ቻምፒየንስ ሊግ፡ አል አሃሊ በሰፊ ግብ ልዩነት በማሸነፍ ለፍፃሜ ደርሷል

አል አሃሊ በአህጉሪቱ እግርኳስ አሁንም ሃያሉ ክለብ እንደሆነ ያስመሰከረበትን ድል ኤትዋል ደ ሳህል ላይ አስመዝግቧል፡፡ አሃሊ ከቱኒዚያ ሃያላን ክለቦች መካከል የሚመደበው ኤትዋልን 6-2 በሆነ ሰፊ ውጤት በመርታት ከ2013 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ መቅረብ ሲችል በፍፃሜው የሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካን የሚገጥም ይሆናል፡፡

በርካታ ግቦች፣ ፈጣን እንቅስቃሴ፣ የባለሜዳዎቹ ደጋፊዎች ድንቅ ድባብን ባሳየን የቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም ጨዋታ አሃሊ ገና ጨዋታው በተጀመረ በሁለተኛው ደቂቃ ቱኒዚያዊው ኢንተርናሽናል አሊ ማሎል ከቀኝ መስመር አከባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት ወደ ግብ መቶ የኤትዋሉ ግብ ጠባቂ አይመን ማትሎቲ ስህተት ታክሎበት ባስቆጠረው ግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል፡፡ አሃሊዎች በተጋጣሚያቸው ላይ ከፍተኛ ጫናን በማሳደር በሞሮኮ ተወላጁ ዋሊድ አዛሮ ሁለት የግንባር ኳሶች 3-0 በመምራት ነበር የመጀመሪያ አጋማሹን ማገባደድ የቻሉት፡፡

ከእረፍት መልስ አዛሮ ሐት-ትሪክ የሰራበትን ግብ በ48ኛው ደቂቃ ሲያስገኝ ራሚ ቤዱኢ ለኤትዋል በማስቆጠር ልዩነቱን ወደ 3 አጥብቧል፡፡ በዚህ ግብ የተነቃቃቱን ኤትዋሎች ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም በመልሶ ማጥቃት አልቀመስ ያሉት አሃሊዎች በማጥቃት ሽግግር ላይ ይበልጥ ጠንክረው ታይተዋል፡፡ ዋሊድ ሱሌማንን ለማስጣል ጥረት ያደረገው የኤትዋሉ ሃምዲ ናጉዝ በስህተት በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮ ውጤቱ 5-1 ሲያደርስ ተከላካዩ ራሚ ራቢያ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ በግሩም ሁኔታ የግብ መጠኑን ግማሽ ደርዘን አድርሶታል፡፡ ኤሃብ ሳክኒ በ90ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ሻሪፍ ኤክራሚ መረብ ላይ አርፋ ጨዋታው 6-2 ተጠናቋል፡፡

አል አሃሊ በመጀመሪያው ጨዋታ ሶስ ላይ 2-1 ቢሸነፍም በመልሱ በግብ ተንብሽብሾ በቀላሉ ለፍፃሜ ቀርቧል፡፡ አሃሊ ሁለት ኃያላን የቱኒዚያ ክለቦች የሆኑት ኤስፔራንስ እና ኤትዋል ደ ሳህልን ከውድድር በማስወጣት አሁንም ጠንካራነቱን አስመስክሯል፡፡ አል አሃሊ በ2013 የቻምፒየንስ ሊጉን ካነሳ በኃላ በውድድሩ ላይ ስኬትን ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ቢሆንም ክለቡ በየሶስት አመቱ ለአህጉሪቱ የክለቦች ውድድር ፍፃሜ ከመድረሱ ባሻገር ዋንጫ ማንሳትም ችሏል፡፡ በ2014 የኮንፌድሬሽን ዋንጫ ባለቤት የሆነው የ8 ግዜ አፍሪካ ቻምፒዮን በካፍ የምዕተአመቱ ምርጥ የአፍሪካ ክለብ ተብሎ መመረጡ ይታወቃል፡፡

ለቱኒዚያ ክለቦች መጥፎ ሆኖ ባለፈው ሳምንት ኤትዋል ደ ሳህል በደረሰበት ከባድ ሽንፈት ምክንያት በክለቡ አሰልጣኝ ላይ እርምጃ መውሰዱ የማይቀር ይመስላል፡፡

በፍፃሜው ዋይዳድ እና አል አሃሊ በሚቀጥለው ሳምንት ሲገናኙ የመጀመሪያው ጨዋታ በአሃሊ ሜዳ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ክለቦቹ ከምድብ አራት ተያይዘው ያለፉ ሲሆን በምድብ ላይ ባደረጓቸው የእርስ በእርስ ግንኙነቶች አንድ አንድ ግዜ መሸናነፍ ችለዋል፡፡

የግማሽ ፍፃሜ ውጤቶች

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 3-1 ዩኤስኤም አልጀር (0-0)

አል አሃሊ 6-2 ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (7-4)

ፍፃሜ

አል አሃሊ (ግብፅ) ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *