ሪፖርት | የሳምንቱ ምርጥ ጨዋታ በድሬዳዋ አሸናፊነት ተጠናቋል

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ ብርቱ ፉክክር በተደረገበት ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ በቻርለስ ሙሴጌ ግቦች ቡናማዎቹን 2ለ1 አሸንፈዋል።

በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ተገናኝተው ብርቱካናማዎቹ በ16ኛው ሳምንት ሀምበርቾን 1ለ0 ሲያሸንፉ የተጠቀሙት አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ ቡናዎች በአንጻሩ በተመሳሳይ ሳምንት ሲዳማ ቡናን 3ለ0 ካሸነፉበት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ አማኑኤል አድማሱን አሳርፈው ብሩክ በየነን በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ አስገብተዋል።

ምሽት 1 ሰዓት ላይ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ መሪነት የተጀመረውን ጨዋታ በተሻለ ግለት የጀመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው መሐመድ አብዱለጢፍ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረው ኳስ በኢስማኤል አብዱልጋኒዩ እና በበረከት አማረ ተነካክቶ ሊቆጠር ተቃርቦ ወንድሜነህ ደረጄ በጥሩ ቅልጥፍና ከመስመር መልሶታል። ብርቱካናማዎቹ በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም በያሬድ ታደሰ አማካኝነት ከረጅም ርቀት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርገው ግብ ጠባቂው በረከት ይዞበታል።

 

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመውሰድ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት የሞከሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ድሬዳዋዎች በአንጻሩ በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ 31ኛው ደቂቃ ላይ የግብ ዕድል ፈጥረው ሱራፌል ጌታቸው በግሩም ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ዘርዓይ ገብረሥላሴ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ጨዋታውን ተቆጣጥረው ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ቡናማዎቹ 40ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው አብዱልከሪም ወርቁ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ መስፍን ታፈሰ ዘግይቶ ደርሶበት ሳይጠቀምበት ሲቀር 45ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ሄኖክ አንጃው መስፍን ታፈሰ ላይ በሠራው አደገኛ ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ዋሳዋ ጄኦፍሪ ወደ ግብ በቀጥታ መትቶት ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተጋግሎ እና ለተመልካች ማራኪ ሆኖ ሲቀጥል ግሩም አጀማመር ያደረጉት ብርቱካናማዎቹ 49ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መሐመድ አብዱለጢፍ በጥሩ ሁኔታ ገፍቶ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ ንጹህ የግብ ዕድል አግኝተው ብሩክ በየነ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ መልሶበታል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም አማኑኤል ዮሐንስ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። አማካዩ ከደቂቃ በኋላም ጉዳት አስተናግዶ በኤርሚያስ ሹምበዛ ለመተካት ተገዷል።

ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ቡናማዎቹ ባልታሰበ አጋጣሚ ግብ አግኝተዋል። ከመሃል ሜዳ በተሻገረው ኳስ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ዳግማዊ ዓባይ እና ግብ ጠባቂው አብዩ ካሳዬ ሳይግባቡ ቀርተው መስፍን ታፈሰ በመሃል ገብቶ በድንቅ ሁኔታ ወደ ውስጥ ሲያሻግረው አንተነህ ተፈራ በቀላሉ አስቆጥሮታል።

የነበራቸውን መረጋጋት እያጡ የመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች 75ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው አንተነህ ተፈራ ከቀኝ ወደ ውስጥ በመቀነስ ያመቻቸውን ኳስ ያገኘው በፍቃዱ ዓለማየሁ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። ሆኖም ብርቱካናማዎቹ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ የግብ ዕድል ፈጥረው መሐመድ አብዱለጢፍ ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ በግንባር ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።

ይበልጥ እየተጋጋለ በቀለጠው ጨዋታ በቡናማዎቹ በኩል 81ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከብሩክ በየነ በተመቻቸለት ኳስ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሲችል ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ብርቱካናማዎቹ ግብ ቢያስቆጥሩም ግቡ ሲቆጠር ቻርለስ ሙሴጌ በተከላካዩ ወንድሜነህ ደረጄ ላይ በሠራው ጥፋት ግቡ ተሽሯል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ሰባት ደቂቃዎች ውስጥ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ግብ አስቆጥረዋል። መሐመድ አብዱለጢፍ ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በድሬዳዋ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት ጨዋታ እንደነበር እና ከዕረፍት መልስም የተሻሉ እንደነበሩ በመናገር ተጫዋቾቻቸው ባደረጉት ጥረት ደስተኛ መሆናቸውን በመግለጽ ተጋጣሚያቸውንም በጠበቁት ልክ እንዳገኙት እና ማንንም ተጫዋችም እንደማይወቅሱ ሲናገሩ የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ኮማንደር ሽመልስ አበበ በበኩላቸው በመጀመሪያው አጋማሽ ተጋጣሚያቸው እንደጠበቁት ኳሱን መቆጣጠሩን ገልጸው ጨዋታ ለማሸነፍ የሚረዳቸውን ቀመር እንዳገኙትም ገልጸዋል።