የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 1-0 ያንግ አፍሪካንስ

የኢትዮጵያው ወላይታ ድቻ የታንዛኒያውን ያንግ አፍሪካንስን 1-0 ዛሬ በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ ቢያሸንፍም በአጠቃላይ ውጤት 2-1 ተሸንፎ የመጀመሪያ ተሳትፎ ካደረገበት ውድድር ተሰናብቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ክለብ አሰልጣኞች አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

“ጥቃቅን ስህተቶች እና ልምድ ማነስ ነው ከውድድር ያስወጣን” የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ

“ለማሸነፍ ገብተናል፡፡ ከሞላ ጎደል እንቅስቃሴው ጥሩ ነው ምንም አይልም፡፡ በተሻለ መከላከል ላይ ተጠናክረው መጥተዋል፡፡ እኛም ደግሞ ይህንን ለማፍረስ በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ጥረት አድርገን ነበር፤ ይህም ተሳክቶልን ግብ አስቆጥረናል፡፡ ከዛ በኃላም እንግዲህ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ ችለናል፡፡ አልተሳካልንም! ልጆቹ ያደረጉት ተጋድሎ ቀላል አይደለም፡፡ የመጀመሪያችን እንደመሆኑ መጠን የዛሬው እንቅስቃሴ በጣም ጥሩ ነው፡፡”

“እኛ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ነው ከእረፍት በኃላ ተነጋግረን የገባነው፡፡ ለዛም ልጆች በተለየ ተጭነው የተጫወቱት፡፡ ይህ ወደፊት መሳባችን እነሱ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት እኛ ግብ ጋር ለመድረስ ጥረት አድርገዋል፡፡ ማግባት እና ማሸነፍ እንዳለብን አቅደን ስለገባን በዛ ምከንያት ነው እነሱ ሊሞክሩ የቻሉት እንጂ እኛ ወደ ፊት እየተጫንን ተጫውተናል፡፡ ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው፡፡ ልጆቹ ልምድ የሌላቸው ናቸው፡፡”
“እዛ የተቆጠሩብን ግቦች ናቸው ዋጋ ያስከፈሉን፡፡ ሁለቱም ግቦች የተቆጠሩብን በትኩረት ማነስ ነው፡፡ አሁን ደግሞ በዛሬው ላይ ትንሽ ጥሩ ስራ ሰርተናል፡፡ ትንሽ ለውጥ አለው፡፡ ሙሉ ለሙሉ አጥጋቢ አይደለም፡፡ ኳሱን ይዞ መጫወት ደረጃ ዛሬ ትንሽ ዝቅ ብለናል፡፡ ከዚህ ውድድር ወጥተናል፡፡ ለፕሪምየር ሊጉ አሻሽለን ተዘጋጅተን እንመጣለን፡፡”

“እዚህ በመድረሴ ደስ ቢለኝም ከዚህ በላይ መሄድ እንዳለብን አውቅ ነበር፡፡ ልጆቹ አቅም ስላላቸው እንችል ነበር፡፡ ጥቃቅን ስህተቶች እና ልምድ ማነስ ነው ከውድድር ያስወጣን፡፡”

“ማለፋችን እድለኛ ያስብለናል” የያንግ አፍሪካንስ ግዜያዊ ዋና አሰልጣን ሻድራክ ንሳጂግዋ

“ጨዋታው ለእኛ ጠንካራ ነበር ምክንያቱም ድቻዎች በሃይለኛ ጫና እና ፍጥነት ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስቆጠሩ ከዛም ደቂቃው ሲገፋ ጫናው እየቀነሰ እየቀነሰ ነበር የመጣው፡፡ በሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ ከፍተኛ ጫናን ለማድረስ ሞክረዋል፡፡ ሆኖም ጥሩ ጨዋታ እና ተመጣጣኝ ነበር፡፡ በውጤቱ ደስተኛ ነኝ፡፡”

“ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡ እኛ የፈጠርነውን እድል ከድቻ ጋር ቢነፃፀር የእኛ የተሻለ ነበር፡፡ ማለፋችን እድለኛ ያስብለናል፡፡ የፈጠርናቸውን እድሎች ግን መጠቀም ላይ ችግሮች ነበሩ፡፡ ይህንንም በቀጣይ ጨዋታዎች እናስተካክላለን፡፡”
“በቤተሰብ ውስጥ አባት ሲለይ ማንም ደስተኛ አይሆንም፡፡ ጆርጅ ሉዋንዲማና ከእኛ ቢለቅም ይህንን ውጤት ሲያይ በጣም እንደሚደሰት አልጠራጠርም፡፡ እንዲያውም ከእኛ በላይ እሱ በጣም እንደሚደሰት አስባለው፡፡ የሊግ ዋንጫ ክብራችንንም ለመድገም ጥሩ የሞራል መነሻሻ የሚሆን ውጤት ነው ያገኘነው፡፡”

“ሙዋንጂ ሃጂ (የግራ ተከላካዩ) የቀየርነው የማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከቱ እና የታክቲክ ለውጥ በማስፈለጉ ነው፡፡ ድቻዎ ረጃጅም ኳሶችን ሲጠቀሙ ስነበር ሃጂ ሰፊ ክፍተቶችን እየተወ ነበር፡፡ ይህንን ማረም ስለነበረብን ለውጡን አድርገነዋል፡፡ ታባኒ ካሙሶኮ እና ፓፒ ቲሺሺምቢ ጉዳት ስላገጠማቸው ነው የቀየርናቸው፡፡”