የአሰልጣኞች ገጽ – ወርቁ ደርገባ [ክፍል 2]

የአሰልጣኞቻችን የእግርኳስ አስተሳሰብ ፣ የስልጠና ሀሳብ ፣ የስራ ህይወት እና የውጤታማነት መንገድ ዙርያ ትኩረት በሚያደርገው ” የአሰልጣኞች ገጽ ” አምዳችን ካለፈው ሳምንት የቀጠለው የአሰልጣኝ ወርቁ ደርገባን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።

የዛሬው የክፍል ሁለት መሰናዷችን ስለ ምክትል ወይም ረዳት አሰልጣኘነት እናወጋለን። ለቃለ ምልልሱ እንዲያመችም ከ”አንቱ” ይልቅ “አንተ” በሚለው ተጠቅመናል።


 


በሚልኪያስ አበራ እና አብርሀም ገብረማርያም


በኢትዮጵያ እግርኳስ የምክትል አሰልጣኞችን ሐላፊነት እና የሜዳ ላይ ሚና “በተግባር ስልጠና ወቅት የተጫዋቾችን መለማመጃ ስፍራ ወሰን ማሳያ እና የልምምዱን አይነት የሚያመላክቱ መሳሪያዎች (ኮን) ደርዳሪዎች” አድርገን የመመልከት ልማድ ይታያል…

★ በምክትል አሰልጣኞቻችን ላይ የሚኖረን እምነት ከምንሰጣቸው ሐላፊነት ጋር ተያያዥ ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ ገዘፍ ያለ ግምት ስለማንቸራቸው ቀለል ያለውን ስራ ነው የምንሰጣቸው፡፡ ረዳት አሰልጣኞች እኮ ናቸው፤ የግድ የስልጠና ስራ ውስጥ ተሳታፊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ኮኑን በየቦታው ማስቀመጥ የሌላ ሰው ተግባር ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር እኔ በድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ስሰራ ምክትሌ ስምኦን አባይ ነበር፡፡ ስምኦንም እኔም በተጫዋችነት ጊዜያችን አጥቂዎች ነበርን፡፡ እኔ ሌሎች ስራዎችን ሳሰራ – እርሱ ደግሞ የአጥቂ ክፍሉ ላይ ያሉ ልምምዶችን ያሰራ ነበር፡፡ ተመልከቱ- ለእኔ እንዴት ስራዎች እየተቃለሉልኝ እንደሚሄዱ! በረኛውን፣ ተከላካዩን እንዲሁም አማካዩን በዚህ ዘዴ በብቁና በፕሮግራም በሚመራ ሰው ስታሰራ ምክትል አሰልጣኞችም የበለጠ እየተሻሻሉ ይመጣሉ፡፡ “አውቀዋለሁ!” በሚል አምጥተህ <ኮን ማስደርደር>ን እንደ ስራ ከሰጠኸው እንዴት አድርገህ ነው ያን ሁሉ ስራ ብቻህን የምትወጣው? የ Coaching Staff ጥቅሙ ይሄ ነው፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጊዜ የተወሰነ ጥሩ ነገር ታይቷል፤ መልካም የሚባል የድጋፍ ሁኔታም ነበር፡፡ ለወደፊቱ አሰራሩ በሰፊው ቢለመድ ጥሩ ነው፡፡

ምክትል አሰልጣኝ መመረጥ ያለበት ለስራው እንጂ ለዋናው አሰልጣኝ ባለው ቅርበት እና አመቺነት መሆን የለበትም፡፡


ብዙውን ጊዜ ምክትሎቹ ሊሰሩ ከሚችሉት ያነሰ ስራ ሲሰጣቸዉ በ” እሺታ” ይቀበሉታል፡፡ ከዚህ ቀደም አሰልጣኝ ሰውነትን ባነጋገርንበት ወቅት “ከዚህ በኋላ ምክትል ሆኜ አልሰራም፤ በረዳትነት እየተሰጠኝ ያለው ስራ ካለኝ የአቅም ደረጃ እጅጉን የወረደ ነው፤… በማለት <ቻሌንጅ ለማድረግ> እሞክር ነበር፡፡” ብሎናል፡፡ አንተ ምክትል አሰልጣኝ ሆነህ በሰራህባቸው ጊዜያት በሚሰጥህ መጠነኛ ሚና ወይም ሐላፊነት ላይ ጥያቄ ታነሳ ነበር? አቅምህን ለማሳየት የተገዳደርከው ፈተናስ ምን ይመስላል?

★በጣም የሚገርመው ለመጀመሪያ ጊዜ አቶ መንግስቱ ወርቁ ለብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሰልጣኝነት ሲመርጠኝ በጭራሽ አላመንኩም ነበር፡፡ በእርግጥ መንግስቱ ቀደም ብሎ አብዮት ፍሬን ሳሰለጥን ቡድኑን በደምብ አይቶልኛል፡፡ እንዲያውም ጀማሪ በነበርኩ ጊዜ አልፎ አልፎ እየጠራኝ ምክሮችን ይለግሰኝ ነበር፡፡ ጀርመን ሄጄ ከመጣሁ በኋላ በባንኮች ስሰራም ቡድኔን ይከታተል ጀመር፡፡ በ1983 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ ለትምህርት ጀርመን አገር ሄጄ ስመለስ ባላሰብኩት ሰዓት ላይ የመንግስቱ ወርቁ ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ መመረጤን ከሚዲያ ስሰማ ደንግጫለሁ፡፡ በወቅቱ ለእኔ በወጣትነቴ ከአቶ መንግስቱ ጋር በብሔራዊ ቡድን መስራት የማይታሰብ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ቀድሞ ስለ መንግስቱ የሚደርስህ መረጃ ደግሞ “ጋሽ መንግስቱ ኃይለኛ ነው፤ ቁጡ ነው፤ አትችለውም፤ ከእሱ ጋር መስራት ያስቸግርሀል፤…” የሚል በመሆኑ ‘ እኔ እኮ በስራ ነው የማገኘው እንጂ በሌላ ጉዳይ አይደለም፡፡’ ብዬ እመልሳለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ መንግስቱ እኔን ሲመርጠኝ ለስራዬ ብቻ ብሎ ሐላፊነት መስጠቱን ማመኔ ጠቅሞኛል፡፡ እኔ የባንኮች እርሱ ደግሞ የጊዮርጊስ አሰልጣኞች ሆነን “ወርቁ ዛሬ እነዚህን ስራዎች ነው የምታሰራው!” የሚል ትዕዛዝ ሰጥቶኝ ወደ ጊዮርጊስ ስራው ይሄዳል፡፡ እኔም የተሰጠኝን እሰራና እጠብቀዋለሁ፡፡ በሚቀጥለው ቀን ደግሞ እኔ ወደ ባንኮች ስሄድ እርሱ ይሰራል፡፡ በዚህ መንገድ የራስ መተማመኔን አዳበረልኝ፡፡ ከዚህ ቀደም በናንተው ደረ-ገጽ ለተዘጋጀው የመታሰቢያ ፅሁፍ የመንግስቱ ወርቁን የአሰልጣኝነት ህይወቱን ስትዳስሱ “የራስ መተማመኔን ከፍ ያደረገልኝ መንግስቱ ወርቁ ነው፡፡” የሚል ምስክርነት ሰጥቻችኋለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ በ1989 ዓ.ም ራሴ ብሄራዊ ቡድን ያዝኩኝ፡፡ ከመንግስቱ ጋር በሰራሁባቸው ሁለት አመታት ያገኘሁት ከፍተኛ የራስ መተማመን ለብቻዬ ሆኜ ስሰራ በእጅጉ ጠቀመኝ፡፡ እንደገና ደግሞ በ1996 ዓ.ም ጋሽ ስዩም አባተ መርጦኝ የእርሱ ምክትል ሆንኩ፡፡ ስዩምም የፈለገኝ ከመንግስቱ ጋር በነበረኝ ቆይታ የሰራሁትን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ምክትል አሰልጣኝ መመረጥ ያለበት ለስራው እንጂ ለዋናው አሰልጣኝ ባለው ቅርበት እና አመቺነት መሆን የለበትም፡፡ በችሎታው አምነህበት እንጂ ጓደኛህ ስለሆነ ልትመርጠው አይገባም፡፡ አስቡት- ከመንግስቱም ሆነ ስዩም ጋር የነበረን ትውውቅ በሙያ ላይ የተመሰረተ ሆኖ እንጂ ጓደኞቼ አልነበሩም፡፡ በጣም ያደገው የእግርኳስ ደረጃ ላይ እስከምንደርስ ይህንን ስርዓት ማሳደግ ይገባናል፡፡ እነሱ (ያደገው እግርኳስ ባለቤቶች) አጠቃላይ የአሰልጣኞች ቡድን አባላትን ራስህ እንድታዋቅር ይፈቅዱልሀል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ በደረጃቸውና በእውቀታቸው ተቀራራቢ ናቸው፡፡ እኛ ጋር እንዲህ አይነት ነገር የለም፡፡ ለምሳሌ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በተለያዩ ዘርፎች ሙያዊ እገዛ የሚያደርጉላቸውን ባለሙያዎች ሲመርጡ እያንዳንዱን ሰው በጥልቀት አጥንተውና በትክክል ሊያግዟቸው የሚችሉ መሆናቸውን እርግጠኛ ሲሆኑ ነው የሚያመጧቸው፡፡ እዚህ አገር ግን እኔ ይዤ የምመርጠው ጓደኛዬ በመሆኑ ብቻ ምናልባትም የc License ያለውን ሊሆን ይችላል፤ መጥቶ የሚረዳኝ ነገር ሳይኖር ኮን የመደርደርና የመሰብሰብ ስራ ይሰራል፡፡


በዋና አሰልጣኝነት እየሰራ ምክትሉን የሚመርጠው ሰው ከላይ በጠቀስከው አዎንታዊ አመለካከት የተቃኘ መሆን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶች በምክትልነት የሚሾሟቸውን ሰዎች “አመቺነት” ለራሳቸው ሲሉ ስለሚያስቀድሙ የሰዎቹን ብቃት ግንዛቤ ውስጥ ሳይከቱ ጥቃቅን ተግባራትን እንዲከውኑ ብቻ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህም መፍትሄው ከሿሚና ሻሪው በተጨማሪ በዋና አሰልጣኙ ቀና መንፈስ ላይ የተመሰረተም ይመስለናል፡፡ ስዩም አባተና መንግስቱ ወርቁ ባንተ የአሰልጣኝነት ህይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ የኖራቸው ከአንተ በላይ ስራህንና ችሎታህን አስቀድመው ምርጫ ስላደረጉ ነው፡፡

★በትክክል! ሁሉምማ ተመሳሳይ አይደሉም፡፡ ያልተለመደ በመሆኑም ቅር የሚሰኙ ዋና አሰልጣኞች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን ደግሞ የበላዩ አካል ለአሰልጣኙ ረዳቶቹን የሚመርጥበትን መስፈርቶች መስጠትም ይቻላል፡፡ ብቁ ሰው አብሮህ በመስራቱ እኮ ምስጋናውንም ተጠያቂነቱንም የጋራ ይሆናል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ሁሉም የየራሱ ድርሻ ስለሚኖረው ከተለያዩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎችም ሁነኛ መልስ ያገኛሉ፡፡


ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች አባላትን (በተለይም የዋናና ምክትል አሰልጣኞችን እርከን) በሚያዋቅርበት ጊዜ የተለመደ አሰራር አለ፡፡ ሁለት ተመሳሳይ የስራ ልምድ ባለቤቶች የሆኑ፣ በተቀራራቢ የውጤታማነት ሒደት ውስጥ ያለፉና በተመዛዛኝ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ አሰልጣኞችን መርጦ አንደኛውን “ዋና” ሌላኛውን ደግሞ “ምክትል” አሰልጣኝ አድርጎ ይሾማል፡፡ ሁኔታውን በአዎንታዊነት ለመመልከት የማይሹ ባለሙያዎች “ዋናውን-የበላይ” እና “ምክትሉን-የበታች” አድርገው የማሰብ አዝማሚያ ሊያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ ይህን አሉታዊ ስሜት ለማስቀረት ዋናው አሰልጣኝ የበታቾቹን የሚመርጥበት መንገድ መኖሩ በሰዎቹም ሆነ በስራው ላይ የሚፈጥረውን ጥሩ ያልሆነ ተጽዕኖ ያስቀራል የሚል እምነት አለ፡፡ ከዚህ አንጻር ያንተ አስተያየት ምንድን ነው?


★ እኔ ‘በስራው ላይ የሚፈጥረው ችግር አይኖርም፡፡’ እላለሁ፡፡ ምክንያቱም የተገናኙት ለስራ ነው፡፡ ዋናውም ምክትሉም የስራ ድርሻ እስካላቸው ድረስ ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ዋናው አሰልጣኝ ለምክትሉ እንዲሰራ የሚያዘውን በአግባቡ የሚፈጽምለት ከሆነ ስራው እኮ እየተሰራ ነው ማለት ነው፡፡ በመሰረቱ በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ሳንገኝ ከእርሱ አንሼ የተመረጥኩ ከሆነማ እኔ ላይ እምነት ኖሮት ሀላፊነት አይሰጠኝም፡፡ አንተን ዝም ብሎ ለስም ያስቀምጥህና ራሱ ሁሉን ሀላፊነቶች ለመወጣት ይሞክራል፡፡ መታመን ያለበት አብዩ ጉዳይ ዋና አሰልጣኝ ተደርጎ የተመረጠ ሰው በራሱም ሆነ በፌዴሬሽኑ አማካኝነት የሚመረጡለት ሰዎች <የሚሰሩ> እና ነገ ሀላፊነትን በጋራ ለመሸከም የተዘጋጁ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሜዳ ላይ በሚተገበሩ የቡድን ስራዎች ብዙ ዘርፎች አሏቸው፡፡ ዋናው አሰልጣኝ የተለያዩ ስራዎችን ሊቆጣጠር እንጂ በምንም መንገድ ብቻውን ሆኖ ሁሉንም ነገር መስራት አይችልም፡፡እንዲያም ቢሆን ግን በእኩል ደረጃ ሊሰሩ የሚችሉ ሰዎችን በአዛዥና ታዛዥ የኃላፊነት ተዋረድ ማሰራት እክል አይሆንም? ለምሳሌ በተከታታይ አመታት ዋንጫ ያስገኙ አሰልጣኞች ወደ ብሄራዊ ቡድኑ ቢመጡና አንተ በጠቀስከው መንገድ ዋናና ምክትል ሆነው የመስራት ፍላጎታቸውና ተነሳሽነታቸው ምን ያህል ይሆናል?

★ አንድ ማመን ወይም መረዳት ያለብን ነገር አለ፡፡ ሁላችንም እኮ በተመሳሳይ መስፈርት አንመረጥም፡፡ በሁሉም መመዘኛዎች ላይ እኩል ነጥቦችን አናገኝም፡፡ የእኔና የስዩም አባተን እንደ አብነት ላንሳላችሁ- ስዩም በ1996 ለኦሎምፒክ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ሲመረጥ በወጡት ማወዳደሪያ መስፈርቶች ከኔ የተሻለ ውጤት አገኘ፡፡ ” ወርቁ ላንተም የተሰጠህ ነጥብ አለ፤ ምክትልነቱን ትቀበላለህ ወይ?” ተብዬ ተጠየቅኩ፡፡ ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆንክ ሌላ በእኔ ደረጃ ያለ አሰልጣኝ ይፈልጋሉ፡፡ አምኜበትና ደስ ብሎኝ ሐላፊነቱን ተቀብዬ ምክትልነቱን ተረከብኩ፡፡ ከስዩም ጋር አብረን በቡና ገበያ ሰርተናል፡፡ ስለዚህ ስዩም እኔን ሲመርጠኝና በፌዴሬሽኑ ተቀባይነት ሲያገኝ “በእኔ ላይ ከፍተኛ እምነት አለው ማለት ነው፡፡” ብዬ ነው መረዳት የሚኖርብኝ፡፡ ይህን መሰል ፈቃደኝነት ማሳየት አለብን፡፡ “አይሆንም ስዩም! እኔ እንዴት ረዳትህ ሆኜ እሰራለሁ?” አላልኩም፡፡ እሱ ለአንድ አላማ እንደፈለገኝ እረዳለሁ፤ በተወሰነ ልምድ እንደሚበልጠኝም አምናለሁ፡፡ ያንን ተቀብዬ ወደ አቴንስ ኦሎምፒክ ለማለፍ ጫፍ የደረሰ ቆንጆ የኦሎምፒክ ቡድን ሰራን፡፡


