“ጨዋታው ከባድ ቢሆንም ተጫዋቾቻችን የተሻለ አቋም ላይ ይገኛሉ ብዬ አስባለው” መሐመድ አሕመድ

በሚቀጥለው ዓመት ኬንያ ለምታስተናግደው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) ለማለፍ የሚደረጉ የማጨረሻ ማጣሪያ ዙር ጨዋታዎች ቅዳሜ ተጀምረዋል፡፡ ከምስራቅ እና መካከለኛ አፍሪካ ዞን ሶስት ሃገራት (አዘጋጇን ኬንያ ጨምሮ) በውድድሩ ላይ ተሳትፎ ያደረጋሉ፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ 10፡00 ሰዓት ላይ ሱዳንን ሀዋሳ ላይ ታስተናግዳለች፡፡ የሱዳን ብሄራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ላይ ካደረገ በኃላ ቡድኑን ለረጅም ግዜያት ያክል የመሩት መሃመድ አብደላ አህመድ (በቅፅል ስማቸው ማዝዳ) ከሶከር ኢትዮጵያ በቡድናቸው ዝግጅት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገዋል፡፡

ስለዝግጅት
ይህ በሃገር ውስጥ ሊግ ብቻ ለሚጫወቱ ተጫዋቾች የተዘጋጀ ውድድር ነው፡፡ ለዚህም ለውድድሩ እያዘጋጀን ያለነው ሙሉ ለሙሉ አዲስ ቡድን ነው፡፡ ይህንን ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጀምሮ ማዘጋጀታችንን ጀምረናል፡፡ ከዛም ከቡሩንዲ ጋር ተጫውተናል፡፡ እንዲሁም ከፊታችን ላለብን ጨዋታ ሩዋንዳን በአቋም መለኪያ ጨዋታ ገጥመናል፡፡ አሁን ሀዋሳ እንገኛለን፡፡ ጨዋታው ከባድ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ ቢሆንም ተጫዋቾቻችን የተሻለ አቋም ላይ ይገኛሉ ብዬ አስባለው፡፡

ከታላላቆቹ አል ሂላል እና ኤል ሜሪክ የተመረጡ ተጫዋቾች ቁጥር ማነስ

ይህ ምንም ለውጥ አይደለም ፤ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ሁልግዜም ምርጫችንን መሰረት ያደረገው በሚሆኑ ዝግጁ በሆኑ ተጫዋቾች ላይ ነው፡፡ ከአካል ዝግጁነት አንፃር ብሄራዊ ቡድን ላይ አይደለም ተጫዋቾች በዚህ ረገድ ዝግጅት የሚጀምሩት ስለዚህም የተሻሉ የምንላቸውን መርጠናል፡፡ ስለዚህም በሊጉ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተጫዋቾችን ይዘናል፤ ከዚህ በፊት በነበረው ጨዋታም ጥሩ ነበሩ፡፡ እኛ ትኩረት ያደረግው አዲስ ቡድን መገንባት ላይ ነው፡፡ የዚህ ቡድን አማካይ እድሜ 23 ዓመት ነው፡፡ አብዛኞቹ ከኦሎምፒክ (ከ23 ዓመታ በታች) ቡድናችን ነው የመጡት፡፡

የሱዳን ብሄራዊ ቡድን በማጣሪያ ጨዋታዎች እያሳየ ስለሚገኘው ደካማ አቋም እና ወቅታዊ የሃገሪቱ እግርኳስ ሁኔታ

በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ አሁን ላይ አንድ ጨዋታ ብቻ የተጫወትነው፡፡ 24 ቡድን ስለሚሳተፍ እድላችን ሰፊ ነው፡፡ አሁን ላይ ከዚህ በፊት ከነበሩት ቡድኖች እየተሻልን ነው፡፡ ማዳጋስካርን በምንገጥምበት ወቅት ከፊፋ ቅጣት ጋር በተያያዘም ከፍተኛ ችግሮች ነበሩብን፡፡ ተጫዋቾችን ለመሰብሰብ እራሱ ችግሮችን ማለፍ ነበረብን፡፡ ለማዳጋስካሩ ጨዋታ ሁለት የልምምድ ግዜያት ብቻ ነበሩን፡፡ ከእግርኳስ ፍልስፍና አንፃር አዲስ ቡድን ይዘህ ሁለት የልምምድ ግዜያት ማለት ምን እንደሆነ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ የአቋም መለኪያ ጨዋታም አላደረግንም ግን ይህንን ችግር እንቀበላለን፡፡ አሁን ላይ የቡድኑ ዝግጅት የተሳካ እንዲሆን የሚሰራ ኮሚቴ አለ፡፡ አሁን በፊፋ ያለን ደረጃ በጣም መጥፎ ነው፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ በዚህ ስራ ላይ ነኝ ግን በነዚህ አመታት ውስጥ እምብዛም የአቋም መለኪያ ጨዋታ አላደረግንም፡፡ አሁን ጥሩ ቡድን አለን፡፡ ሊጉም ጥሩ እየሆነ ነው፡፡ ሁለቱ ታላላቅ ክለቦቻችን (ሂላል እና ሜሪክ) እራሱ በሊጉ እየተፈተኑ ነው፡፡ አዳዲስ ተፎካካሪ ቡድኖች እየመጡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከኮንፌድሬሽን ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ ላይ ከቲፒ ማዜምቤ የሚጫወተው ሂላል ኦባያድን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከዚሁ ቡድን 6 ተጫዋቾችን ይዘናል፡፡ ይህ ለሃገሪቱ እግርኳስ አዲስ ነው፤ ከሜሪክ እና ሂላል ውጪ ያለ ቡድን ብዙ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን ሲያስመርጥ፡፡ ሂላል እና ሜሪክ ሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ብቻ ያስመረጡት፡፡ ሃገራችን በችሎታ በኩል ምንግዜም አትሰቃይም፡፡ መጫወት የሚችሉ ልጆች አሉን፡፡ ችግሩ ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የፋይናንስ አቅም ሊኖርህ ይገባል፡፡

ለረጅም ግዜ በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ስለመቆየታቸው

ከዚህ በፊት የነበራችሁ አሰልጣኝ (ሰውነት ቢሻው) ጥሩ ነገሮችን ሲሰራ ነበር በተመሳሳይም ረዘም ላለ ግዜ ቆይቷል፡፡ ጥሩ ጓደኛሞች ነን፡፡ በሃገራችን ጥሩ የሆነ የእግርኳስ አሰልጣኝ ካለ ረጅም ግዜ መስራት ይችላል፡፡ ይህ ምንም ሚስጥር አይደለም፡፡ ልምድ አለኝ እንዲሁም በምመርጣቸው ተጫዋቾች በአብዛኛው ደጋፊው ከእኔ ጋር ይስማማል፤ በምርጫ ላይም አልቸገርም በዚህ ላይ ይህ ሃገር በሜሪክ እና ሂላል ባላንጣናት የተከፈለ ሃገር በመሆኑ ሁልግዜም ቴክቲካል የሆኑ አስተያየቶችን የሚሰጡ በርካታ ደጋፊዎች ያሉበት ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ረጅም ግዜ ለመቆየት ጠንካራ መሆንን ይፈልጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *