በቡና ማልያ የመጀመርያ ጎሉን ያስቆጠረው ቃልኪዳን ዘላለም…

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ትላንት 11:00 ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ ቡና እና ደደቢት ጨዋታ ሲገባደድ የመርሐ ግብሩን ማሳረጊያ ጎል ያስቆጠረው ወጣቱ አጥቂ ቃልኪዳን ዘላለም ነው።

በኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ስር ያለፈው አጥቂው ቃልኪዳን ከአምና ጀምሮ ወደ ዋናው ቡድን እየተመላለሰ መጫወት የጀመረ ሲሆን በትላንትናው የሳምንቱ ታላቅ ጨዋታ ላይ በተጠባባቂ ወንበር ላይ በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ የመቀመጥ እድል አግኝቷል። 

ክለቡ በጨዋታው እየተመራ የነበረበት ወቅት በ82ኛው ደቂቃ የመስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገብረትንሳይን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ከግራ መስመር እየተነሳ ወደ ውስጥ በመግባት በቀሩት ደቂቃዎች የጎል እድሎች መፍጠር ችሏል። የቡድኑን የአቻነት ጎል ለማስቆጠር የፈጀበት ደቂቃም 8 ብቻ ነበር። ከግራ መስመር ያገኘውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት በማስቆጠር ለክለቡ አንድ ነጥብ አስገኝቷል።

ቃልኪዳን ከጨዋታው በኋላ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጠው አጠር ያለ አስተያየት ጎል ማስቆጠሩ የፈጠረበትን ደስታ ገልጿል። ” የአመቱ የመጀመርያ ጨዋታዬን በዚህ ወሳኝ ፍልሚያ ላይ ማድረግ መቻሌ ትልቅ ነገር ነው። ተቀይሬ ከገባሁ በኋላ የቡድኑን የአቻነት ጎል በማስቆጠሬ ደግሞ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። ” ብሏል።

ወጣቱ አጥቂ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ማልያውን አውልቆ በግራ ጥላፎቅ ወደሚገኙ ደጋፊዎች በመሮጥ በቲሸርቱ ላይ ያሰፈረውን ፅሁፍ ሲያሳይ ተስተውሏል። ቃልኪዳን ያሳየው ፅሁፍ ከእለቱ ጋር ተያያዥ እንደሆነም ይናገራል። ” ዛሬ ቀኑ ግንቦት 21 (ማርያም) በመሆኑ በዚህ ቀን ጎል በማስቆጠሬ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ተቀይሬ ከገባሁ ጎል እንደማስቆጥር አስብ ስለነበር በማልያዬ ውስጥ በለበኩት ልብስ ላይ ‘ማርያም’ የሚል ፅሁፍ አስፍሬ ነበር። ጎሉ ከተቆጠረ በኋላ ይህን ፅሁፍ ወደ ተመልካች በመሔድ አሳይቻለሁ። ”

በህዳሴ ግድብ ዋንጫ ላይ ጨዋታዎች ማድረግ የቻለው ቃልኪዳን በፕሪምየር ሊጉ ለመጀመርያ ጊዜ የተጫዋቾች ዝርዝር ውስጥ በተካተተበት ጨዋታ የመጀመርያ ጨዋታውን አከናውኖ የመጀመርያ ጎል እና የማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከት የሚታወስ እለትን አሳልፏል።