አንተ ይህን ነገር በበጎ ጎኑ ተቀብለህ ትሰራለህ፡፡ ሆኖም ግን አስራት ኃይሌን የስዩም አባተ ምክትል አልያም ስዩም አባተን የአስራት ኃይሌ ረዳት አድርጎ መምረጥ ትንሽ አስቸጋሪ አይሆንም?

★ ሐሳቡ እኮ ገብቶኛል፡፡ በመጀመሪያ የመምረጫ መንገዶችን ስታወጣ የዚህ አይነት ነገር ሊኖር እንደሚችልና ኃላፊነቱ አገራዊ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንደምንሰራ ተማምነን መቀበል አለብን፡፡ አለበለዚያ ራሴን ማግለል ነው፡፡ አንደኛም ሆንኩ አምስተኛ አሰልጣኝ ለማገልገል የተነሳሁት ኢትዮጵያን በመሆኑ በዚያ አረዳድ ነው መታየት ያለበት፡፡ ለአገር ጉዳይ እንዲህ ካላሰብክማ መጀመሪያውኑም ቢሆን መምጣት የለብህም፡፡ ፌዴሬሽኑም ቢሆን ይህንን በእጩነት ለሚይዛቸው አሰልጣኞች በደንብ ማሳመን ይኖርበታል፡፡ በህብረት ስራ የሚያምነው ይስራ፤ የማይፈልገው ደግሞ ይሂድ- በቃ! ታችስ ተወርዶ ታዳጊዎች ላይ ይሰራ የለ እንዴ! ታዲያ ምንድን ነው ችግሩ? ያው እግር ኳሱን አይደለም እንዴ የምንሰራው? ዋናው ጥያቄ የደረጃው ጉዳይ ሳይሆን በጋራ የምታመጣው ውጤት ነው፡፡ በህብረት ሲሰራ በእርግጠኝነት ጥሩ ነገር ይመጣል ብዬ ነው የማስበው፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በስልጠናው ዘርፍ በችሎታ የተቀራረበና ሰፋ ያለ መጠን ያለው የአሰልጣኞች ቡድን አባላት ይኑሩ፡፡ ውይይቱ፣ ምክክሩና ክርክሩ ብዙ ያስገኘናል፡፡ ለብቻው ሶስትና አራት ገጽ የሚሆን ነገር ጽፎ እየሰጠህ የምትሰራ ከሆነ መጨረሻ ላይ በሚመጣው ጉዳይ ዝም ነው የምትለው፡፡ በጋራ ሰርቶ በጋራ መጠየቅ ነው መለመድ ያለበት፡፡


አንዳንድ አሰልጣኞች ውጤት ሲጠፋ በፌዴሬሽኑ የተመረጠላቸውን ምክትልና የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ” ለኔ የአጨዋወት ዘይቤ ተስማሚ ስላልነበሩ ልንግባባ አልቻልንም፡፡” የሚል ሰበብ ሲያቀርቡ ይሰማል፡፡የአሰልጣኞች ቡድን ሲመሰረት አባላቱ ምን አይነት ይዘት ሊኖራቸው ይገባል? በተመሳሳይ አስተሳሰብና ፍልስፍና የተሰባሰቡ ወይስ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው ሰዎች ስብጥር መሆን ይኖርበታል?

