የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን መልቀቂያ ተቀብሏል

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለሁለተኛ ጊዜ ያስገቡትን የልቀቁኝ ጥያቄ በቅድመ ሁኔታ መቀበሉ ታውቋል፡፡

ፌድሬሽኑ ዛሬ በፅህፈት ቤቱ ከ5፡30 ጀምሮ ባደረገው ስብሰባ የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው ከግንቦት 2009 ጀምሮ ሲሰሩ የቆዩትን የአሸናፊ በቀለን ውል ለማፍረስ ተስማምቷል፡፡ ሆኖም የፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት አቶ ጁኒየዲ ባሻ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት አሰልጣኝ አሸናፊ ስለብሄራዊ ቡድኑ ሪፖርት ካቀረበ በኃላ ውሉ ሙሉ በሙሉ የሚፈርስ ይሆናል፡፡ ይህም በቀጣዮቹ ሁለት እና ሶስት ቀናት ውስጥ አሰልጣኝ አሸናፊ ሪፖርቱን ካቀረበ በኃላ ተፈፃሚ የሚሆን ይሆናል፡፡ ይህንን ተከትሎ አሰልጣኝ አሸናፊ የኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስራቸውን ከውሉ መፍረስ በኃላ መጀመር ይችላሉ፡፡

ካፍ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማራዘሙን ተከትሎ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከሴራ ሊዮን ጋር የሚያደርገው ጨዋታ በ2010 መጨረሻ የሚደረግ ይሆናል፡፡ ጥር 5 የፌድሬሽኑ ምርጫ የሚካሄድ በመሆኑ አሁን ላይ ፌዴሬሽኑ አዲስ አሰልጣኝ እንደማይሾም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከምርጫው በኃላ ኢትዮጵያ በአምስት አመታት ውስጥ አምስተኛው የዋሊያዎቹ አለቃን እንደምትቀጥር ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *