​ጸጋዬ ኪዳነማርያም የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሁለተኛ ዙር ደካማ አቋም ያሳየው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን ቀጣዩ የክለቡ አስልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡

ክለቡ የውድድር ዘመኑን በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ መሪነት ጀምሮ ቀስ በቀስ የውጤት ቀውስ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ አሰልጣኙን በማሰናበት በምክትሉ በረከት ደሙ መሪነት እንዲቀጥል ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በውድድር አመቱ አጋማሽ ከንግድ ባንክ ጋር የተለያዩት ጸጋዬ ኪዳነማርያምን ለመቅጠር ድርድር ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ ሀዋሳ ላይ በተደረገ ስምምነት ቀጣዩ የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በረከት ደሙ ደግሞ የአሰልጣኝ ጸጋዬ ረዳት ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ጸጋዬ ኪዳነማርያም በትራንስ ኢትዮጵያ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ረዳት ኋላ ላይ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ ሆነው በመስራት የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኘነት ህይወትን የጀመሩ ሲሆን በሐረር ቢራ 7 የውድድር ዘመናት ካሳለፉ በኋላ በ2005 ለአጭር ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናን አሰልጥነዋል፡፡ ቀጥሎም እስከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ አድርገዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ እንደሌሎች አመታት ሁሉ በዝውውር መስኮቱ ላይ እየተሳተፈ የማይገኝ ሲሆን እስካሁን ምንም ተጫዋች ማስፈረም አልቻለም፡፡ ሆኖም አሰልጣኝ ጸጋዬ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ለክለቡ የሚያስፈልጉ ተጫዋቾችን የመመልመል ስራ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *