​የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ተገባደዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዝዮን 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከእሁድ ጀምሮ ሲካሄዱ ቆይተው ዛሬ ተገባደዋል። ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ እና ኢትዮጵያ ቡና በምርጥ አጀማመራቸው ሲቀጥሉ አርባምንጭ፣ ቂርቆስ ፣ ቦሌ እና ልደታ ከሜዳቸው ውጭ ጣፋጭ  ድል አስመዝግበዋል።

እሁድ እለት ወደ ሻሸመኔ ያቀናው ልደታ ክፍለ ከተማ አዲስ መጪው ሻሸመኔ ከተማን 2-1 በማሸነፍ በድል ተመልሷል። በቀጣዩ እለት ጎንደር ላይ በአፄ ፋሲል ስቴዲየም አዲስ መጪዎቹ ፋሲል ከተማዎች አሁንም በሰፊ የግብ ልዩነት መሸነፋቸውን ቀጥለውበት በሜዳቸው በቦሌ ክ/ከ  የ4-1 ሽንፈት አስተናግደዋል።

ማክሰኞ ከሸገር ደርቢ አስቀድሞ 08:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም በበርካታ ተመልካች ፊት የተደረገው የኢትዮዽያ ቡና እና አአ ከተማ ጨዋታ ኢትዮዽያ ቡና ከእረፍት በፊት በተቆጠረ ብቸኛ ጎል ታግዞ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ትላንት በአአ ስታድየም በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች በርከት ያሉ ጎሎች ሲመዘገቡ በጨዋታም እንቅስቃሴ ጠንካራ ፉክክር መመልከት ችለናል። 09:00 በተደረገው ጨዋታ እንግዳው አርባምንጭ ከተማ ከጨዋታ ብልጫ ጋር አቃቂ ቃሊቲን 5-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ሲያሸንፍ 11:00 ላይ ቀጥሎ በተካሄደውና ጠንካራ ፉክክር በተስተናገደበት የንፋስ ስልክ እና ቅ/ማርያም ጨዋታ ዋና አሰልጣኙን በአራት ጨዋታ እገዳ ምክንያት ያጣው ቅ/ማርያም 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። 

ዛሬ በአአ እና ባህርዳር ላይ በተመሳሳይ 09:00 ላይ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ያልተጠበቀ ውጤት ተመዝግቧል። በባህርዳር አለማቀፍ ስታድም ጥረት ኮርፖሬት ቂርቆስ ክ/ከተማን አስተናግዶ ባልተጠበቀ ሁኔታ 1-0 ተሸንፏል። ውጤቱ ሶስት ተከታታይ ድል አስመዝግቦ ለነበረው ጥረት በውድድር አመቱ የመጀመርያ ሽንፈት ሆኗል። አአ ላይ በተካሄደው የኢትዮዽያ ወጣቶች አካዳሚ እና ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ጨዋታ ድራማዊ በሆነ መልኩ ሲጠናቀቅ በመጨረሻው ደቂቃ ጥሩነሽ ዲባባዎች ያገኙትን ፍ/ቅ /ምት ተጠቅመው 3-2 ማሸነፍ ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ሁሉንም ጨዋታ ያሸነፈው ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ለብቻው መሪነቱን መያዝ ችሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *