ጨዋታው 14ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ዐፄዎቹ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በስህተት ያቀበለውን ኳስ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ወደ ውስጥ ሲቀንሰው አቤል እንዳለ በማይታመን ሁኔታ ኳሱን መረቡ ላይ ሳያሳርፈው ቀርቷል። ፋሲሎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ችለውም ነበር።

ቀስ በቀስ ወደ ተሻለ ግለት በመምጣት ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች 19ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ወገኔ ገዛኸኝ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ ቢገጨውም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመጠኑ በማስመለስ ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት መድኖች 25ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ወገኔ ገዛኸኝ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ከቀኝ መስመር ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ወጥቶበታል። ያሬድ ዳርዛም 28ኛው እና 32ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ ሙከራዎችን አድርጎ በግብ ጠባቂው ይድነቃቸው ኪዳኔ ተመልሰውበታል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ዐፄዎቹ ጥሩ ፉክክር ቢያደርጉም አጋማሹ ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮጵያ መድኖች ግብ የሚያስቆጥሩበት አጋጣሚ ቢያገኙም አቡበከር ወንድሙ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው መሐመድ አበራ እንደ አቤል እንዳለ ሁሉ ኳሱን ክፍቱ መረብ ላይ ማሳረፍ ሳይችል ቀርቶ አባክኖታል።

አምሳሉ ጥላሁንን እና አፍቅሮተ ሰለሞንን በቃልኪዳን ዘላለም እና በኤልያስ ማሞ ቀይረው በማስገባት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ያሻሻሉት ፋሲል ከነማዎች ቅያሪያቸው ፍሬ አፍርቶ 68ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። አፍቅሮተ ሰለሞን በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ከንክኪ በኋላ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግሩም ክህሎት ኳሱን ወደኋላ ሲያዞር ሚሊዮን ሰለሞን ጥፋት ሠርቶበት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በቀኝ በኩል የግብ ጠባቂውን አቡበከር ኑራ እጅ ጥሶ አስቆጥሮታል።

ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን ያስቀጠሉት ዐፄዎቹ በተደጋጋሚ ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ሲችሉ 85ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። አፍቅሮተ ሰለሞን ከጌታነህ ከበደ የተቀበለውን ኳስ ተቀይሮ ለገባው ናትናኤል ማስረሻ ሲያመቻችለት ናትናኤልም ከሳጥን አጠገብ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በደረሱበት ልክ ፈታኝ ሙከራቸውን ለማድረግ የተቸገሩት መድኖች ጎልቶ በታየባቸው አባካኝነታቸው ምክንያት መረጋጋት ተስኗቸው ታይቷል። በተለይም ግብ ካስተናገዱ በኋላም ይበልጥ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። በአንጻሩ ባደረጓቸው የተጫዋቾች ቅያሪያች ምክንያት ጠንካራ እየሆኑ የቀጠሉት ፋሲሎችም ጨዋታውን 2ለ0 ማሸነፍ ችለዋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የፋሲል ከነማው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ክፍት ጨዋታ እንደነበር እና ሁለቱም የግብ ዕድሎችን ማባከናቸውን በመጠቆም ከዕረፍት መልስ ያደረጉት ቅያሪ ውጤታማ እንዳደረጋቸው እና ከቀናት በፊት ቡድኑን የተቀላቀለው አፍቅሮት ሰለሞን እና ተቀይሮ ገብቶ የመጀመሪያ የፕሪሚየር ሊግ ጎሉን ያስቆጠረው ናትናኤል ማስረሻን እንቅስቃሴ መልካም እንደነበር ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በበኩላቸው ቡድናቸው ለውጥ እያሳየ መሆኑን የጠቆመ እንቅስቃሴ ማድረጉን በመግለጽ የሚያባክኗቸው ኳሷች ዋጋ እያስከፈሏቸው እንደሆነ እና አዳዲስ የሚያስፈርሟቸው ተጫዋቾችን ለዚህ መፍትሔ ለማድረግ እንደሚጥሩ በመናገር በተከታታይ ጨዋታዎች መሐመድ አበራ ክፍት ጎሎችን ቢያባክንም የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ እንደሆነ እና ወደፊት መረጋጋት ሲችል ጠንካራ አጥቂ እንደሚሆን ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።