ሪፖርት | አዳማ ከተማ ድቻን በማሸነፍ ደረጃውን ወደ ሦስተኛ አሻሽሏል

በ18ኛ ሳምንት መጋቢት 26 ሊደረግ መርሀግብር ወጥቶለት በወላይታ ድቻ በካፍ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታ ምክንያት የተሸጋገረው ጨዋታ ዛሬ በአዳማ አበበ በቂላ ስታድየም 09:00 ላይ ተደርጎ አዳማ ከተማ በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠረ ብቸኛ ጎል ወላይታ ድቻን አሸንፏል።

አዳማ ከተማ በ22ኛው ሳምንት ወደ ጎንደር አቅንቶ ከፋሲል ከተማ ጋር ያለ ጎል ከተጠናቀቀበት ጨዋታ ውስጥ በስብስቡ ግብጠባቂው ጃፋር ደሊልን ከጉዳት በተመለሰው ጃኮ ፔንዜ ሲተካው ተስፋዬ ነጋሽ ፣ ኤፍሬም ዘካርያስ ፣ ጫላ ተሺታ  እና ፍርድአወቅ ሲሳይን በማሳረፍ በምትኩ ምኞት ደበበ ፣ ሱራፌል ዳኛቸው ፣ ቡልቻ ሹራ እና ዳዋ ሆቴሳን በመጠቀም ወደ ሜዳ ገብተዋል። በወላይታ ድቻ በኩች ወደ መቐለ አቅንቶ በመቐለ ከተማ 2-0 በሆነ ውጤት ከተሸነፈበት ስብስቡ ውስጥ ከተጨዋቾች ጋር በፈጠረው ግጭት በዲሰፒሊን ውሳኔ መሰረት ግብጠባቂው ወንድወሰን ገረመውን በአማኑኤል ፌቮ ሲተካ ወንድወሰን ቦጋለ ፣ እዮብ አለማየሁ ፣ ተስፉ ኤልያስ ፣ ውብሸት አለማየሁ እና ጃኮ አራፋትን በማሳረፍ በምትኩ ሙባረኩ ሽኩር ፣ እሸቱ መና ፣ ያሬድ ዳዊት ፣ ታዲዮስ ወልዴ እና ዳግም በቀለን በማካተት ጨዋታውን ጀምረዋል።

ዝቅ ያለ የተመልካች ቁጥር በተከታተለውና ፌዴራል ዳኛ አክሊሉ ድጋፌ በመራው በዚህ ጨዋታ ከጨዋታው አስቀድሞ የአዳማ እግርኳስ ክለብ ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚ እንስጥ የሚል መልዕክት ያየዘ ባነር ተጫዋቾቹን በማስያዝ ለስፖርት ተመልካቹ በማሳየት መልዕክት አስተላልፏል።

በመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል መልካም እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን ጎሎችን ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት ለተመልካች አዝናኝ እና ሳቢ የሚባል እንቅስቃሴ እንዲመለከት አስችሎታል። በ4ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ከነዓን ማርክነህ በግንባሩ በመግጨት ሲያስቆጥር ግብጠባቂው አማኑኤል ፌቮ ቆሞ ከማየት ውጭ ምንም ማድረግ አልቻለም ነበር።

ወላይታ ዲቻዎች ጎሉ ይቆጠርባቸው እንጂ ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት እና ወደፊት በመሄድ ጎል ለማስቆጠር የነበራቸው ጥረት የአዳማ ተከላካዮች ምንም ነፃ የሜዳ ክፍል እንዳያገኙ በማድረጋቸው ሳይሳካ ቀርቷል። በረጅሙ ኳሱን ለብቸኛው አጥቂ ዳግም በቀለ በመጣል ጎል ፍለጋ ጫና ሲፈጥሩም ነበር ። ይህ የማጥቃት ዘዴን አዳማዎችም በተመሳሳይ በመጠቀም ለአጥቂው ዳዋ ሆቴሳ ኳሶችን በረጅሙ በማሻገር የጎል እድል ለመፍጠር ጥረዋል።  12 ኛው ደቂቃ ላይ ወላይታ ድቻ የመጀመርያውን የጎል ሙከራ በበዛብህ መለዮ አማካኝነት አድርጓል። በመልሶ ማጥቃት መሀል ሜዳ ላይ ሁለት የአዳማ ተከላካዮች ብቻ አጋጥመውት ከመሀል ሜዳ ላይ ጀምሮ ኳሱን እየገፋ ወደ ፊት በመሄድ ለዳግም በቀለ የሚሰጥ መስሎ አክርሮ ከሳጥን ውጭ የመታው ኳስ ግብጠባቂው ጃኮ ፔንዜ እንደምንም ያዳነበት ጠንካራው የጎል ሙከራ ነበር።

የጨዋታው ፍሰት ሆነ ኳሱን አደራጅቶ በመጀመር ወደ ማጥቃት ሽግግሩ የሚገቡበት መንገድ መልካም ቢባልም የሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ዞን ውስጥ ሲገቡ በተደጋጋሚ በሚሰሩት ስህተት ጠንካራ የጎል ሙከራ ሳንመለከት ዘልቋል። በ30ኛው ደቂቃ ላይ ዳዋ ሆቴሳ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በጥሩ ሁኔታ በግንባሩ ቢገጨውም ለጥቂት በብረቱ ጠርዝ በመውጣት ጎል ከመሆን ድናለች። በመቀጠልም 38ኛው ደቂቃ ቡልቻ ሹራ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት አክሮ የመታውን ኢማኑኤል ፌቮ እንደምንም በእግሩ ተጠቅሞ ያወጣው ኳስ በአዳማ በኩል ተጠቃሽ የጎል ሙከራ ነበር። ድቻዎች በቀሪው የመጀመርያ አጋማሽ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ጫና የፈጠሩ ሲሆን በሦስት አጋጣሚ አጥቂው ዳግም በቀለ ከበዛብህ መለዮ የተሻገረለትን በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት የወጣበት ፣ ሁለቱን አጋጣሚዎች ደግሞ የተቀበለውን ኳስ ወደ ጎል መቶ ጃኮ ፔንዜ ያዳነበት ግልፅ የጎል አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከእረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች የተሻሉ ሆነው የቀረቡበት ፣ አዳማዎች በአንፃራዊነት ከመጀመርያው አጋማሽ ተዳክመው የቀረቡበት የጨዋታ  ክፍለ ጊዜ ነበር። 53ኛው ደቂቃ አብዱልሰመድ ዓሊ አክርሮ የመታውን ጃኮ ፔንዜ ሲተፋው በዛብህ መለዮ ኳሱን አግኝቶ ወደ ጎልነት ቢቀይረውም ረዳት ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው መሻራቸው ሳይፀድቅ የቀረውና የወላይታ ድቻ ተጨዋቾች እና የቡድኑ አባላት ያላስደሰተ ውሳኔ ነበር።

ድቻዎች ጃኮ አራፋትን በፀጋዬ ባልቻ ፣ ፀጋዬ ብርሃኑን ደግሞ በአብዱሰመድ በመቀየር የማጥቃት ኃይላቸውን ጨምረው ጎል ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም 61ኛው ደቂቃ ላይ ታዲዮስ ወልዴ ከርቀት አክርሮ በመምታት ካደረገው የጎል ሙከራ ሌላ የግብ እድል መፍጠር የቻሉት በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በገባው በዮናታን ከበደ የቅጣት ምት ሙከራ ብቻ ነው።

በሁለተኛው አጋማሽ ተዳክመው ወደ ሜዳ ይግቡ እንጂ ባለሜዳዎቹ  አዳማዎች በዳዋ ሆቴሳ እና በረከት ደስታ አማካኝነት ጠንካራ የጎል አጋጣሚ ቢፈጥሩም ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ የተመለሰው ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል ፌቮ በግል ብቃቱ ኳሱን አድኖባቸዋል። ጨዋታው ወደ መጨረሻ ደቂቃ ላይ በተለያዩ ምክንያቶች እየተቆራረጠ ቀጥሎ ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት ከእረፍት በፊት ከነዓን ማርክነህ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል በአዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድንቅ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ከነዓን በሁለቱ ቡድኖች የመጀመርያ ጨዋታ አዳማ ወደ ሶዶ አቅንቶ 2-1 ባሸነፈበት ጨዋታ ላይም ሁለቱንም ጎሎች ማስቆጠሩ የሚታወስ ነው።

ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ነጥቡን ወደ 36 ከፍ አድርጎ ወደ ደረጃውን ወደ 3ኛ ሲያሻሽል ወላይታ ድቻ በ27 ነጥቦት የነበረበት 10ኛ ደረጃ ላይ ረግቷል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ተገኔ ነጋሽ – አዳማ ከተማ

በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ ተወስዶብን ነበር። ያም ቢሆን የተሻልን በነበርንበት የመጀመርያው አጋማሽ ጎል አስቆጥረናል። በዛም ይሁን በዚህ ሦስት ነጥብ አሳክተን አሸንፈን መውጣት ችለናል ።

ዘነበ ፍስሀ – ወላይታ ድቻ

ጨዋታው ጥሩ ነበር ትንሽ ተቀዛቅዘን በነበርንበት አጋጣሚ ጎል አስተናግደናል። ጎሉ ከተቆጠረብን በኋላ የተሻለ መንቀሳቀስ ብንችልም ጎል ማስቆጠር አልቻልንም። እንዳሳየነው እንቅስቃሴ ውጤቱ አያስከፋም።