​ሪፖርት | ወልዋሎና ወልዲያ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል 

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 10ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር አዲስአበባ ስታዲየም ላይ ወልዋሎ ዓ.ዩ እና ወልዲያ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ወልዋሎ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ጅማ አቅንቶ በጅማ አባጅፋር 3-0 ከተረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ ተከላካዩ ሮቤል ግርማን በተከላካይ አማካዩ ብርሃኑ አሻሞ ፣  በጉዳት በዛሬው ጨዋታ ላይ ያልነበረው አጥቂውን ሙሉአለም ጥላሁንን በእዮብ ወልደማርያም እንዲሁም ግብጠባቂው በረከት አማረን በዘውዱ መስፍን በመተካት በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርጽ ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡  በአንጻሩ ወልዲያ ባሳለፍነው ሳምንት በሜዳው አርባምንጭ ከተማን 2-0 ከረታው የቡድን ስብስብ ውስጥ በተመሳሳይ የ4-3-3 ቅርፅ የፊት አጥቂውን አንዱአለም ንጉሴን ብቻ በኤደሞ ኮድዞ በመተካት ጨዋታውን ጀምረዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፍፁም የሆነ የኳስ ቁጥጥር እንዲሁም ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ሙከራዎችን የማድረግ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ወልዋሎዎች የመጀመሪያ አስደንጋጭ ሙከራቸውን ለማድረግ የፈጀባቸው 3 ደቂቃዎች ነበሩ። የመስመር አጥቂው ከድር ሳሊህ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የተገኘችውን ኳስ 2 የወልዲያ ተከላካዮች ለ4 የወልዋሎ ተጫዋቾች ሆነው ያገኘውን አጋጣሚ በቀላሉ ለቤሌንጌ ያሳቀፈው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸው ነበረች፡፡

የወልዋሎዎች ጠንካራ የማጥቃት አማራጭ በሆነውና የመስመር አጥቂው ፕሪንስ ሴቪሪንሆ ዋንኛ ተዋናይ በሆነበት የወልዋሎዎች የቀኝ መስመር በኩል ባጋደለ መልኩ ጥቃቶችን በተደጋጋሚ ሲሰነዝሩ የነበሩ ሲሆን በተለይም በ10ኛውና በ14ኛው ደቂቃ ፕሪንስ ከቀኝ መስመር አደገኛ ኳሶችን ወደ ሳጥን ውስጥ ቢጥልም እዮብ ወልደማርያም ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል፡፡

የወልዲያ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች እንዲሁም ከተከላካይ አማካዩ ዳንኤል ደምሴ ፊት የነበሩት ሁለቱ አማካዮች ቡድኑ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚያደርገው ሽግግር ላይ ያላቸው እጅግ ዘገምተኛ  ሽግግር የወልዲያን የተከላካይ ክፍል በእጅጉ ተጋላጭ ሆኖ ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ በወልዋሎዎች በኩል እንደወትሮው ሁሉ ጠበብ ባለ የቦታ አያያዝ የሚጫወቱት ሶስቱ አማካዮች እንዲሁም ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በወልዲያ የተከላካይና የአማካይ መስመሮች መካከል የነበሩትን እጅግ ሰፋፊ ክፍተቶችን በጥቂት አጋጣሚዎች እዮብ ተጎድቶ እስኪወጣ ድረስ ካደረጋቸው የተወሰኑ ጥረቶች በስተቀር በአግባቡ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡

ፈጥን ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደተጋጣሚያቸው የግብ ክልል መድረሳቸውን የቀጠሉት ወልዋሎዎች በደቂቃዎች ልዩነት አከታትለው አስደንጋጭ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በ24ኛው ደቂቃ መኩሪያ ደሱ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ወደ ግብ የላካት በወልዲያው የመሀል ተከላካይ ስትመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው አፍወርቅ ሀይሉ በድጋሚ ወደ ግብ የላካት ኳስ በሚያስገርም ሁኔታ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ከአንድ ደቂቃ በኃላ ደግሞ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው ለመከላካል ሲሞክሩ የነበሩት የወልዲያ ተከላካዮች ባልተደራጁበት ሁኔታ በቀጥታ ከተከላካዮች የተላከውን ኳስ ተጠቅሞ እዮብ ወልደማርያም ከኤሚክሬል ቤሊንጌ ጋር 1ለ1 ተገናኝቶ በግብ ጠባቂው አናት በላይ ለማስቆጠር የሞከረውን ኳስ ቤሌንጌ ለጥቂት አድኖበታል፡፡ ከዚች ሙከራ በኃላ ጉዳት ያስተናገደ የሚመስለው አጥቂው እዮብ ወልደማርያም በ28ኛው ደቂቃ ላይ በቢኒያም አየለ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡ እዮብ ከወጣበት ደቂቃ አንስቶም ወልዋሎዎች ወደ ማጥቃት ሂደት ሲገቡ የነበራቸው አስፈሪነት ቀንሶ ተስተውሏል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ በመከላከሉም በማጥቃቱም ረገድ ይህ ነው የሚባል ጠንካራ ጎን ያልነበራቸው ወልዲያዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ኢላማውን የጠበቀም ሆነ ያልጠበቀ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ይልቁንም በ36ኛው ደቂቃ የቀኝ መስመር ተከላካዩ ታደለ ምህረቴ ባጋጠመው ጉዳት በብርሃኔ አንለይ ተቀይሮ ከሜዳ ለመውጣት ተገዷል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ወልዲያ ከተማዎች ከጉዳት ጋር ጨዋታውን የጀመረውን አንበላቸውን አዳሙ መሀመድን አስወጥተው ሌላኛውን ከጉዳት የተመለሰውን ተስፋዬ አለባቸውን ማስገባት ችለዋል ፤ በዚህም ቅያሬ የተነሳ በመጀመሪያው አጋማሽ የተከላካይ አማካይ የነበረው  ዳንኤል ደምሴ ወደ መሀል ተከላካይ ስፍራ ሲሸጋሸግ ተቀይሮ የገባው ተስፋዬ አለባቸው በተከላካይ አማካይ ስፍራ መጫወት ችሏል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ወልዋሎ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በቀኝ መስመራቸው ባደላ መልኩ ተደጋጋሚ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቢቀጥሉም የወልዲያው ግብ ጠባቂ የሚቀመስ አልሆነም፡፡ በተለይም በ53ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ አለባቸው ለቡድን አጋሮቹ ለማቀበል አስቦ የተሳሳተውን ኳስ አልሳሪ አልመሀዲ አግኝቶ የወልዲያው ግብ ጠባቂ የግብ ክልሉን ለቆ መውጣቱን በመመልከት በቀጥታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ እንደምንም ቤሌንጌ አድኖበታህ።

ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በተሻለ ቁመና ወደ ሜዳ የገቡት ወልዲያዎች በ54ኛው ደቂቃ ምንያህል ተሾመ በራሱ የሜዳ አጋማሽ የነጠቀውንና ፊት ላይ ብቻውን ለነበረው ፍፁም ገ/ማርያም ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ ፍፁም በቀላሉ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ በቅርብ ርቀት የነበረው የወልዋሎ ተከላካይ የነጠቀው ኳስ ጥሩ ማሳያ ነበረች፡፡

በርከት ያለ የተጫዋቾች ጉዳት በታየበት የሁለቱ ቡድኖች የዛሬ ጨዋታ የወልዋሎው የመሀል ተከላካይ ኤፍሬም ጌታቸው ተጎድቶ በሮቤል ግርማ ለመተካት ተገዷል። በዚህም ቅያሬ መሠረት በመጀመሪያው አጋማሽ በመስመር ተከላካይት ሲጫወት የነበረው ተስፋዬ ዲባባ ወደ ቀድሞው ቦታው ሲመለስ ሮቤል ግርማ በግራ መስመር ተከላካይነት የቀሩት ደቂቃዎች መጫወት ችሏል፡፡ የሮቤል ግርማ ተቀይሮ መግባት ወልዋሎዎች በመጀመሪያው አጋማሽ በቀኝና በግራ የመስመር ተከላካይነት ሲጠቀሙባቸው የነበሩት አልሳሪ አልመሀዲና ተስፋዬ ዲባባ ተፈጥሮአዊ የመስመር ተከላካይ ባህሪን ያልተላበሱ በመሆናቸው ኳስ በሚቀበሉበት ወቅት ከፊት ለፊታቸው የሚገኙ ሰፋፊ ክፍተቶችን ለመጠቀም ያላቸው ተነሳሽነት አነስተኛ በመሆኑ የተነሳ ቡድኑ በማጥቃት ሂደት ውስጥ በሚገኝበት ጊዜ ቅርፁ ጠባብ እንዲሆን ሲገደድ ነበር። ነገርግን ሮቤል ተቀይሮ ከገባ ወዲህ ይህ ችግር በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ ነበር ለማለት ያስችላል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ወልዲያዎች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አደጋ ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በተለይም በ70ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ወልዋሎ የግብ ክልል ከደረሱ በኃላ ያሬድ ብርሃኑ አመቻችቶ ያቀበለውን ያለቀለት ኳስ ፍፁም ገብረማርያም ከግቡ ጥቂት ሜትር ርቀት ላይ እጅግ ለማመን በሚከብድ ሁኔታ ለዘውዱ መስፍን ያሳቀፈው ኳስ በወልዲያዎች በኩል በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበር፡፡

በ77ኛው ደቂቃ የወልዋሎው አማካይ አፈወርቅ ሀይሉ ባጋጠመው ጉዳት በአብዱራህማን ፎሴይኒ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ፤ ይህም በጨዋታው ሶስተኛ በጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ ከሜዳ የወጣ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ከዚህ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች ወልዋሎዎች በመጠኑ ወደ ኃላ አፈግፍገው የአቻ ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ መከላከልን ሲመርጡ በአንጻሩ ወልዲያዎች በተሻጋሪ ኳሶች ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው ያለ ጎል አቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ወልዋሎ በ12 ነጥብ በነበሩበት 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ በአንጻሩ ወልዲያዎች ነጥባቸውን ወደ 10 ከፍ በማድረግ ወደ 11ኛ ደረጃ ከፍ ብለው መቀመጥ ችለዋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔር – ወልዋሎ

“ምንም እንኳን ግብ ማስቆጠር ባንችልም ሜዳ ላይ ተጫዋቾቼ ኳስን ተቆጣጥረው ለመጫወት ባደረጉት ጥረት ግን በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ የቡድናችን እንቅስቃሴ እየተሻሻለ መጥቷል ፤ ለዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የደጋፊዎቻችን ቁጥር ምስክር ይሆናል፡፡”

ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ – ወልዲያ ከተማ

“በጨዋታው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ወልዋሎዎች ከኛ በተሻለ በስሜትና በፍላጎት ይጫወቱ ስለነበር የተሻሉ ነበሩ፤ በሁለተኛው አጋማሽ እኛም ይህን ተመልክተን ብልሀት በታከለበት መልኩ መጫወታችን በሁለተኛው አጋማሽ የበላይ ሆነን ለመጫወት አብቅቶናል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *