” ሰው ጨዋታዬን ተመልክቶ ምክር ሲለግሰኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ ” እዮብ አለማየሁ

ከወላይታ ሶዶ ከተማ 17 ኪሜ ርቃ ከምትገኝ ጉኑኖ በተባለች ወረዳ ነው የተወለደው። ቤተሰቡ ውስጥ ሌላ እግር ኳስን ተጫውቶ ያለፈ ሰው እንደሌለ የሚናገረው እዮብ ለቤቱ ሁለተኛ ልጅ ነው።  እግርኳስን በዚህችው ትውልድ መንደሩ መጫወት ከጀመረ በኃላ 2007 ላይ በቦዲቲ ከተማ የተዘጋጀ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ቢሞክርም ውድድሩን የሚያዘጋጁት ኮሚቴዎች ፣ ደጋፊዎች እና ዳኞች እድሜው ዝቅተኛ ነው በማለት ሳይፈቅዱለት ቀሩ። ሆኖም በዚህ ሰዐት ያሁኑ የወላይታ ድቻ ዋና አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሀ ያኔ ያሰለጥንበት ወደነበረው የወላይታ ድቻ ከ17 አመት በታች ቡድንን እንዲቀላቀል አደረገ። ለአንድ አመት ያህልም እዮብ ያለ ምንም ደሞዝ ከሶዶ ከተማ ወደ ጉኑኖ እየተመላለሰ ሲጫወት ቆይቷል። 

በ2008 ለወላይታ ድቻ ከ17 አመት በታች ቡድን እየተጫወተ በነበረበት ወቅትም  በአሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ አማካኝነት ለኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ በሁሉም ማጣርያ ጨዋታዎች ላይ በቋሚነት መሰለፍ ቻለ። 

አጋጣሚው በፈጠረለት መነሳሳት ፈጣን እድገቱን የቀጠለው እዮብ በቀጣዩ የውድድር አመት ደግሞ በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ዝግጅት የጀመረ ቢሆንም ዕድሜው ገና ስለነበር ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እየሰራ በ17 አመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለወላይታ ድቻ መጫወት አለበት በመባሉ ተመልሶ ለ17 አመት በታች ቡድኑ መጫወት ነበረበት። በወቅቱ አዳማ ላይ የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ያነሳው ቡድን አባልም ነበር።


ፕሮፋይል

ሙሉ ስም – እዮብ አለማየሁ አላምቦ 

የትውልድ ዘመን – 1992

ቁመት – 1.78 ሜትር 

ክብደት –  60 ኪግ

የሚጫወትበት ቦታ – አማካይ

ክለብ – ወላይታ ድቻ 


በያዝነው የውድድር አመት ለመጀመሪያው ቡድን መጫወት የጀመረው እዮብ አንደኛው ዙር ላይ ብዙም የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል ማግኘት አልቻለም ነበር። በሁለተኛው ዙር ግን የመጫወት ዕድል ከማግኘት ባለፈ ግቦችንም እያስቆጠረ ይገኛል። በወላይታ ድቻ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ ከዛማሊክ እና ያንግ አፍሪካንስ ጋር በነበሩት የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ የቻለው የመስመር አማካዩ አዲስ አበባ ስታድየም በነበረው ጨዋታ በቡሩንዲ 2-0 የተሸነፈው የ20 አመት በታች ብሔራዊ ተሰላፊም ነበር። እዮብ በመጨረሻ የሊግ ጨዋታው ክለቡ ፋሲል ከተማን 3-0 ሲያሸንፍ ሐት-ትሪክ ስለመስራቱ እና ዘንድሮ ስላሳየው እድገት ሀሳቡን ሲገልፅ እንዲህ ይላል።            

” ገና በታዳጊ እድሜዬ በሀገር ውስጥም ሆነ በኢንተርናሽናል ውድድሮች ላይ መሳተፌ ለእኔ በጣም ትልቅ ስኬት ነው። ፈጣሪዬ ረድቶኝ እዚህ ደርሻለው። ገና ብዙ የሚቀረኝ እና የሚጎለኝ ነገር አለ። አሁን ልምድ እያገኘው ነው።  ሁሌም የማስበው ነገ ትልቅ ደረጃ መድረስን ነው። ጎል ካላገባው ፣ የተሻለ ነገር መስራት ካልቻልኩ ምን እሰራለው እያልኩ እራሴን ለለውጥ አነሳሳለው። በፋሲል ጨዋታ ላይ ጎል እንደማስቆጥር እርግጠኛ ነበርኩ። እንዳሰብኩት ሆኖልኝ ጎሎችን አስቆጠርኩኝ ፤ በጣም የተለየ ስሜት ነው ውስጤ የፈጠረብኝ። ወደፊትም ጎሎችን በማስቆጠር ክለቤን በሚገባ ማገልገል እፈልጋለው።” 

የሳላዲን ሰዒድ እና የጌታነህ ከበደ አድናቂ የሆነው እዮብ በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን በተለያዩ ቦታዎች ላይ እየተሰለፈ መሆኑ የመጫወቻ ቦታ አማራጩን ስለሚያሰፋለት በበጎ መንገድ እንደሚወስደው ይናገራል። ወጣቱ አማካይ ስለአጠቃላይ የእግር ኳስ ህይወቱ እና ቀጣይ ዕቅዶቹ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል።

” በቀጣይ ጠንክሬ በመስራት የዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መለያ መልበስ እና መጫወትን እፈልጋለው። ብዙ ተአምር መስራት እፈልጋለው ፤ ፈጣሪም ይረዳኛል። አሁን ለደረስኩበት ደረጃ ሁሌም የሰዎችን ምክር መቀበሌ በጣም ረድቶኛል። ሰው ጨዋታ አይቶ ይህን አስተካከክል ብሎ ሲመክረኝ በጣም ነው ደስ የሚለኝ። ከራሴ በላይ የሰውን ነገር መጀመርያ አዳምጣለው ። ሁሌም እራሴን ለማሻሻል የሰዎች ምክር እንደሚያስፈልገኝም አምናለው። እኛ ወጣቶች ትንሽ ነገር ማሰብ የለብንም ትልቅ ነገር ማሰብ ያስፈልጋል ። ይህ የሚሆን ከሆነ ሁሉን ነገር መስራት እንችላለን። የማይቻል ነገር የለም።