★ ሁሌም ቢሆን ተመሳሳይ የሆነ አስተሳሰብ ያለው የባለሙያዎች ስብስብ አታገኝም፡፡ አንድ መተማመን ያለብን ነገር አለ፡፡ በሁሉም የአሰለጣጠንም ይሁን የአጨዋወት ፍልስፍና ውስጥ የመጨረሻው ግብ ውጤት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ መጀመሪያ ውጤት ለማምጣት በአካሄዱ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ስምምነት ላይ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምንም እኮ የተለየ ነገር የለም፤ በቃ በተወሰነ መርሆዎች ላይ ከተግባባን ሁላችንም ጥሩ ጨዋታ የሚያሳዩና በአካል ብቃታቸው ጠንካራ የሆኑ ተጫዋቾችን እንፈልጋለን፡፡ ይህን የማይሻ ወይም የሚክድ አሰልጣኝ ካለ ምን ሊሰራ እንደሚመጣም ማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ” አይሆንም! እኔ የአካል ብቃት ልምምድ አላሰራም! ቅብብሎችን ብቻ ነው ትኩረት የምሰጠው፡፡” የሚልህ አሰልጣኝ የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ጥሩ የቴክኒክ ችሎታን የያዙ፣ የተሻለ የታክቲክ አረዳድና ግንዛቤ ያላቸው፣ ከዘጠና ደቂቃ በላይ ሊያጫውት የሚችል የአካል ብቃት ደረጃ ላይ የደረሱና በስነ ልቦናውም ‘አገራዊ ውጤት እናመጣለን!’ የሚል ጠንካራ እምነት ያላቸውን ተጫዋቾች መምረጥ ሁሉን የሚያስማማ እና ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡


በመሰረታዊ ነገሮች ላይ መስማማት ማለት ነው?

★ አዎ! በመሰረታዊዎቹ ግብዓቶች ላይ ከተስማማህ ሌላው ነገር የማያጣላ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ አሰለጣጠን መንገድ ላይ እንዲሁ ስናወራ ሃያ አመት ሞላን፡፡ ለነዚህ ሁሉ አመታት ሳንስማማ መቅረታችን ያሳዝነኛል፡፡ ባሳለፍናቸው የክርክር ጊዜያት ብዙ ነገር አበላሽተናል፡፡ ተጠያቂዎቹ ደግሞ እኛ ሁላችንም ነን፡፡ በሚዲያም ሆነ በስልጠናው አለም ያለን ሰዎች በዚህ ጉዳይ ተጸጻች መሆናችን አይቀርም፡፡ ስናወራው፣ ስናወራው፣……ምንም ያመጣነው ነገር የለም፡፡ ከሁለቱም ወገን የተውጣጡ አምስት ወይም ስድስት ሰዎች ቁጭ ብለው ቢነጋገሩ ይስማማሉ፡፡ “ጥሩ ኳስ የሚጫወት፣ Physically fit, endured እና flexible የሆነ፣ እልህና ወኔ ያለው ተጫዋች እንፍጠር!” ቢባል ማነው የሚጠላው? አስታውሳለሁ፤ ካሳዬ የኔ ተጫዋች ነበር፤ በብሄራዊ ቡድንም መርጬው የምፈልገውን ነገር እንዲሰራልኝ አድርጌዋለሁ፡፡ ጥሩ ሰርቶልኛል፤ እሱም ያምንበታል፤ ውጤትም አምጥተንበታል፡፡ እያጠቃ በሚከላከል ቡድን ውስጥ አጥቂምው ሆነ ተከላካዩ በሜዳ ላይ እኩል ድርሻ ሲኖራቸውና አጥቂው ለመከላከል ተከላካዩም ለማጥቃት በሚያደርጉት ምልልሳዊ እንቅስቃሴ ተጫዋቾች በአካል ብቃቱ ረገድ ብቁ ሆነው መገኘት አለባቸው፡፡ በቃ ጥያቄው እንደነዚህ አይነት ተጫዋቾችን እንፍጠርና እንምረጥ ነው፡፡ “እኔ እገሌን ነው የምመርጠው፤ ቆሞ ይጫወታል፥ኳሱን ብቻ ስጠው፡፡” ማለት አይሰራም ፡፡እግርኳስ የሚፈልጋቸውን መሰረታዊ ግብዓቶች ሊያሟሉ የሚችሉ ተጫዋቾችን መምረጥ ሁላችንም የሚያስማማ መፍትሄ ነው፡፡