ለፋሲል ከተማ የፈረሙት የውጪ ዜጋ ተጫዋቾች…

ፋሲል ከተማ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሚፈቅደውን የውጭ ተጫዋቾች የቁጥር ገደብ በመጠቀም 5 የናይጄርያ ፣ ማሊ እና ዩጋንዳ ዜጌነት ያላቸው ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

ፊሊፕ ዳውዚ

ፊሊፕ ዘንድሮ ለክለቡ ከፈረሙት የውጭ ተጫዋቾች መካከል ቀዳሚው ነው፡፡ በ2003 ለኢትዮ ኤሌክትሪክ በመፈረም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፊሊፕ እስከ 2008 የውድድር ዘመን ድረስ በኤሌክትሪክ ፣ ደደቢት እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካሳለፈ በኋላ ወደ ኩዌቱ አልናስር እና አልሻባብ አምርቶ ካሳለፈ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለፋሲል ከተማ ፈርሟል፡፡ ፊሊፕ በ2007 የውድድር ዘመን 16 ግቦች ያስቆጠረበት አመት በሊጉ ያሳለፈው ምርጡ ጊዜው ነው፡፡

ንቲጄ ሚኬል ሳማኬ

የማሊ ዜግነት ያለው ግብ ጠባቂው ሳማኬ ላለፉት ሳምንታት የሙከራ ጊዜ አሳልፎ ክለቡን በማሳመኑ ፈርሟል፡፡ ሳማኬ በ2015 በሴኔጋል አስተናጋጅነት በተደረገው የአፍሪካ ከ23 አመት በታች ቻምፒዮንሺፕ በተጠባባቂ ግብ ጠባቂነት ወደ ስፍራው አምርቶ ነበር፡፡ ወደ ፋሲል ከመምጣቱ በፊትም በሀገሩ ክለብ ስፖርቲቭ ዱጉዎሎፊላ አሳልፏል፡፡

ያስር ሙገርዋ

ዩጋንዳዊው አማካይ በ2009 ቅዱስ ጊዮርጊስን ተቀላቅሎ እምብዛም የመሰለፍ እድል ባያገኝም በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች መልካም እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ቀሪ የአንድ አመት ኮንትራት የነበረው ያስር በክረምቱ ለወላይታ ድቻ ለመፈረም ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም የውል ማፍረሻውን ሳይከፍል በመቆየቱ ሳይሳካ ቀርቶ በመጨረሻም ለፋሲል ከተማ ፊርማውን አኑሯል፡፡ ያስር በሀገሩ ክለብ ዩጋንዳ ሬቨኑ አውቶሪቲስ እና በደቡብ አፍሪካው ኦርላንዶ ፓያሬትስ እንዲሁም ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል፡፡

ሮበርት ሴንቶንጎ

ለበርካታ ክለቦች የተጫወተው ሮበርት ሴንቶንጎ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የሙከራ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ማረፊያውን ፋሲል ከተማ አድርጓል፡፡ የቀድሞው የሲንባ ፣ ዩጋንዳ ሬቨኑ አውቶሪቲ ፣ ቪላ እና ኬሲሲኤ አጥቂ በ2006 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርቶ ያልተሳካ የአጭር ጊዜ ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ሀገሩ በመመለስ ለዩጋንዳ ሬቨኑ አውቶሪቲ እና ኬሲሲኤ ተጫውቷል፡፡ ለዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድንም 38 ጨዋታዎች አድርጓል፡፡

ክሪስቶፈር አሞስ ኦቢ

ናይጄርያዊው አጥቂ አሞስ ኦቢ በክለቡ የሙከራ እድል ተሰጥቶት የፈረመ ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ ሆኖም የተጫዋቹን ፕሮፋይል ለማግኘትም ሆነ ከፋሲል ከተማ ስለተጫዋቹ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *