ሪፖርት | ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ፋሲልን በመርታት ወደ ድል ተመልሷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መደበኛ መርሐ ግብር በ23ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሲቀጥል ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ ፋሲል ከተማን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።

ባለሜዳዎቹ ሀዋሳ ከተማዎች በ22ኛው ሳምንት ድሬደዋ ላይ ከተጠቀሙት የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ መሀመድ ሰይላ ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ዳዊት ፍቃዱን በመሳይ ጳውሎስ ፣ አስጨናቂ ሉቃስ እና ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ለውጠዋል። በፋሲል ከተማ በኩል ደግሞ ይስሀቅ መኩሪያ እና ኤርሚያስ ኃይሉ በሙሉቀን አቡሀይ እና መጣባቸው ሙሉ ምትክ የገቡበት ለውጥ ጎንደር ላይ ያለግብ በተጠናቀቀው የአዳማው ጨዋታ ላይ ከጀመረው ስብስብ በተለየ የታየ ቅያሪ ነበር።ከጨዋታው አስቀድሞ የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ለዳኞች ክብር አለን በማለት እስከ ጨዋታው ፍፃሜ ያላቸውን አክብሮት የገለፁበት መንገድ የተለየ ክስተት ነበር። ልክ 9፡00 ላይ በኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ታጅቦ በፌደራል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ መሪነት የጀመረው ጨዋታ የሀዋሳዎችን የተለመደ ኳስ ይዞ የመጫወት ሂደት እንዲሁም በመከላከል ላይ ትኩረት ያደረገ እና መጠነኛ የማጥቃት ፍላጎት የታየበትን የፋሲል ከተማን አቀራረብ አስመልክቶናል።

ሀዋሳ ከተማ 4-2-3-1 እንዲሁም ፋሲል ከተማ 4-3-3 አሰላለፍን ሲተገብሩ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ተመሳሳይ የጨዋታ አቀራረብ እና ይዘት የነበራቸው ቢሆንም የኋላ ኋላ የሀዋሳ ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር። በተለይ በሁለቱም ኮሪደሮች በቀኝ እና በግራ የተሰለፉት አዲስዓለም ተስፋዬ እና ደስታ ዮሀንስን ማዕከል ያደረጉ እንቅስቃሴዎች እና በመሀል ሜዳ ላይ ታፈሰ ሰለሞን ልዩነት መፍጠር የቻለበት ሂደት የታየ ሲሆን አፄወቹ በአንፃሩ ኄኖክ ገምቴሳ እና ተከላካዩ ሰንደይ ሙቱክ ለራምኬል ሎክ እና ኤርሚያስ ኃይሉ በረጅሙ በሚጥሏቸው ኳሶች ለመጠቀም ሞክረዋል። ሆኖም ኤርሚያስ እያገኘ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ መሳይ ጳውሎስ በተደጋጋሚ እንዲቋረጡ የሚያደርጋቸው ኳሶች ሲባክኑ ታይተዋል። 

በ6ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች ያገኟትን የቅጣት ምት አዲስአለም ተስፋዬ አክርሮ ሲመታ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት አጋጣሚ የጨዋታው ቀዳሚዋ ሙከራ ነበረች። ከአንድ ደቂቃ በኃላ ደግሞ እስራኤል እሸቱ በቀኝ መስመር በኩል ከግብ ጠባቂው ሚካኤል ሳማኬ ጋር ተገናኝቶ የሞከረው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። 17ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ አዲስዓለም ከታፈሰ ጋር ባደረገው አንድ ሁለት ቅብብል ታፈሰ ለፍሬው አመቻችቶለት ፍሬው በቀጥታ ቢሞክርም ግብ አልቀናውም።  ፋሲሎች የጨዋታ ሂደታቸው በመስመር ላይ ያጋደለ ቢመስልም የመጨረሻው የኳሱ ማረፊያ ግን በቀላሉ የሚባክን ሲሆን ተስተውሏል። 22ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ሎክ በግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ኤርሚያስ ከግብ ጋር ቢገናኝም አስጨናቂ ሉቃስ እንደምንም አስጥሎታል።

ፋሲሎች እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ በረጅሙ በሚሻገሩ ኳሶች ለመጠቀም ጥረት ቢያደርጉም ጥረቶቻቸው የመሳይ ጳውሎስ ሲሳይ ሆነዋል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በ28ኛው ደቂቃ ራምኬል በተመሳሳይ የጣለውን ኳስ ኤርሚያስ አግኝቶ አልፎ ወደ ግብ ሲሄድ መሳይ እንደምንም የነጠቀበት ሂደት ነው። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኄኖክ ገምቴሳ ከማዕዘን ምት ሲያሻግር በሳጥን ውስጥ ራምከል አግኝቶ ሲሞክር ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ ምናልባትም አፄወቹን ቀዳሚ የምታደርግ ዕድል የነበረች። 33ኛው ደቂቃ ላይ ሀዋሳዎች በታፈሰ ሰለሞን አማካይነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጭ ተብሎ የተሻረባቸው ሲሆን ወደ እረፍት ለማምራት ሁለት ደቂቃዎች ሲቀራቸው ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ደግሞ ሚካኤል ሳማኪ በቀላሉ ይዞበታል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ማጥቃት ላይ መሰረት አድርገው የገቡት ሀዋሳ ከተማዎች ፍፁም ብልጫ የነበራቸው ሲሆን ፋሲሎች ከመጀመሪያው አጋማሽ ተዳክመው የታዩበት ነበር። ፋሲሎች በመሀል ሜዳ ላይ እንዲበለጡ ምክንያት ነው ያሉትን ያስር ሙገርዋን በኤፍሬም አለሙ መተካታቸው በመጠኑም የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴያውቸ እንዲረጋጋ አስችሏል። ጥሩ ሲንቀሳቀስ በነበረው ኤርሚያስ ሀይሉ ምትክ ፊሊፕ ዳውዝን ቀይረው ማስገባታቸው ደግሞ የማጥቃት ኃይላቸውን አዳክሞታል። ሀዋሳዎች በአንፃሩ በጉዳት የወጣው እስራአል እሸቱን በዳዊት ፍቃዱ ፣ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን በያቡን ዊሊያም መለወጣቸው ስኬታማ ሆኖላቸዋል።

