ሪፖርት | አዳማ ከተማ ከ7 ዓመታት በኋላ ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፏል

አዳማ ከተማ በሙሴ ኪሮስ እና ቢኒያም ዐይተን ድንቅ ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን 2ለ1 መርታት ችሏል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር አዳማ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተገናኝተው አዳማዎች በ18ኛው ሳምንት ሀምበርቾን 3ለ0 ሲያሸንፉ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ ፈረሰኞቹ ሻሸመኔ ከተማን 2ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ባደረጉት የአንድ ተጫዋች ለውጥ ዳግማዊ አርዓያን አስወጥተው አማኑኤል ኤርቦን በቋሚ አሰላለፍ አስገብተዋል።


10፡00 ሲል በቅርቡ ሕይወቱ ላለፈው የባህር ዳር ከተማ አማካይ አለልኝ አዘነ የሕሊና ጸሎት በማድረግ በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ በሴኮንዶች ውስጥ ሙሴ ኪሮስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ባሕሩ ነጋሽ አስወጥቶበታል።

ጨዋታው 6ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዮሴፍ ታረቀኝ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሙሴ ኪሮስ ኳሱ ዓየር ላይ እንዳለ በእግሩ በመምታት በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ጊዮርጊሶች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጭነው ለመጫወት በመሞከር 8ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከቀኝ መስመር አሻግሮት ሞሰስ ኦዶ በግንባሩ በገጨው እና 11ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር አሻምቶት በተከላካይ በተመለሰ ኳስ በረከት ወልዴ ከሳጥን አጠገብ ባደረገው ሙከራ የተጋጣሚን ሳጥን መፈተን ችለው ነበር።

መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ አዳማዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን የሚያጠናክሩበት ዕድል ፈጥረው ከራሳቸው የግብ ክልል የተሻገረውን ኳስ የመሃል ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ ሳይቆጣጠረው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው ቦና ዓሊ ያደረገው ሙከራ መረቡ ላይ ሲጠበቅ ኳሱ ለጥቂት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ወጥቶበታል።

በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ፈረሰኞቹ ሁለተኛ ግብ ከማስተናገድ ከተረፉበት የቦና ዓሊ ሙከራ በኋላ በሴኮንዶች ልዩነት አቻ መሆን የሚችሉበት ወርቃማ የግብ ዕድል አግኝተው ናትናኤል ዘለቀ በድንቅ ዕይታ በሰነጠቀው ኳስ አማኑኤል ኤርቦ ከግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ግብ ጠባቂው አግዶበታል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቁ በተጨመሩ 3 ደቂቃዎች ውስጥ የመጀመሪያው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ቢኒያም ዐይተን ከሙሴ ኪሮስ በተመቻቸለት ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ሲመልስበት በሴኮንዶች ልዩነት የጊዮርጊሱ አማኑኤል ኤርቦ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ አስወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ አዳማዎች 54ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ጊዮርጊሶች በግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገሩትን ኳስ መመለስ ችለው ቢኒያም ዐይተን ከረጅም ርቀት በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ እየገፋ በመውሰድ ለዮሴፍ ሲያቀብለው ዮሴፍም በግሩም ሁኔታ ሰንጥቆ ለራሱ ለቢኒያም መልሶ አመቻችቶለት ቢኒያም ዐይተን ግብ ጠባቂውን ባሕሩ ነጋሽን አታልሎ በማለፍ እጅግ ማራኪ በሆነ ብቃት አስቆጥሮታል።

እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ የተቸገሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 69ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከረጅም ርቀት ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የተጋጣሚያቸውን የመከላከል አደረጃጀት ለመፈተን ሲቸገሩ ቢስተዋልም 74ኛው ደቂቃ ላይም ሄኖክ አዱኛ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል የወጣ ሙከራም ማድረግ ችሎ ነበር።

ጨዋታው 77ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፈረሰኞቹ ግብ አስቆጥረዋል። በቅድሚያም 76ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ኤርቦ ወደ ግብ የሞከረውን ኃይል የለሽ ኳስ ያገኘው ረመዳን የሱፍ እጅግ ወርቃማውን የግብ ዕድል ቢያባክነውም ከሴኮንዶች በኋላ ግን ራሱ ረመዳን የሱፍ በሳጥኑ የግራ ክፍል በመግባት ተቀይሮ ከገባው ተገኑ ተሾመ የተመቻቸለትን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ተቀይሮ የገባው ታምራት ኢያሱ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በመጠኑ እየተቀዛቀዙ ሄደው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት አዳማዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተቀይሮ የገባው ኤልያስ ለገሠ ከዮሴፍ ታረቀኝ በተቀበለው ኳስ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ መልሶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም አዳማ ከተማ ፈረሰኞቹን ለመጨረሻ ጊዜ በ2009 ካሸነፈ በኋላ የመጀመርያው ሆኖ ሲመዘገብ ቅዱስ ጊዮርጊስም የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ለመቻል አሳልፎ ለመስጠት ተገዷል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የውጤቱን መታሰቢያ በአለልኝ አዘነ ሞት ምክንያት ሀዘን ውስጥ ላሉት የስፖርቱ ቤተሰቦች በማበርከት ቡድናቸው መሻሻል ላይ እንዳለ እና በክፍያ ምክንያት ተፈጥሮ የነበረው ችግር መቀረፉ እንደረዳቸው ሲናገሩ ከሁለቱ ግቦችም የሙሴ ኪሮስን ግብ እንደሚመርጡ ጠቁመዋል። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው የትኩረት እና የፍላጎት ማጣት እንደነበረባቸው በመግለጽ ጨዋታው መጥፎ እንዳልነበር ሆኖም በእግርኳስ በሁሉም ጨዋታ ላይ ጥሩ መሆን እንደማይቻል ሲናገሩ የተጫዋቾችን ጥረት አድንቀው የአጨራረስ እና የቅንጅት ችግራቸው ላይ እንደሚሠሩ ሀሳባቸውን ስጥተዋል።