ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ |  የግንቦት 10 ተስተካካይ ጨዋታዎች

በሳምንቱቱ መጀመሪያ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎችን አስተናግዶ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ ደግሞ ሌሎች ሁለት ጨዋታዎች እንደሚደረጉበት ይጠበቃል። ድሬደዋ እና መቐለ ላይ የሚደረጉት እነዚህ ጨዋታዎች የዛሬው ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ ትኩረቶች ይሆናሉ።

ድሬደዋ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ከዚህ ጨዋታ የሚገኙ ነጥቦች ከወላይታ ድቻ በላይ ለባለሜዳው ድሬደዋ ከተማ እጅግ አስፈላጊዎች ናቸው። በሊጉ ግርጌ ተቀምጦ ያለው ድሬደዋ በጊዚያዊነትም ቢሆን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እና ቀጣይ ጨዋታዎችን በተሻለ የዐዕምሮ ደረጃ ላይ ተገኝቶ ለማድረግ የዛሬዎቹን ሶስት ነጥቦች የመሰብሰብ ግዴታ ይኖርበታል። ከሜዳው ውጪ በደካማ ሪከርዱ ይቀጠለው ወላይታ ድቻ በበኩሉ እንደተጋጣሚው ጫና ውስጥ ሆኖ የሚያከናውነው ጨዋታ ባይሆንም ራሱን ከመሀል ሰፋሪነት ለማላቀቅ የሚያገኘው የመጨረሻ ዕድል ይመስላል። ውድድሩ ከመቋረጡ አስቀድሞ ሜዳው ላይ ካስተናገደው ሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው ድሬደዋ ከተማ በ17ኛው እና 18ኛው ዙሮች አራት ነጥቦችን አሳክቶ የነበረ ቢሆንም በመሀል በአዳማ ከተማ ሽንፈትን ቀምሷል። ግብጠባቂው ወንደሰን ገረመው ላይ ቅጣት ያስተላለፈው ወላይታ ድቻ ደግሞ ከበርካታ ሳምንታት በኃላ ከሜዳው በወጣባቸው ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ገጥሞት ነው ወደዚህ ጨዋታ የሚያቀናው።

በጨዋታው የተሰማው ብቸኛ የጉዳት ዜና በሀዋሳው ጨዋታ በእጁ ላይ ጉዳት ያስተናገደው የድሬደዋ ከተማው አማካይ ሚካኤል አካፉ ብቻ ሲሆን ቀሪዎቹ የሁለቱም ቡድኖች ተሰላፊዎች ሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ።

ጥንቃቄ የተሞላበት እንደሚሆን በሚጠበቀው ጨዋታ ለኳስ ቁጥጥር ቦታ ያላቸው ሁለቱ ቡድኖች አማካይ ክፍል ላይ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል። የድሬደዋው የኢማኑኤል ላርያ እና ሳውሬል ኦልሪሽ ጥምረት ከበዛብህ መለዮ እና አብዱልሰመድ አሊ የሚገናኙባው አጋጣሚዎች ተጠበቂ ሲሆኑ ኃይማኖት ወርቁም የድሬደዋን ሶስት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች ለመቆጣጠር የመስመር አማካዮቹን እገዛ የሚፈልግ ይሆናል። የፊት አጥቂያቸው አትራም ኩዋሜ ከጉዳት ተመልሶ ግብ ያስቆጠረላቸው ድሬዎች ዛሬም በዋነኝነት ከአማካይ ክፍሉ ወደጋናዊው አጥቂ በሚላኩ ኳሶች ላይ ተነስርተው እንደሚያጠቁ ይጠበቃል። በዚህም አትራም በድቻ የተከላካይ እና የአማካይ ክፍል መሀል በሚኖሩ ክፍተቶች ያለኳስ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ወሳኝ ይሆናሉ። ፀጋዬ ብርሀኑ እና እርቅይሁን ተስፋዬ ከጉዳት መመለሳቸውን ተከትሎ አማራጮች የበዙለት የሚመስለው ወላይታ ድቻ በበኩሉ በማይለዋወጥ የመጀመሪያ አሰላለፍ ያገኘውን የቡድን ውህደት በመጠኑ እያጣ የመጣ ይመስላል። አሰልጣኝ ዘነበ በማጥቃት ሂደት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑ ተጨዋቾች ላይ ቅያሪዎችን ሲያደርጉ መታየቱ ለዚህ አንዱ ማሳያ ሲሆን ቡድኑ የፊት አጥቂው ጃኮ አራፋትን መሰረት ያደረገ ማጥቃትን ቢተገብርም ከመስመር አማካዮቹ እንቅስቃሴ መነሻነትም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እንደሚሞክር ይጠበቃል።

የእርስበእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ሁለቱ ቡድኖች 5 ጊዜ በሊጉ ተገናኝተው ድሬዳዋ ሁለት ጊዜ በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን 3 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። ወላይታ ድቻ ድሬዳዋን አሸንፎ አያውቅም። እስካሁንም ድሬ 4 ፣ ድቻ 1 ጎሎች አስቆጥረዋል።

– ድሬዳዋ ላይ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች አንዱን ድሬዳዋ ሲያሸንፍ በሌላኛው አቻ ተለያይተዋል። ድሬ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ድቻ በሁለቱም አጋጣሚዎች ጎል አላስቆጠረም።

– ድሬደዋ ከተማ በ13ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ከገጠመው ሽንፈት በኃላ ካደረጋቸው 5 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ በሶስቱ አቻ ተለያይቷል።

– ወላይታ ድቻ በሁለተኛው ዙር ወደ አዳማ እና መቐለ ካደረጋቸው ጉዞዎች ምንም ነጥብ ያላሳካ ሳይሆን ዛሬ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ ከሜዳው ውጪ የሚጫወት ይሆናል።


Hulusport.com | ሊንኩን ተጭነው ይወራረዱ


መቐለ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር የአዲስ አበባ ስታድየም ጨዋታ ያስተናገደው ፉክክር በብዙዎች የሚዘነጋ አይደለም። አሁን ደግሞ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ሆነው መገናኘታቸው የጨዋታውን ትኩረት ከወዲሁ ከፍ አድርጎታል። ከዛሬው በተጨማሪ ከወልዋሎ ዓዲግትራ ዩኒቨርሲት ያልተጠናቀቀ ጨዋታ የሚቀረው መቐለ ከተማ ሙሉ ውጤት ካገኘ ሊጉን የመምራት ዕድል ይኖረዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስም አሸናፊ ከሆነ ከመሪው ጅማ አባ ጅፋር ጋር ራሱን በነጥብ ማስተካከል የሚችል ይሆናል። የጨዋታው ውጤት ለሁለቱም ከሚያስገኝላቸው የደረጃ መሻሻል ባለፈ ሁለቱም ቡድኖች ከድል መልስ መገናኘታቸው የ9 ሰዐቱን ጨዋታ አጓጊ አድርጎታል። በ18ኛው ሳምንት ይህ መርሀግብር ካለፈው በኃላ ከሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ አሳክቶ የነበረው መቐለ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት በደደቢት እና ወላይታ ድቻ ላይ ያሳካቸው ተከታታይ ድሎች ወደ አሸናፊነት መልሰውታል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የ18ኛው እና 20ኛው ሳምንት ጨዋታዎችን ሳይከናውን ግን ደግሞ ሶስት ተከታታይ ድሎች ከቀኑት በኃላ በአርባምንጭ ከተማ ከደረሰበት ሽንፈት ባሳለፍነው ሰኞ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመርታት ወደ ድል አድራጊነት መመለሱ ይታወሳል።

ባለሜዳዎቹ መቐለዎች ከጉዳት እና ቅጣት ነፃ ሆነው ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግን የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው ሳላዲን ሰይድን ጨምሮ በኢትዮ ኤሌክትሪኩ ጨዋታ ጉዳት የገጠማቸው አማራ ማሌ እና ሪቻርድ አፒያ እንዲሁም ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ የወጣው አቡበከር ሳኒ የማይሰለፉ ይሆናል።

