ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አርባምንጭ ከተማ ወሳኝ ድል አስመዝግቦ መሪነቱን አጠናክሯል

በምድብ ለ የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ዛሬ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ አርባምንጭ ከተማ ሸገር ከተማን በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ አሸንፎ ወሳኝ ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሸገር ከተማ የመሀል ክፍሉን በመቆጣጠር እና በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የግብ እድል ለመፍጠር ጥረት አርጓል። በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማ በመስመር እና በረጃጅም ኳስ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያረግ ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎ በ15ኛው ደቂቃ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ከጥልቅ የሸገር ከተማ የመሀል ክፍልን የቀነሰ ኳስ ለአሸናፊ ተገኝ በመስጠት አሸናፊ በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።

ከግቡ መቆጠር በኋላም አርባምንጭ ከተማ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ሸገር ከተማም ኳስን በመመስረት ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። ሆኖም ጠንካራውን የአርባምንጭ ከተማን የተከላካይ ክፍል መስበር ተስኗቸው ምንም ግብ ሳይቆጠር በአርባምንጭ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ የሚባል ፉክክር እና ተመጣጣኝ እንቅስቃሴን ተመልክተናል። በ47ኛው ደቂቃ የሸገር ከተማ ተጫዋች የሆነው በኃይሉ ተስፋዬ ግልፅ የግብ አግኝቶ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቶ ቡድኑን ወደ ጨዋታው መመለስ ሚችልበትን እድል አባክኗል። ጨዋታው በሄደ ቁጥር አርባምንጭ ከተማ የወሰዱትን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ጥንቃቄን አብዝቶ ጨዋታውን ፍጥነት ለመቀነስ ሲሞክሩ ተስተውሏል።

በ76ኛው ደቂቃ የሸገር ከተማ ተጫዋች የሆነው ዘነበ ከድር ከግራ መስመር ወደ አርባምንጭ ከተማ የግብ ክልል የላከውን ኳስ አላዛር ሽመልስ በግንባሩ በመግጨት ለጥቂት የግቡ አግዳሚውን ታካ መውጣት ችሏል። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠረ ግብ ተጠናቆ አርባምንጭ ከተማ 1-0 በሆነ ውጤት ጣፋጭ ሶስት ነጥብ አሳክተዋል።