ገና ከመግባታቸው አንድ ደቂቃ እንደተቆጠረ ሙሉዓለም ረጋሳ በረጅሙ ከላካትን ኳስ እስራአል እሸቱ ሞክሮ ለጥቂት ወጥታበታለች። በተደጋጋሚ ወደ ፋሲል የግብ በር አጋድለው መጫወት የቻሉት ሀይቆቹ በ55ኛ ደቂቃ ላይ ደግሞ ታፈሰ ሰለሞን የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ወደ ግብ አክርሮ የመታት እና ሳማኬ በሚገባ ያላራቃትን ኳስ እስራኤል አግኝቷት ወደ ግብ ከመቀየሩ በፊት ኬኒያዊው ተከላካይ ሰንደይ ሙቱክ ደርሶ አስጥሎታል፡፡ ፋሲሎች በመልሶ ማጥቃት 58ኛው ደቂቃ ላይ ሀሚዝ ኪዛ ካደረሳት ኳስ ኤርሚያስ ሀይሉ ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳህ ጋር ተገናኝቶ ሜንሳህ እንደምንም አውጥቶበታል። 62ኛው ደቂቃ ላይ ግን በግራ የፋሲል የግብ ክልል በሙሉአለም ረጋሳ ላይ በተሰራ ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ደስታ ዮሀንስ ወደ ግብ ሲያሻማ ጋናዊው የመሀል ተከላካይ ላውረንስ ላርቴ በግንባሩ በመግጨት ግብ ማስቆጠር ችሏል። ላውረንስ በሀዋሳ መለያ የመጀመሪያ ግቡን ነው ያስቆጠረው።

ጫና በመፍጠር በተሻለ መልኩ ብልጫን ያሳዩት ባለሜዳወቹ 75ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት አጋጣሚ ደዊት ፍቃዱ ለዊሊያም ሰጥቶት ዊሊያም ወደ ግብ ሲመታት ሚካኤል ሳማኪ በቀላሉ ይዞበታል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ደስታ ዮሀንስ በረጅሙ የላካትን ኳስ ያቡን ዊሊያም በነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ፍሬው ሰለሞን አሳልፎለት ፍሬው በቀላሉ ማስቆጠር የሚችልበትን አጋጣሚ በይስሀቅ መኩሪያ ተነጥቋል።

80ኛው ደቂቃ ላይ በእለቱ በመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ላይ ልዩነት ሲፈጥር የነበረው ታፈሰ ሰለሞን በቀኝ በኩል ለዳዊት ፍቃዱ አቀብሎት ዳዊት እየገፋ ገብቶ ለደስታ ዮሀንስ ሰጥቶት ደስታ ከግብ ክልሉ መስመር ጠርዝ የሳማኪን መውጣት ተመልክቶ በመቁረጥ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ የሀዋሳን የግብ መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል። ከግቧ መቆጠር በኃላ ያሉትን ቀሪ ደቂቃዎች ሀዋሳ ከተማዎች ማራኪ ቅብብሎችን በማድረግ ያሳለፉት እና ፋሲል ከተማዎች አንድም ኳስ ለመንጠቅም ሆነ ወደ ግብ ለመድርስ ያልቻሉበትን እንቅስቃሴ ያሳየን ነበር። የመጨረሻው ደቂቃ ላይ አዲስአለም ከመሀል ሜዳ በቀጥታ ግብ ቢያስቆጥርም የእለቱ ዳኛ ሰአት ተጠናቋል በማለት ግቧን ሲሽሯት የሀዋሳ ከተማ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች ግን ግብ መስሏቸው ደስታቸውን ሲገልፁ አስተውለናል፡፡ ጨዋታውም በዚህ መልኩ በሀይቆቹ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ውበቱ አባተ – ሀዋሳ ከተማ

ጨዋታው ሊጉ ተቋርጦ ከጨዋታ ርቀን የነበረ ከመሆኑ አንፃር ጥሩ ነበር። በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ጥሩ ለመጫወት ሞክረዋል። እኛ ግን በሁለተኛ አጋማሽ ያን አርመን ጥሩ ተጫውተን አሸንፈናል። እነሱም ግብ እንዳይቆጠርባቸው ሲጠነቀቁ ነበር ፤ በትዕግስት መጫወታችን ግን እንድናሸንፍ አስችሎናል።

መሳይ ተፈሪ – ፋሲል ከተማ

ሀዋሳ በሜዳው ምን እንደሚያደርግ የሚታወቅ ነው። እኛ ደግሞ የመረጥነው አጨዋወት ዞናል ነበር። ከአሁን በኃላ በተለይ ከስነ-ልቡና እና ከማጥቃት ጋር በተያያዘ መስራት ያለብን ስራ አለ። በዚህ ጨዋታ እኛ የማጥቃት እንቅስቃሴያችን ደካማ ነበር። ሀዋሳ የተሻለ ስለነበር አሸንፎናል ፤ ይህ በእግር ኳስ የሚያጋጥም ነው ።በቀጣይ ሰርተን ወደ ማሸነፍ እንመጣለን።