ከተጋጣሚዎቹ የቡድን መዋቅር ጥንካሬ አንፃር ጨዋታው በተለያዩ የሜዳው ክፍሎች ላይ ብርቱ ፉክክር የሚደረግባቸውን ቅፅበቶች እንደሚያሳየን ይገመታል። በጋቶች ፓኖም መምጣት ይበልጥ የተጠናከረው የዐመለ ሚልኪያስ እና ሚካኤል ደስታ ጥምረት እንደ አስፈላጊነቱ የቦታ ልውውጥ ሲያደርግ ቢታይም በተለይ በመከላከሉ በኩል ተጠናክሮ ቀርቧል። በመሆኑም በአብዱልከሪም ኒኪማ የሚመራው የቅዱስ ጊዮርጊስ የማጥቃት አማካዮች ጥምረት ቀጥተኛ ቅብብሎችን ከማድረግ ይልቅ በማጥቃት ላይ እምብዛም ሲሳተፉ ከማይታዩት የመቐለ መስመር ተከላካዮች ብዙ ክፍተት እንደማያገኙ ወደሚጠበቁት መስመር አጥቂዎቹ አመዝኖ እንደሚጫወት ይገመታል። ሆኖም በጉዳት እና ቅጣት የሳሳው የቡድኑ የፊት መስመር በዋነኝነት በበሀይሉ አሰፋ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ መሰረት እንደሚያደርግ ይገመታል። የፊት አጥቂነት ዕድሉን ዳግም የሚያገኘው አሜ መሀመድም ከተሻጋሪ ኳሶች መነሻነት የሚገኙ አጋጣሚዎችን ወደ ግብ የመቀየር ሀላፊነት ይኖረዋል። እንደአማካይ ክፍሉ ሁሉ ተለዋዋጭ የሆነው የአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ቢስማርክ ኦፖንግ ጥምረት ደግሞ እነደ ኑሁ ፋሰይኒ አይነት ታታሪ ተሰላፊዎቹን በመጠቀም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ከናትናኤል ዘለቀ ግራ እና ቀኝ ከሚገኙ ቦታዎች ላይ በሚነሱ ኳሶች ጥቃት እንደሚሰነዝር ይጠበቃል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመሀል ተከላካይ ክፍል አካላዊ ጥንካሬ አንፃር አማኑኤልን ወደ መስመር በማውጣት ለኦፖንግ የፊት አጥቂነቱን ሀላፊነት እንደሚሰጡ የሚጠበቁት መቐለዎች ከአማካይ ክፍላቸው ከሚነሱ ኳሶች ፍጥነታቸውን በመጠቀም ከተጋጣሚያቸው ተከላካዮች ጀርባ በሚኖረው ክፍተት በመጠቀም ላይ እንደሚያተኩሩ ይታሰባል። በዚህም በጥሩ አቋሙ ከገፋበት መሀሪ መና እና አብዱልከሪም መሀመድ ጋር የሚኖሩት የአንድ ለአንድ ፍልሚያዎች ወሳኝ ይሆናሉ።

የእርስበእርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ የሊግ ግንኙነት ዘንድሮ በ3ኛው ሳምንት የተደረገ ሲሆን ውጤቱም 1-1 ነበር።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሜዳው ውጪ ካደረጋቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች መሀል በሶስቱ ሽንፈት ሲገጥመው አንዴ በድል አንዴ ደግሞ በአቻ ውጤት ተመልሷል።

– መቐለ ከተማ ሁለተኛው ዙር ከተጀመረ ሜዳው ላይ ያደረጋቸው ጨዋታዎች ሁለት ብቻ ሲሆኑ በድምሩ ስድስት ግቦችን አስቆጥሮ መረቡን ሳያስደፍር መሉ ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል።

– ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ መቐለ ተጉዞ ለመጨረሻ ጊዜ ባደረገው ጨዋታ በ2003 ትራንስ ኢትዮጵያን 1-0 አሸንፎ ተመልሷል።